
ዛሬ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ጉዳይ ከቀናቶች በፊት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራውን መጀመሩን ተከትሎ ከተላለፉት መልእክቶች መካከል ይህኛው ቀልቤን ስለገዛው ነው። በአርግጥ በሀገራችን ኢትዮጵያ የወጣቶች ሞትና የእናቶች ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የወላጆች እንባ መፍሰስ ከጀመረ የቅርቡን ብናነሳ እንኳን ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ አስቆጥሯል። በእነዚህ ጊዜያት በዋናነት ከምናነሳቸው መካከል የ1960 ዎቹ ማጠናቀቂያ ቀይ እና ነጭ ሽብር ቀዳሚ ተደርጎ ይወሰዳል።
በዘመነ ደርግ በተካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት ከሁለቱም ወገን የረገፉት ወጣቶች ቁጥርና በቅርቡ የተከሰተውን ለውጥ ተከትሎ በዋናነት የሰሜኑ ጦርነትና ዛሬም ድረስ በአንዳንድ አካባቢዎች ብልጭ ድርግም የሚሉት ግጭቶችም የቅርብ ጊዜ ሳይሆን የአሁን ትዝታዎቻችን ናቸው። እነዚህን ያነሳሁት እርስ በእርስ የተላለቅንባቸው እርስ በእርስ የተደማማንባቸውና የቆሰልንባቸው ራሳችንን የሚያሙን፤ ራሳችን የፈጠርናቸው፤ የራሳችን ቁስሎች በመሆናቸው ነው።
እንደ ሀገር ከዘመን ዘመን አሸጋግረን ዛሬ ላይ ያደረስናቸው እነዚህን ግጭቶች ብቻ ሳይሆን ለግጭቶቹ መነሻ የሚሆኑ ቁርሾና ጥላቻዎችንም ነው። በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ዛሬ ለሚሞተው ወገናችን ዛሬ ለሚፈሰው የወገናችን ደም እና እንባ በየደረጃው ጥንስሱ ትናንት የጀመረ ነው። ከዚህ የመገዳደል የመገፋፋትና የመጠላላት አዙሪት ልንወጣ ያልቻልነው ችግሩ ትናንት የተፈጠረ ስለነበር ሳይሆን በቀና ልቦና በሰጥቶ መቀበል መንፈስ ፊት ለፊት ቁጭ ብለን መምከር ባለመቻላችን ነው።
ዛሬም ድረስ ያለ ውጪ ሸምጋይ እንዳንመካከር የሚይዘን ደግሞ በእኔ እይታ በአንድ ወገን ለዘመናት እያዳበርነው የመጣነው ያለመተማመን መንፈስ ሲሆን፤ በሌላ በኩል የእብሪትና የተሸናፊነት ስሜት ነው። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ባህሩን ተሻግረን ለምክክር ራሳችንን ዝግጁ ካላደረግን ሀገራችን ከችግሩ ጋር የመቆየቷ ጉዳይ አይቀሬ ይሆናል። ችግሩ ደግሞ መፍትሄ ሳያገኝ ውሎ ባደረ ቁጥር ከማመርቀዝ ባለፈ ሁላችንንም የሚበክለን መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው።
በአሁኑ ወቅት የአማራ ብሄራዊ ክልል የሰላም እጦት በስፋት ከሚስተዋልባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች አንዱ ነው። ምን አልባትም ያለፈውን አንድ ዓመትና ከዛ በላይ አካባቢው ሙሉ ለሙሉ ሰላም ውሎ ያደረበት ጊዜ ጥቂት ይመስለኛል። ችግሩ ደግሞ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት ከመቅጠፍ አካል ጉዳት ከማድረስና ንብረት ከማውደም ባለፈ አርሶ አደሩን የልፋቱን ፍሬ እንዳይበላ እያደረገው ይገኛል።
ከሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ወይንም ሁለቱንም ሟችንና ገዳይን እድል አግኝቶ ይህን የምታደርጉት ለምንድን ነው? ብሎ የሚጠይቅ ቢኖር ምላሻቸው ለሕዝባችን የሚል እንደሚሆን ግልጽ ነው። ታዲያ እንዴት ነው አንድን የሚወዱትን…. የእኔ የሚሉትን… ሕዝብ ለመታደግ እርስ በእርስ መገዳደል መፍትሄ የሚሆነው?።
በታሪካችን የገጠሙንን የእርስ በእርስ ችግሮች ስንፈታ የኖርነው እንደ ስፖርት ግጥሚያ አንዱ ተሸናፊ አንዱ አሸናፊ በሚባልበት የሀሰት መደምደሚያ ነው። የሀሰት መደምደሚያ ያልኩት ተሸናፊና አሸናፊ አልነበረም ለማለት ሳይሆን ወንድም ወንድሙን ገሎ የገዛ እናቱን እያስለቀሰ የሚገኝ ድል ለእኔ ውርደት እንጂ አሸናፊነት ባለመሆኑ ነው።
በመሠረቱ በጋራ ልንዘምትበት የሚገባ የሁላችንም ጠላት የሆነ ድህነት የሚባል ችግር እንዳለብን ቀድመን መገንዘብ በተገባን ነበር። ይህም ሆኖ እስከሚበቃን ከተጎዳዳንና ከተገዳደልን በኋላ ራሳቸው የግጭት ሴራ የጠነሰሱልን፤ መሣሪያ እና ቀለብ የሰፈሩልን አሸማጋይ ሆነው ሲያስታርቁን ቆይተዋል።
የግጭትና የመጠፋፋት የታሪክ ምዕራፋችንን መዝጋት ባንችልም ቢያንስ የራሳችንን ጉዳይ በራሳችን አቅም በመፍታት ረገድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ግን ተስፋ አስጭረውናል። ለዚህ ደግሞ ለሰሜኑ ችግር መፍትሄ በፕሪቶሪያ የተደረገው ስምምነት አንዱ ሲሆን ነገን በተስፋ እንድንጠብቅ የሚያደርገን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንቅስቃሴ ደግሞ ሌላው ነው። የኮሚሽኑ ይዞት የመጣውን እድል በአግባቡ ከተጠቀምንበት በጋራ እንድናተርፍ የሚያስችለን ይሆናል የሚል ጽኑ አምነት አለኝ።
እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የኮሚሽኑን ሥራ ተስፋ እንድጥል የሚያደርገኝ እየሄደበት ያለው መንገድ ነው። ከዚህ ውስጥ መንግሥትን በመቃወም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ጥያቄያቸውን በአጀንዳነት ለማስያዝ ይችላሉ። የሚለው ነው።
ይሄ ማለት በአሁ ወቅት መሣሪያ አንስተው የትጥቅ ትግል እያደረጉ ያሉ አካላትም የታጠቁትን መሣሪያ ሳይሆን ሃሳባቸውን ለኮሚሽኑ ሊያስረክቡ የሚችሉበት ሰፊ እድል አለ። ይህንን በማድረጋቸው ደግሞ ብዙ የሚያተርፉት ነገር እንደሚኖር መገመት የሚከብድ አይደለም ። የእኛና የምንታገልለት ሕዝባችን ያልተመለሰ፤ እኛንም ለሃይል እንቅስቃሴ የዳረገን ችግር ይሄ ነው በማለታቸው የሚያጡት ነገር አለ ብዬ አልገምትም።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉት አካላት ሃሳብ ፍላጎትና እንቅስቃሴ በዛው ባሉበት ቦታ ብቻ የተቀነበበ እንዳልሆነም እገነዘባለሁ። ይህ ማለት ደግሞ እነሱን የሚደግፉ ሃሳባችሁ ሃሳባችን ነው የሚሉ ሌሎች አካላት በሀገር ውስጥና በውጪ ይኖራሉ። የዚህ ጽሁፌ መልእክትም ለእነዚህ አካላት ነው።
ይህ ብዙ ሊተረፍበት የሚችል ግን ደግሞ ምንም ጉዳት የሌለው እድል ሊያልፈን አይገባም። እነሱን በርቱ ግፉበት ከማለት ተቆጥባችሁ በእነሱም በኩል ሆነ ራሳችሁ ሃሳባችሁን ለኮሚሽኑና ለኢትዮጵያ ሕዝብ አድርሱ ። ያኔ ለችግር የሚዳረገው ሕዝብ እረፍትም ሰላምም ያገኛል። ቸር እንሰንብት።
ተስፋይ መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28 ቀን 2017 ዓ.ም