በልጉና በቆሎ

እያደገ ለመጣው የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ግብዓት ከሚሆኑ ዋነኛ የሰብል ዓይነቶች አንዱ የሆነው በቆሎ በፊት መሪነት ደረጃ ከሚገኙት የብርዕ ሰብል መካከልም አንዱ ሲሆን፣ ሰፋ ባለ የአየር ፀባይ ባለበት አካባቢ በዋነኝነት በወይናደጋ አካባቢ ይበቅላል፤ ይመረታል፡፡

የበልግ ዝናብ ባለባቸው አካባቢዎች (ከቅርብ ዘመዶቹ አንዱ የሆነው ማሽላን ጨምሮ) በየካቲትና በመጋቢት ወራት የሚዘራ ሲሆን፤ በአንዳንድ አካባቢዎች በሚያዝያና ግንቦት ወራት ይዘራል። ሁለት የዝናብ ወቅት ባሉባቸው አካባቢዎች በዓመት ሁለት ጊዜ የሚዘራበት አጋጣሚም አለ። ይሁን እንጂ፣ እንደ ገበያው ስፋት ከዚህ በላይ በብዙ እጥፍ መመረት የነበረበት ከመሆኑ አኳያ ምርቱ በቂ አለመሆኑ ይነገራል።

ማእከላዊ እስታቲስቲክስ ኤጄንሲ፣ የምርት ትንበያ ናሙና ዳሰሳ 2011/12 (እ.ኤ.አ), (ቡለቲን 532) እንዳሚያመለክተው በቆሎ አምራች አካባቢዎቻችን ብዙ ሲሆኑ፣ በክልል ደረጃ ኦሮሚያ 2,880,600 ቶን (57.8%)፣ አማራ 1,214,807 ቶን (24.4%)፣ ደቡብ 556,547 ቶን (11.2%)፣ ትግራይ 149,853 ቶን (3.0%)፣ ሌሎች 184,325 ቶን (3.0%) ምርትን ለሀገሪቱ ያበረክታሉ። በተለይ ከደቡብ ክልል ዞኖች ስልጤ 96,980 ቶን የቦቆሎ ምርትን በመስጠት ይገኛል።

ከኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጠቃሚ ከሆኑ ሰብሎች መካከል አንዱ የሆነውን በቆሎ በኩታገጠም በማምረት ምርታማነቱ ከፍ እንዲል በርካታ የጥናትና ምርምር ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።

ከዚሁ ተቋም የተገኘ መረጃ (2024) እንደሚያሳየው በበቆሎ ምርት ላይ ከ48 በላይ የምርምር ሥራዎች የተሠሩ ሲሆን፤ በቆሎን በኩታገጠም በማምረት ምርታማነትን መጨመር ተችሏል (የበቆሎ ምርታማነት በሄክታር ከ20 ኩንታል ወደ 46 ኩንታል ከፍ ማለቱንም ይገልፃል)። እንደዚሁ ተቋም ከሆነ፣ በቀጣይ የበቆሎ ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግ በቴክኖሎጂ የታገዙ የምርምር ሥራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል።

በቀድሞው በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የግብርና ግብይት ሥርዓት መጠናከሪያ ጥናት ላይ እንደሰፈረው፣ በቆሎ በኢትዮጵያ የብርዕ ምርቶች ከፍተኛውን ድርሻ ከሚይዙት ምርቶች ተርታ የሚመደብ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ጠቅላላ የበቆሎ ምርት መጠን 4,986,132 ቶን ይሆናል። ዋንኛው የበቆሎ አምራች አካባቢዎችም ከ1500-2200 ሜትር ከባሕር ወለል በላይ የሆኑ አካባቢዎች ናቸው፡፡

የኦሮሚያ ክልል ዋነኛው የበቆሎ አምራች አካባቢ ሲሆን የምርት መጠኑ 2,880,600 ቶን ሲሆን በሀገሪቱ 57.8% ድርሻን ይሸፍናል። የአማራ ክልል 1,214,807 ቶን (24.4%) ምርት ድርሻን በመያዝ 2ኛ፤ የደቡብ ክልል በሀገር ደረጃ 3ኛ የበቆሎ አምራች ሲሆን የምርት መጠኑም 556,547 ቶን እና 11.2% በሀገር አቀፍ ደረጃ ድርሻ እንዳለው በዚሁ ጥናት ላይ ሰፍሮ ይገኛል።

ጥናቱ እንደሚያመለክተው፣ እስከ 90% የሚደርሰው ምርቱ ለቤት ውስጥ ፍጆታ የሚውለው በቆሎ በደቡብ ዞኖች እስከ 75% በበልግ ወቅት የሚመረት ሲሆን፤ የሽያጭ መጠኑ ዝቅ ያለ ነው።

ገበያን በሚመለከት አርሶ አደሮች ምርታቸውን በአቅራቢያ ወደ አለው ገበያና የመሰብሰቢያ ጣቢያ በአህያ፣ በፈረስ ወይም በጋሪ ያመጣሉ። አርሶ አደሮች ማጠራቀሚያ ጐተራ የሌላቸው በመሆኑ ምርት ከሰበሰቡ በኋላ ብዙም ሳያቆዩ በትርፍነት ያለውን እህል ገበያ አውጥተው ይሸጣሉ። ይህ ደግሞ፣ በተለይ ምርቱ በአፍሪካ ደረጃ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለውና ለወጪ ንግድ መዋል የሚገባው ከመሆኑ አኳያ ከፍተኛ ጉዳት አለው። በመሆኑም ገበያና ግብይቱን የማዘመን ሥራ ሊሠራ ይገባል።

በዚሁ ከላይ በጠቀስነው የመረጃ ምንጭ ላይ በማሳያነት እንደሰፈረው በከፋ ዞን በማሣ ላይ ዋጋ 175ብር በ100 ኪ.ግራም ይሆናል። ምርት ማጓጓዝ ዋጋ በአይሱዙ የጭነት መኪና 80 ብር በ100 ኪ.ግራም ነው። የደላላ ኮሚሽን 5 ብር በ100 ኪ.ግራም ነው። ምንም እንኳን ዛሬ ይህ ዋጋ በሕይወት አለ ብሎ መናገር ባይቻልም እንደ አጠቃላይ ያለውን የበቆሎ ገበያ ትስስር ችግር ያሳያልና ምርቱ ሀገርና ሕዝብን በሚጠቅም፤ ኢኮኖሚውን በሚደጉም መልኩ ጥቅም ላይ (በተለይም ለወጪ ንግድ) መዋል አለበት የሚለው የብዙዎች ምክር ነው።

“በአማራ ክልል በመስኖ ከለማው የበቆሎ ሰብል 2ሺህ 948 ሄክታሩ በአሜሪካ መጤ ተምች መወረሩንና ለመከላከል ጥረት እየተደረገ” መሆኑን የሰማንበት የአንድ ሰሞን አሳዛኝ ዜናም እንዳይደገም የመከላከል ሥራን መሥራት የሁል ጊዜ የቤት ሥራችን ሊሆን ይገባል።

በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ስር ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ፕሮጅክት (የግብርና ባዮ-ቴክኖሎጂ መድረክ (ኦፋብ ኢትዮጵያ)) የሥራ ሃላፊዎች እንደሚናገሩት በበቆሎ ላይ የቴክኖሎጂ ሥራዎችን በመሥራት ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት የሚቻል ሲሆን (እየመጣም ነው)፤ ተቋማቸውም በባዮ-ቴክኖሎጂ አማካኝነት የቦቆሎን ምርት ማሳደግ የቻለ መሆኑን ይናገራሉ። “የአፍሪካ አህጉርን የሥርዓተ ምግብ አቅም መገንባት፣ የሰው ሀብት ልማት፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማትን ማፋጠን” በሚል መሪ ቃል የተከበረው 35ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባዔም ትኩረቱ በቆሎንና ሌሎቹንም በዚሁ በባዮ-ቴክኖሎጂ በመደገፍ ማልማት ተገቢ መሆኑን እንደሚያካትት ልብ ማለት ያስፈልጋል።

በመጨረሻም ወደዚህ ጽሑፍ አጠቃላይ ዓላማ ወደሆነው ወጪ ንግድ እንምጣ።

በመስኖ ልማት አማካኝነት በግብፅ፤ በህንድ ውቅያኖስ ሬዩንዮን እና ሞሪሺየስ ደሴቶች በአንድ ሄክታር ከፍተኛ ምርት የሚገኝበት በቆሎ በተለይ በአፍሪካ በከፍተኛ ደረጃ ተፈላጊነት ያለው የብርዕ ሰብል ነው። ይህን እንበል እንጂ፣ የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈቶ ኢስሞ (ዶ/ር) እንደተናገሩት በበቆሎ ምርምር ዘርፍ በአፍሪካ የመጀመሪያውን የተዳቀለ የበቆሎ ዝርያ ያስተዋወቀች ሀገር ኢትዮጵያ ነች። እኛም እንላለን፣ ልክ እንደዚሁ ሁሉ በበቆሎ ምርት የዓለምን (በተለይም ብዙ ፈላጊ ያለውን የአፍሪካ) ገበያ ሰብራ በመግባት የወጪ ንግድ (ለውጭ ገበያ የማቅረብ ሥራ) ላይ መሥራት አለባት። ለዚህ ደግሞ ወቅቱ ነውና ገበሬው በሚገባ ሊደገፍ ይገባል።

በግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You