ለለውጥ እየተጉ ያሉ-ባለብሩህ አዕምሮዎች

ምዕራብ ሐረረጌ ዞን፣ ገለምሶ ከተማ፣ ዳዲ ገላን መንደር ነዋሪ የሆነው ወጣት ሀምቢሳ በሺ መሐመድ ከመኪናው ደገፍ ብሎ ቆሟል፤ የተደገፋት መኪና ቁርጥ ዘመናዊዋን ቴስላ ትመስላለች። የእጆቹ ሥራ ናት። ገና የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፤ ከዋናው ትምህርቱ ባሻገር በገለምሶ ከተማ በሚገኘው ፖሊ ቴክኒክ ውስጥ መለስ ቀለስ እያለ ቴስላ መሳይ መኪና መሥራቱን አጫውቶናል።

ወጣቱን ያገኘነው ዘንድሮ ለስድስተኛ ጊዜ ከሚያዚያ 19 እስከ 23 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በኦሮሚያ ክልል በአዳማ ከተማ “ብሩህ አዕምሮዎች፤ በክህሎት የበቁ ዜጎች” በሚል መሪ ሃሳብ ሲካሔድ የነበረው መርሃ ግብር በፓናል ውይይትና በእውቅና አሰጣጥ ሥርዓት በተጠናቀቀበት ወቅት ነው። እርሱ እንዳለን፤ ወደ አዳማ ከተማ ይዞ የተገኘው ቴስላ ሳይበር ትራክ መኪና የምትመስለውን ሠርቶ ነው።

ቴስላ መሳይዋ መኪና ላይ “ገለምሶ ሲቲ” የሚል ጽሑፍ ይታያል። መኪናዋን ለመሥራት የተጠቀመው እቃ እዚሁ ሀገር ውስጥ ያለውን ሲሆን፤ ከባጃጅ፣ ከሞተር እና መሰል ብረታ ብረት ላይ ያገኘውን ነው። ይህን ለመሥራት ያነሳሳው ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘትም ጭምር ነው ይላል።

ወጣቱ ሀምቢሳ፣ መኪናዋ የፈጀችበት ወጪ 290 ሺህ ብር ሲሆን፤ ብትሸጥ ደግሞ እስከ 600 ሺህ ብር ድረስ ያወጣል ሲል ይናገራል። ከአሽከርካሪው ውጪ አምስት ሰው እና ተጨማሪ አምስት ኩንታል የመያዝ አቅም እንዳላትም ነው ያስረዳን።ለጊዜው የምትጠቀመው ነዳጅ ሲሆን፤ እቃዎች ሲመቻቹልኝ ግን ወደ ኤሌክትሪክ እመልሳታለሁ ብሏል።

መኪናዋ በሰዓት ከ70 ኪሎ ሜትር እስከ 80 ድረስ የምትጓዝ መሆኗንም ጠቅሶ፤ የባለቤትነት ይሁንታው ግን ገና በሂደት ላይ እንዳለ አውግቶናል። በቀጣይ ከአነስተኛ እስከ ትልልቅ ተሽከርካሪዎች መሥራትና በሀገር ውስጥ ያለውን ችግር መቀነስ ሲሆን፤ በሒደት ደግሞ ከጎረቤት ሀገር እስከ ሌሎች ሀገራት ድረስ ኤክስፖርት የማድረግ ሕልም አለኝ ብሏል።

ሌላው ወጣት ተስፋሁን ጣሰው፣ የመጣው ከኢሉባቦር ነው። አናቢ እና አርሶ አደር ነው። ብዙ ጊዜ አናቢዎች የሚሠሩት ማር እና ሰም ላይ ትኩረት በማድረግ ነው ይላል። እኛ ግን ከ210 በላይ የንብ ቀፎ በማዘጋጀት ከማር እና ከሰም ውጪ ሌላ ከንብ የሚገኘውን ምርት በማምረት ወደ ውጪ ለመላክ እቅድ አለን ሲልም ይናገራል። ይኸውም ምርት የንብ አበባ ዱቄት በመባል የሚታወቅ ነው ያለው ወጣቱ፤ በ2018 በጀት ዓመት የንብ አበባ ዱቄት ወደ ውጭ ለመላክ እቅዱን ይዘናል ይላል። የንብ አበባ ዱቄት በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋጋው ውድ ነው፤ አንድ ኪሎ የሚሸጠው አስር ሺህ ብር ድረስ ነው። ከአንድ ቀፎ እንደየአካባቢው ሁኔታ አበባ የሚያብብበት ጊዜ መሆኑ ከተጤነ እስከ 150 ግራም መሰብሰብ እንችላለን ሲል ይገልጻል።

እርሱ እንዳለን፤ ለምሳሌ ቢያንስ አንድ አርሶ አደር በጓሮው አምስት ቀፎ ቢኖረው በቀን በጣም ብዙ ብር ማግኘት ይችላል። የንብ አበባ ዱቄት ሲባል ንቢቱ ወደ ቀፎዋ ከመግባቷ በፊት በእግሯ ይዛ የምትመጣው የአበባ ዱቄት ነው። ይህ ዱቄት ደግሞ የተሟላ ምግብ በመባል የሚታወቅ ነው። ለምሳሌ የእድሜ መቀንጨር ያጋጠማቸው ሕጻናት ሊጠቀሙበት የሚያስችል ነው። አርሶ አደሩ እራሱ ዱቄቱን ከሰላጣ እንዲሁም ከእርጎ ጋር አድርጎ ቢበላው ጥሩ የሆነ የምግብ ይዘት ያለው ነው። ይህ በእኛ ሀገር የተለመደ አይደለም ያለው ወጣቱ፤ እኛ ግን አሁን እየሠራንበት ነው ሲል ያስረዳል።

በዕለቱ የፓናል ውይይቱ በተጠናቀቀበት ወቅት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ እንዳሉት፤ እንደ ሀገር ከድህነት ለመውጣት የሚያግዘው ነገር ቢኖር የፈጠራ ሥራ፣ ክህሎት እና ቴክኖሎጂ በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው። ስለዚህ በተለይ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶች ዘርፉን መቀላቀል አለባቸው። እነርሱ ዘርፉን በተቀላቀሉ ቁጥር ሀገር የምትፈልገውን ዓይነት ፈጠራ ማግኘት ይቻላታል። ይህ በመሆኑም ክህሎቱ እና እውቀቱ ያላቸውን የፈጠራ ችሎታ ባለቤቶችን የተሻለ ሥራ ይሠሩ ዘንድ ማበረታታት ያስፈልጋል ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል በክህሎት፣ በቴክኖሎጂ እና በፈጠራ ብቁ የሆነ እና በመስኩ መወዳደር የሚችል ዜጋ በማፍራቱ በኩል የበኩሉን ሚና እየተጫወተ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ የሥራ እድል ፈጠራ እና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ኤባ ገርባ፤ በዘርፉ የተሰማሩ ኮሌጆች ብቁ የሆነ ዜጋ በማፍራቱ በኩል የላቀ ሚናቸውን መጫወት ይጠበቅባቸዋል። በቴክኖሎጂና በፈጠራ ብቁ እንዲሆኑም ጭምር መትጋት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በዕለቱ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩ፣ በትራንስፖርቱ ዘርፍ የሚታየውን ችግር የሚቀርፉ እንዲሁም ከግብርና ጋር ተያይዞ ጊዜ እና ጉልበትን የሚያሳርፉ መሳሪያዎች ለእይታ የቀረቡ ሲሆን፤ በጥቅሉ ወደ 22 ክላስተሮች በውድድሩ የተሳተፉ መሆናቸው ታውቋል። ተወዳድረው ያሸነፉ የተሸለሙ ሲሆን፤ እነርሱም ዋንጫ፣ የምስክር ወረቀት እና ሜዳሊያ አግኝተዋል። እንደ አጠቃላይ 22 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ አንደኛ ሆኖ ያሸነፈው የአዳማ ክላስተር ሲሆን፣ ሁለተኛ የወጣው ደግሞ የሰበታ ክላስተር እንዲሁም ሶስተኛ የወጣው አትሌት ቀነኒሳ ክላስተር መሆኑ ታውቋል።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 26 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You