በፈተና ውስጥ የሚካሄደው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና

54ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ከትናንት በስቲያ ጀምሮ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ተጀምሯል። ቻምፒዮናው ገና ሳይጀመር ከቀናት በፊት ይካሄድ ወይስ ይቅር በሚል የፌዴሬሽኑን ሥራ አስፈፃሚዎች ጭምር ለሁለት ከፍሎ ሲያነጋግር ነበር። ለዚህም ዋነኛው ፈተና ቻምፒዮናው እጅግ በተጎዳው የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ መም ላይ መካሄዱ ሲሆን፣ መሙ በተለይም የመጀመሪያው የአትሌቶች መሮጫ መስመር ከጥቅም ውጪ መሆኑ ጥያቄ አስነስቷል። ይህም አትሌቶችን ለጉዳት ከማጋለጥ በተጨማሪ ቻምፒዮናው ደረጃውን የጠበቀ እንዳይሆን ያደርገዋል በሚል አስተያየት ከስፖርቱ ቤተሰብ ቅሬታ ሲቀርብ ቆይቷል።

በዚህም ቻምፒዮናው ቢሰረዝ ወይም የተሻለ መም ያለባቸው ከተሞች ላይ ይካሄድ የሚሉ ድምፆች ተበራክተዋል። ይሁን እንጂ ፌዴሬሽኑ በተያዘው እቅድ መሠረት በአካዳሚው እንዲካሄድ ወስኖ ባለፈው ማክሰኞ ተጀምሮ ዛሬ በተለያዩ ፉክክሮች ሦስተኛ ቀኑን ይዟል።

ከስፖርት ቤተሰቡ የተነሱ ምክንያታዊ ቅሬታዎች እንዳሉ ሆነው በፈተና ውስጥ የተጀመረው ቻምፒዮና ጅማሬ የተፈራውን ያህል ሳይሆን በውድድር ረገድ በጥሩ ፉክክር ደምቆ ታይቷል። በመጀመሪያው ቀን የተካሄደው የ 10ሺ ሜትር ድንቅ ፉክክርም ቻምፒዮናውን ይበልጥ ደማቅና የብዙዎችን ትኩረት የሳበ አድርጎታል።

በተለይ ለወርቅ በተፋለሙት አትሌት መቅደስ ሽመልስ እና በአትሌት ትዕግስት ደጀኔ መካከል የታየው ትንቅንቅ ተመልካቹን ቁጭ ብድግ ያደረገ ሲሆን፣ ድንቅ አትሌት መሆኗን በግሩም አጨራረሷ ያስመሰከረችው የአዳማዋ አትሌት ትዕግስት ደጀኔ 32:58:40 በሆነ ሠዓት በመግባት የውድድሩን የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳልያ አጥልቃለች። ውድድሩን 200 ሜትር እስኪቀረው ድረስ በርካታ ዙሮችን ስትመራ ቆይታ የተቀደመችው ሌላኛዋ ጠንካራና ተስፋ የተጣለባት የአማራ ክልል ተወካይዋ አትሌት መቅደስ ሽመልስ 33:06:07 በሆነ ሠዓት የብር ሜዳሊያውን ወስዳለች። የመቻል ክለብን የወከለችው አትሌት አያል ዳኛቸው 33:18:89 በሆነ ሠዓት የነሐስ ሜዳሊያው አሸናፊ ሆናለች።

ከዚህ ሌላ በሴቶችና በወንዶች የ100 ሜትር የፍፃሜ ውድድር ተካሂዶ በርካታ አትሌቶች ከመነሻ ችግር (ዲሲፒሊን)ጋር በተያያዘ ከውድድር ውጪ ሲሆኑ ቢታይም ለመሸናነፍ ጠንካራ ፉክክር አድርገዋል። በዚህም በ100 ሜትር ወንዶች ፍፃሜ ቢኒያም ፊሊጶስ 10:25 በማጠናቀቅ ከሲዳማ ቡና የወርቅ ሜዳሊያው አሸናፊ ሆኗል። ሲሳይ ተገኝ በ10:30 በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ የብርና አዳም ሙሳ በ10:45 ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የነሐስ አሸናፊዎች ናቸው። በተመሳሳይ በ100 ሜትር ሴቶች ፍፃሜ መሠረት ጉደራ በ11:48 ከሲዳማ ቡና ቀዳሚ ሆና ስታጠናቅቅ፣ ሰላማዊት ኮኮብ በ11:60 ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሁለተኛ፣ አርያት ዴቪድ በ12:05 ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሦስተኛ ሆነው አጠናቀዋል።

የቻምፒዮናውን መጀመር በይፋ ያበሠረው የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን ባደረገው ንግግር የአዲስ አበባ ስታዲየም ትራክን (መም) የማስተዳደር ኃላፊነት ለአትሌቲክስ ፌዴሬሽን እንዲሠጥ በይፋ ጥያቄውን አቅርቧል። አንጋፋው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ከ1963 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ እንደሚገኝ ያስታወሰው ስለሺ ስህን፣ ቻምፒዮናው ኢትዮጵያን በታላላቅ ዓለም አቀፍ መድረኮች ያስጠሩ በርካታ ከዋክብት አትሌቶች ተወዳድረው ያለፉበትና አሁንም ብዙዎች ሊሳተፉበት የሚጓጉለት እንደሆነ ተናግሯል።

የዘንድሮው ቻምፒዮና እየተካሄደበት የሚገኘው የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በርካታ ክፍተቶች እንዳሉትና ከፍተኛ የትራክ (መም) ችግር እንዳለ አፅኖት በመስጠትም “ትልቁና አንጋፋው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮናን በዚህ ደረጃውን ባልጠበቀና ባልተሟላ መልኩ ለማድረግ ተገደናል” ሲልም ፕሬዚዳንቱ ቻምፒዮናው የገጠመውን ፈተና ገልጿል።

አንጋፋውና ታሪካዊው ጀግና አትሌት አክሎም፣ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በቀጣይ በምንሳተፍባቸው ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ቻምፒዮናዎች ዝግጅት በጥገና ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባ ስታዲየም ትራክ በተቻለ ፍጥነት እንዲጠናቀቅና እንዲሁም የማዘውተሪያ ስፍራውን የማስተዳደር ኃላፊነት ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እንዲሠጥ ጥሪ አቅርቧል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 30 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You