የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ የስትራቴጂክ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥን የመጀመሪያ የሆነውን ጆርናል መጋቢት ሁለት ቀን ማስመረቁ ይታወሳል። በምርቃት መርሃ ግብሩ ላይ አንጋፋ ዲፕሎማቶችና የዘርፉ ምሁራን ተገኝተዋል። ጆርናሉ ወደፊት በተከታታይነት የሚዘጋጅ ሲሆን የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የዲፕሎማሲ ታሪክ ላይ ጥናት በማካሄድ የዓለም ማኅበረሰብ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያደርጋል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የተቋቋመው የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነትና በተለይም ስትራቴጂክ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ነው። ኢንስቲትዩቱ በውጭ ግንኙነት ረገድ ልህቀትን የማንጣት ተልዕኮ ተሰጥቶት በ2014 ዓ.ም የፌዴራል ተቋማት እንደ አዲስ ሲደራጁ የተቋቋመ ሲሆን ለዘርፉ ባለሙያዎች ሥልጠና በመስጠትና ጥናት በማካሄድ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል።
በጆርናል ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚ ስትራቴጂ እና በአህጉራዊ ተፅእኖ ላይ የሚኖራትን ሚና የሚያጎሉ ጥናቶች ተካተውበታል። ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ከበርካታ ሀገራት ጋር ዲፕማሲያዊ ግንኙነት እንዳላት፣ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲን በማከናወን ብሔራዊ ጥቅሟን በዓለም ደረጃ የማስከበር ሥራ በስፋት ስለመሥራቷ ይገልጻል። እንዲሁም የዓለም የጥቁር ሕዝቦች በባርነት በነበሩበት ጊዜ ነፃ እንዲሆኑ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ስለመታገሏ ያብራራል። አሁን ባለንበት ዘመንም የአፍሪካን ጉዳዮች አጀንዳ በማድረግ አፍሪካውያን ጥቅሞቻቸው እንዲከበሩ እየሠራች ነው። ይሁንና ከጥንት ጀምሮ ለአፍሪካና ለዓለም ያላትን አበርክቶ በጥናትና ምርምር ማሳወቅና ማስገንዘብ ላይ ክፍተቶች እንዳሉ ይጠቁማል።
አሁን ያለንበት ዘመን እየተቀያየረ መሆኑን የሚያነሳው ጆርናሉ፤ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ፈጣንና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ሊደገፍ ይገባል ይላል። በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዲመጣ ኢትዮጵያ የምትጫወተውን ሚና በዘርፉ ያሉ ምሁራን ምርምሮችን በማካሄድ ማጉላት ይኖርባቸዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑና ጠንካራ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ያላቸው ሀገራት መነሻቸው ጥናትና ምርምር ነው። ተደማጭና ተጽዕኖ ፈጣሪ በመሆን ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ የሚቻለው ኢትዮጵያ ለአፍሪካና ለዓለም ያደረገችውን የሰላም አስተዋጽኦ ማስገንዘብ ሲቻል ብቻ ነው። እንዲሁም ኢትዮጵያ ለጋራ ተጠቃሚነት ቅድሚያ የሚሰጥ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እንዳላት ማሳወቅና የተፈጥሮ ሀብቶቿን ለጋራ ጥቅም ማዋሏን መግለጽ ሲቻል መሆኑን ይገልጻል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ እንደገለጹት፤ ጆርናሉ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂካዊ እና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የሚቀርብበት ነው። ጆርናሉ የመጀመሪያ መሆኑንና በቀጣይ ምሁራን ጥናታቸውን የሚያቀርቡበት እንደሚሆንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር የወንድማማች ግንኙነት ቅድሚያ የሚሰጥ ነው። እንዲሁም ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገሮች ቅድሚያ የሚሰጥ የውጭ ፖሊሲ እንደምትከተል በተጨባጭ ማስረጃዎች አስደግፎ ለዓለም ማሳወቅ ተገቢ ነው። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የልማት እና የደህንነት ድርጅቶች ጋር ጠንካራና የቆየ ትብብር አላት።
አቶ ጃፋር እንደሚሉት፤ ኢንስቲትዩቱ ባለፉት አራት ዓመታት ከጥናትና ምርምሮች በተጨማሪ ውይይቶችን በማዘጋጀት፣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ለባለድርሻ አካላት ሥልጠናዎችን በመስጠት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲንና የውጭ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርስ የራሱን አበርክቶ እያደረገ ይገኛል። ጆርናሉን ለማዘጋት ሶስት ዓመታት የፈጀ ሲሆን በርካታ ልምድ ያላቸው ምሁራን ተሳትፈዋል፤ ወደፊትም የኢትዮጵያን አጀንዳ መቅረጽ የሚችል እንዲሆን ለማድረግ ይሠራል።
የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲና ዲፕሎማሲ በጥናትና ምርምር ላይ የተመረኮዘ መሆን አለበት የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ መታተም የጀመረው ጆርናል የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የሚያቀርብ በመሆኑ ጠቀሜታው ጉልህ ነው። እንዲሁም ኢትዮጵያ ዓለም ላይ ያላትን የዲፕሎማሲያዊ ትርክት መልካም እንዲሆን የሚያደርግበት ይሆናል።
በቀጣይ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅና በዓለም መድረክ ተደማጭነትን ከፍ ለማድረግ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ዙሪያዎች ጥልቅ እውቀት ያላቸው ምሁራን ጥናታቸውን የሚያቀርቡበት ጆርናል ይሆናል። እንዲሁም ኢትዮጵያ ለቀጣናው መጠናከር ያላትን አበርክቶ በግልጽ ለማስረጽ ይጠቅማል። የአፍሪካ ሀገራትና አውሮፓውያን ስለ ቀጣናው የበለጠ መረጃ እንዲኖራቸው በማድረግ ቀጣናው ከግጭት የጸዳ ለማድረግ ያስችላል።
የኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ወንድማማችነትን በማጠናከር፣ ለጋራ ዓላማ በጋራ መቆምና በአፍሪካ አንድነት ጉዳዮች ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያስገነዝባል። በውጭ ግንኙነት ረገድ የተቀናጀና ተከታታይነት ያለው ጥናትና ምርምር በማካሄድ የምትከተለውን ፖሊሲ ማስተዋወቅ ተገቢ ነው፤ እንዲሁም ለገጽታ ግንባታ ማዋል እንደሚገባ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ዘላቂ የምትላቸውን የውጭ ግንኙነት ጥቅሞችን ለማስከበርና ለማስጠበቅ በሳይንሳዊ መንገድ ትርክት መቅረጽ አለበት። በሳይንሳዊ መንገድ የተደረገ ጥናት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ይኖረዋል። እንዲሁም ተወዳዳሪ ሀገር ለመፍጠር ያግዛል። አጥኚዎች በሚያጠኗቸው ጥናቶች የኢትዮጵያን ትርክት የሚሳድጉና ለዓለም የሚያስተዋውቁ መሆን መቻል አለባቸው።
ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም፣ ለአፍሪካ አንድነትና ለጥቁር ሕዝቦች ነፃነት ያደረገችውን አስተዋጽኦና ተፈጥሯዊ ሀብቶችን በፍትሐዊነት ለመጠቀም ያስቀመጠችውን መርህ በጥናት በማረጋገጥ በውጭ ግንኙነት ዙሪያ ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ እንዲኖረው ማድረግ ይገባል። በዚህ ረገድ የተሠሩ ጥናትና ምርምሮች የሚታተሙበት ወጥ የሆነ መንገድ አልነበረም፤ አሁን ላይ በኢንስቲትዩቱ መታተም የጀመረው ጆርናል የኢትዮጵያን ትርክት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደማጭና ተደራሽ እንዲሆን ያስችላል።
የውጭ ግንኙነት ፖሊሲን በማስረዳት ከሀገራ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር በሚደረገው ሂደት ውስጥ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት አስተዋጽኦ ትልቅ መሆኑን የሚያነሱት ዳይሬክተሩ፤ በዋናነት በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ዙሪያ ጥናትና ምርምሮችን ያካሂዳል። የውጭ ግንኙነት አሠራሮች በጥናት የተደገፉ በማድረግ ውጤታማ ሥራዎች እንዲሠሩ ያስችላል። ጥናትና ምርምር ላይ ተመርኩዞ የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀት፣ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ዙሪያ ውይይት በማድረግ የዘርፉ ምሁራን ዘርፉን መምራት የሚያስችላቸውን የፖሊሲ አጀንዳ አቋም እንዲይዙ የሚያደርግ ነው።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ኢትዮጵያ ስብስብ ውስጥ እንዴት ጥቅሟን ማስጠበቅ ትችላለች የሚለውን፣ ኢትዮ- ሶማሊያ ከነበሩበት ችግር ወጥተው ወደ አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ እንዲገቡ ከማድረግ አኳያና በቀይ ባሕር ዙሪያ ልትከተለው የሚገባውን ፖሊሲ የማመላከት ጥናቶችን በማካሄድ ብሔራዊ ጥቅም እንዲጠበቅ ይሠራል። እንዲሁም የውጭ ግንኙነት ውሳኔ ሰጭ አካላትን የማማከርና በጋራ ከመሥራት አንጻር ትልቅ ሀገራዊ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት በርካታ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በማካሄድ የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በሚገባ የማስተዋወቅ ብሔራዊ ጥቅሟን የማስጠበቅ ሥራ እየሠራ ነው። ወደፊትም መሰል ሥራዎችን አጠናክሮ ይቀጥላል። በተካሄዱ ጉባኤዎች የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት ትርክቶች፣ ፍላጎቶችና የረጅም ጊዜ ግቦች ላይ የተሻለ መረዳትን መፍጠር የሚያስችሉ ሥራዎችን መሥራት ተችሏል። ከሚከናወኑ ጉባኤውን በተጨማሪ በምሁራን በሚካሄዱ ጥናቶች የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት አጀንዳዎችን ለዓለም እንዲተዋወቁ ለማድረግ ተችሏል። የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት የማስተዋወቅ አካል የሆነው ጆርናሉ የውጭ ተመራማሪዎችና አጥኚዎች የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዎችንና ትርክቶችን በሚገባ እንዲረዱ ከማድረግ አንጻር የሚኖረው አስተዋጽኦ ትልቅ ነው።
በዓባይ ግድብ ዙሪያ ሳይንሳዊ የሆኑ ጥናቶችን በማድረግ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እውነታውን ለማሳወቅ የሚረዳ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ያስፈልጋል። ግብጾች በዓባይ ወንዝ ላይ የተሳሳቱ ጥናቶችን በማድረግ የኢትዮጵያን ትርክት ወደ ኋላ ያስቀሩበት ሂደት አለ። ይሁንና በቅርቡ ከኢትዮጵያ በኩል በሚወጡ ጥናቶች የዓለም ማኅበረሰብ እውነታውን እያወቀው መጥቷል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አብዲ ዘነበ (ዶ/ር) እንደሚያስረዱት፤ ተደራዳሪና ተፎካካሪ ሀገር ለመፍጠር ጥናቶች ያስፈልጋሉ። የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲን በጥናት መለየትና ማሳወቅ ይጠበቃል። ይህን ከማድረግ አኳያ ኢንስቲትዩቱ ብዙ ሥራዎችን እየሠራ ነው፤ በቀጣይነት በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲና ዲፕሎማሲ ዙሪያ የሚታተም ጆርናል አዘጋጅቷል። ይህ ዓለም አቀፍ ምሁራንና ተመራማሪዎች ስለ ኢትዮጵያ እውነተኛ መረጃዎች እንዲኖራቸው ያስችላል። ያለንበት ዓለም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እየተቀያየረ በመሆኑ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመውጣት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በጥናትና ምርምር መደገፍ ይኖርበታል። በውጭ ግንኙነት ዙሪያ የሚሠሩ ጥናትና ምርምሮች ለአጥኚዎች የሚደርሱበት ሁኔታ መመቻቸቱን ጠቁመዋል።
ዘመኑ እጅግ ውስብስብ ከመሆኑ የተነሳ እንዴት የሀገርን ጥቅም በዘላቂነት ማስጠበቅ ይቻላል የሚለውን ለመመለስ ጥናት አስፈላጊ ነው። እንዲሁም ለፖሊሲ አውጭዎች የሚሆን ጥናትና ምርምር ለማድረግ ተገቢ ነው። እንደ ሀገር የነበሩ እውነታዎችን በመግለጽ ለዲፕሎማሲያዊ ጥቅም ማዋል እንደሚገባ ገልጸዋል።
ከዓለም መለዋወጥ በተጨማሪ ኢትዮጵያም እየተለወጠች ነው የሚሉ አብዲ (ዶ/ር)፤ በሁሉም ዘርፍ ለውጦች ይስተዋላሉ። ከውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በተጨማሪ ከሁሉም አቅጣጫ የሚመጡ ጫናዎች ለመቋቋምና የኢትዮጵያን እውነታዎች ለማስረዳት ጥናትና ምርምር ማድረግ ጊዜው የሚፈልገው መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ዓይነተኛ መንገድ ነው፤ አሁን ካለንበት ጊዜ አንጻር ሀገር በመከላከያ ሠራዊት ብቻ ሳይሆን በዲፕሎማሲና በውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ልትጠበቅ ይገባል። የተጠናከረ የውጭ ፖሊሲና ዲፕሎማሲ ያለው ሀገር ተደራድሮ ጥቅሙን የማስጠበቅ አቅም ይኖረዋል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የሚያከና ውናቸው ጥናትና ምርምር ሀገርን የመገንባትና አቅም የመፍጠር ሂደት ነው የሚሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር ጥያቄያችን ማስመለስ ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግ ቀደምት እውነታዎችን ለዓለም ማኅበረሰብ በጥናትና ምርምር የተደገፈ መረጃን መስጠት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ተደርጎ ሊታይ ይገባል።
ጥናቶች የወደፊት ክስተትን አመላካች በመሆናቸው ለጥናትና ምርምር ትኩረት መስጠት እንደሚገባ የገለጹት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ በውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ረገድ ተጽዕኖ ፈጣሪ ለመሆን ያስችላል። ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ መከራከሪያ ነጥብ የጥናት ውጤት መሆኑን በመገንዘብ እንደ ሀገር በጥናትና ምርምር የተደገፈ አካሄድ መከተል እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 28 ቀን 2017 ዓ.ም