
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ የንግድ ፖሊሲዎቿን ከቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የንግድ ሥርዓቶች ጋር በማጣጣም እያደረገቻቸው የሚገኙ ማሻሻያዎች ለኮሜሳ ነፃ የንግድ ቀጣና መጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ማሳያ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና በኮሜሳ ትብብር በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ ከተማ የተዘጋጀው 2ኛው የኮሜሳ ተቋማት የግንዛቤ ማስጨበጫ ፎረም ትናንት ሲካሄድ እንደገለጹት፤ ትብብሩ በኮሜሳ አባል ሀገራትና በአፍሪካ ደረጃ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት ለማረጋገጥ ያስችላል። ኢትዮጵያ የንግድ ፖሊሲዋን በማጣጣም በአህጉራዊ እና ዓለምአቀፋዊ የግብይት ሥርዓት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ለመሆን እየሠራች ትገኛለችም ብለዋል።
ፈጣንና ቀጣይነት ያለውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት ለማረጋገጥ፣ በቀጣናው የንግድና ኢኮኖሚ ትስስሮችን ለማጠናከር፣ የንግድ ግንኙነቶችን ማጎልበት እና የነጋዴ ሴቶችን አቅም ለመገንባት ትኩረት እንደሚደረግም አመልክተዋል።
በቀጣናው የነጋዴ ሴቶችንና ሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን አቅም መገንባት፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና መልካም እድሎችንና አማራጮችን ማስፋትና የሴት ነጋዴዎችና ሥራ ፈጣሪዎችን ለማብዛት ትኩረት እንደሚደረግም ነው የተናገሩት።
የንግድና ኢኮኖሚ ትስስሮችን በማጠናከርም የንግድ ግንኙነቶችን እያጎለበተ ዕውቀት፣ ልምድና ቴክኖሎጂ ሽግግር እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። አዳዲስ የቢዝነስ ዕይታዎችን በማበረታታት ቀጣይነት ያለው የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስርን ለማጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በአረንጎዴ ዐሻራ ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በስንዴ ምርታማነትና መሰል መርሃ ግብሮች የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን ሰፋፊ ሥራዎች መከናወናቸውን፣ በአዲስ አበባ በኮሪዶር ልማት የተከናወኑና በሂደት ላይ የሚገኙ የልማት ሥራዎችም ከተማዋን ሳቢና ማራኪ በማድረግ የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር ማስቻሉን ተናግረዋል።
የኮሜሳ ዋና ጸሃፊ ኩዋምፕዌ በበኩላቸው፤ ጥምረቱ ሴቶች በሥራ እድል ፈጠራ፣አካታች ኢኮኖሚ እድገትን በማሳደግ እና ድህነትን በመቅረፍ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማስፈን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሴቶች በሥራ ፈጠራ ተሳትፎ በማድረግና በገበያው ውስጥ በመሳተፍ ራሳቸውን እየጠቀሙና ለኢኮኖሚው ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረክቱ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ሥራ ፈጣሪ ሴቶች ሥራቸውን ለማስፋፋት በርካታ ተግዳሮቶች እንደሚገጥሟቸውና በሴቶች የሚተዳደሩ አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በንግድ እንቅስቃሴዎቻቸው አሸናፊ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው በቂ የንግድ እቅድ፣ ግብይት እና አስተዳደር ክህሎት እንዳልነበራቸውም ተናግረዋል።
የፋይናንስ አገልግሎት ለማግኘት አስፈላጊው ክህሎትና ግብአት ችግር እንደሚገጥማቸውም ጠቁመዋል። ጥምረቱ ሴቶች ብቁ እንዲሆኑ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
ሴት ሥራ ፈጣሪዎች መብቶቻቸውን እና እምቅ ችሎታቸውን ከተገነዘቡ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማስመዝገብ ከፍ ያለ አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ እንደሚችሉ እርግጠኞች ነን ። ለዚህም በትኩረት እንሠራለም ብለዋል
በሴቶች ሥራ ፈጣሪነት ዙሪያ ያለውን ድጋፍ ለማጠናከር እና ሥራ ፈጣሪነት እንቅፋቶችን ለመፍታት የተለያዩ መርሃ ግብሮች መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል።
የተሻለ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በመጠቆምም፤ ጥምረቱ ዕቃዎቻቸውን እና አገልግሎቶቻቸውን ለገበያ እንዲያቀርቡ፣ ጠቃሚ መረጃ እንዲያገኙ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግም ተናግረዋል። በቀጣይነትም 6ኛው የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ነጋዴ ሴቶች ፌዴሬሽን የኮሜሳ ንግድ ትርዒትና ቢዝነስ ኮንፍረንስ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 29 ቀን 2017 ዓ.ም