የሴት ሥራ ፈጣሪዎችን አቅም ለማፈርጠም

ዜና ሐተታ

የሀገር ባህል ፋሽን ልብስ አምራቿ ማላዊቷ ኤሚ ሳካ፤ ኢትዮጵያን የማየት ዕድል ማግኘቷ እንደመልካም አጋጣሚ ታነሳለች፡፡ የሥራ ግንኙነት እና መልካም ጓደኝነትን ለመመሥረት ጠቃሚ መሆኑንም ነው የምትገልጸው፡፡

የሴት ነጋዴዎችን አቅም ማጠናከር እና እርስ በእርስ ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከርን ዓላማው አድርጎ በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው 6ኛው የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ሴት ሥራ ፈጣሪዎች የንግድ ትርዒትና ኮንፍረንስ ዛሬ ይጠናቀቃል።

‹‹ኮሜሳ ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ መሳተፌ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተወከሉ ሴት ነጋዴዎች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ለመመልከት አስችሎኛል›› ስትልም ትናገራለች፡፡

የንግድ ትርኢትና ባዛሩን ለመሳተፍ አዲስ አበባ የተገኘችው ኤሚ፤ ዝግጅቱ በኢትዮጵያ እውን እንዲሆን ያደረጉትን ሁሉ ለማመስገን እፈልጋለሁ፤ መድረኩ የሃሳብ ልውውጥ ለማድረግ አግዞኛል ስትል ትናገራለች፡፡

ኢትዮጵያንም ለመጎብኘት እድል ማግኘቷንም ትናገራለች፡፡ የሀገሯን ባህል ለማስተዋወቅ እንደቻለች፣ የሌሎች ሀገሮችን ባህልም ለመመልከት እድል እንደሰጣት እና በዋናነት ደግሞ የገበያ ትስስርን እንደፈጠረላትም ኤሚ ሳካ ትጠቁማለች፡፡

መርሃ ግብሩ ከ21 የኮሜሳ አባል ሀገራት የተውጣጡ ከሁለት መቶ በላይ ሴት ሥራ ፈጣሪዎችና ነጋዴዎች የተሳተፉበት ነው፡፡ የአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ውህደትን ለማፋጠን የሴቶችን ተሳትፎ የበለጠ ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑ ይታመናል፡፡ የተዘጋጀው ባዛርና ኮንፍረንስ ይህንኑ ዓላማ ለማሳካት የሚረዳ እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡

በ2013 ዓ.ም በተገኘ ብድር ሥራ የጀመሩት የኦቦሮ ቡና መሥራችና ባለቤት ጸሃይ ደመቀ፤ በ10 ሺህ ብር ካፒታል ቡና በመቁላት ፈጭቶ ለገበያ ማቅረብ ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙም ይጠቅሳሉ፡፡ ዘንድሮ ወደ ሙሉ ሥራ መሸጋገራቸውን እና ካፒታላቸውም ወደ 600 ሺህ ብር ማደግ መቻሉን ይናገራሉ፡፡

ቀደም ሲል ይሠሩት የነበረው ሥራ ሳይሳካ ሲቀር የቢዝነስ ሃሳብ ላይ ትኩረት ያደረገ ሥልጠና መውሰዳቸውን ምን ልሥራ የሚል ጥያቄ በማንሳት ሃሳብ ማመንጨት እንዳስቻላቸውም ነው የሚናገሩት፡፡ ሁሉም ሥራ ችግር አለው ነገር ግን በአቅሜ ልሠራው የምችለውን ሥራ መፈለግ ቀጠልኩኝ ነው ያሉት፡፡

ለመሥራት የተመቸኝ እና በፍቅር ልሠራው የምችለው ቡና መሆኑን ስላመንኩ ወደ ቡና ሥራ መሸጋገር ችያለሁ። የቡና ቅምሻ ሥልጠና በመውሰድ ከብድር ተቋም ብድር ወስደው ሥራውን መጀመራቸውንም ነው የጠቆሙት፡፡

ሥራ ለመጀመር አስቸጋሪ ከሚሆኑ ጉዳዮች መካከል የገበያ ትስስር እንደሚጠቀስ በመጠቆምም፤ እንደኮሜሳ አይነት የንግድ ትርኢትና ባዛር የገበያ ትስስር በመፍጠር ጠቃሚ መሆኑንም ያነሳሉ፡፡

በኢትዮጵያ የንግድ ሥራ ለመጀመር ቀላል አለመሆኑን የሚጠቁሙት ጸሃይ፤ ፍቃድ ለማውጣት፣ ድጋፍ ለማግኘትና የሚጠየቀውን ማስያዣ በማሟላት ብድር ለማግኘትም ከባድ ነው፣ ወለዱም ብዙ ጫና ይፈጥራል ሲሉ ነው የሚገልጹት፡፡

ኬላዎች የበዙበት በመሆኑም ዋጋው እንዲንር ምክንያት መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡ የቡና ገበያ ውድድር ከፍተኛ እንደመሆኑ፤ እንደጀማሪ ጥራት ያለው ምርት ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ የቡና ማሸጊያም በቀላሉ የማይገኝ ሌላ ወጪ የሚጠይቅ ነው ባይ ናቸው፡፡

የልምድ ልውውጥ ለማድረግ መድረኩ ጠቃሚ ቢሆንም፤ ያለሁበትን ደረጃ ለመለካት ተመሳሳይ ምርት ይዘው የገቡ የውጭ ነጋዴዎች አልገጠሙኝም ሲሉም ይገልጻሉ፡፡

የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር አባል በመሆኔ መረጃውን በቀላሉ ለማግኘት ችያለሁ፣ በባዛሩ ላይ ለመሳተፍም እድል አግኝቻለሁ ሲሉም ይናገራሉ፡፡

በኢትዮጵያ የንግድ ሥርዓቱ ቀለል እንዲል ቢደረግ መልካም ነው፣ ወደንግድ ሥርዓቱ ሳይገባ መቆየት ደግሞ ጊዜና ገንዘብ እንዲባክን ያደርጋል የሚሉት ጸሀይ፤ የመሥሪያ ቦታ ለማግኘትም ብዙ ጥረት እንደሚፈልግና አሠራሩን ምቹና ቀላል ማድረግ እንደሚገባም ይመክራሉ፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር አምባሳደር ሳልማ ማሊካ በበኩላቸው በአፍሪካውያን መካከል የሚደረገውን የንግድ ልውውጥ በማሳደግ የአህጉሪቱን የኢኮኖሚ ውህደት ማፋጠን ይገባል ባይ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያውያን ሴቶች በቀጣናው የሚያደርጉትን ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ እንዲሁም ተሳታፊነትን ለማሳደግ ትርጉም ያለው ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ይጠቁማሉ። የአፍሪካ ህብረት የሴቶችን እኩልነት ለማረጋገጥና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ የተለያዩ መርሃ ግብሮችን በመቅረጽ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛልም ነው የሚሉት፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚንስትር ዴኤታ ያስሚን ውሀብረቢ ሴቶችን በንግድ ሥራ፣ በፋይናንስ አቅርቦት፣ በትምህርት እና በገበያ እድል ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ከምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (COME­SA) ጋር ተቀራርቦ እየሠራ እንደሚገኝም ያመለክታሉ፡፡

መድረኩ በሴት ሥራ ፈጣሪዎች ለተመረቱ ምርቶች እና አገልግሎቶች የገበያ እድልና ትስስር ለመፍጠር እንዲሁም የወጪ ንግድን ለማስተዋወቅ እንደሚያስችልም ይጠቁማሉ።

የቀጣናውን እምቅ ሀብት እና የፈጠራ ውጤቶችን በማስተዋወቅም በቀጣናው ለሚገኙ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ሥራ ፈጣሪዎች በንግዱ ዓለም በሚያጋጥሟቸው ችግሮች እና መልካም እድሎች ዙሪያ እንዲመክሩና ልምድ እንዲለዋወጡ ጉልህ ሚና እንደሚጫወትም ነው የሚገልጹት።

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You