
ሴቶች ወደ ላይ ለእናቶቻቸው፣ ለአባቶቻቸው፣ ለአያቶቻቸውና በእድሜ ለሚበልጧቸው የማህበረሰብ አካላት፣ ወደጎን ለሕይወት አጋሮቻቸውና በዙሪያቸው ላሉ፣ ወደታች ለልጆቻቸው፣ ለልጅ ልጆቻቸው፣ ለታናናሾቻቸውና ለአካባቢ ማህበረሰብ ሁሉ አጋዦች፣ ተንከባካቢዎች፣ ጠባቂዎች፣ አስተማሪዎች ፣ አማካሪዎች፣ የልማት አጋሮች ፣ ችግር ፈቺዎችና የሰላም እርግቦች ናቸ ው።
ሁሉንም ያካትታል ባይባልም አብዛኛዎቹ ሴቶች የሚጋሩትና በተፈጥሮ የተሰጣቸው ወይም ከአካባቢያቸው የሚያዳብሩት ልዩ ባሕሪያት አሏቸው። በቤት ውስጥ እንደ እማወራ አቅደው፤ በጀት በጅተው እንደየ አቅማቸው ያላቸውን አብቃቅተው ቤታቸውን ይመራሉ።
ቤተሰባቸውን የመንከባከብ የመምራትና የመግራት፣ ባህልን፣ እሴትን ቱፊትንና መልካም ሥነ-ምግባርን ለልጆቻቸው በማስተማር ብቁ ዜጋ የመፍጠር ኃላፊነቶችንና መሰል ተግባራትን መሸከም የሚያስችል ትእግስት፣ ጥንካሬና ራሳቸውን የመስጠት አቅም አላቸው። በእዚሁ ላይ በአደባባይም ሆነ በሙያዊ ሥራ ላይ የተሰጣቸውን ተግባርና ኃላፊነት በታማኝነት ፣ በጥራትና በፍጥነት የመከወን ችሎታም ባለቤት ናቸው።
በዙሪያቸው የሚኖሩ የማህበረሰብ አካላት በመከባበር፣ በፍቅር፣ በመተሳሰብ፣ በመደጋገፍና በአብሮነት ስሜት የተሳሰረ ግንኙነት እንዲኖራቸው ጥሩ የግንኙነት መረቦችን የመዘርጋት ችሎታ አላቸው። በቤተሰብ ፣ በሥራ ቦታ፣ በማህበራዊ ቡድኖች ውስጥ ስምምነትን የመፍጠር፣ ግንኙነትን የማጠናከርና ትብብርን የማሳደግ ችሎታ ያላቸው የግንኙነትና የአብሮነት አሳላጮች ናቸው።
ቤተሰብንና ማህበረሰብን በአዎንታዊ መንገድ መገንባት፤ ሥራን መምራትና ማነቃቃት የሚችሉ፤ በርካታ ተግባራትን በጥራትና በፍጥነት መከወን ይችላሉ። ትልልቅ ኃላፊነቶችን በሚዛናዊነትና በብልሃት የሚወጡ፤ በግል ሕይወትም ሆነ በሙያዊ ሥራዎች የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን እንደ አመጣጣቸው በትእግስት መፍታት የሚችሉ፤ ታማኞች፤ ጥሩ አድማጮች፤ አማካሪዎችና ደጋፊዎችም ናቸው።
ነገሮችን በቀላሉ መረዳት የሚያስችል የግንዛቤ ችሎታ ስላላቸው ግንኙነቶችን፤ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችንና የተወሳሰቡ ስሜቶችን በመገምገም ጥሩ ውሳኔ መስጠት ይችላሉ። ጥበብን በተላበሰ አገላለጽ ችግሮችን የሚፈቱበትና ለእለት ተእለት የኑሮ ፈተናዎች አዳዲሰ መፍትሔዎችን መስጠት የሚችሉበት የፈጠራ አቅም ባለቤቶችም ናቸው።
ደህንነትና ሰላም አብዝተው የሚጨነቁና ለመርዳት የሚታትሩ ሩህሩሆችም ናቸው። ለሴቶች ያሏቸውን እነዚህን እምቅ ችሎታና ልዩ ባህሪያት ትኩረት ሰጥቶ በትምህርት ፣ በሥልጠና ፣ በክትትልና በክህሎት በማጎልበት ዜጎችንና ሀገርን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል በብዙ ይታመ ናል።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ የነበሩት ባንኪ ሙን በአንድ መድረክ ላይ ስለሴቶች ሲናገሩ “ሴቶችን ማብቃት ቤተሰብን ፣ ማህበረሰብንና ዜጎችን ማብቃት ነው። ሴቶችን ከማብቃት የተሻሻለ ውጤታማ የእድገት መሳሪያ የለም” ብለው ነበር። ይህም የበቁ ሴቶችን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አጉልቶ ያሳያል።
የበቁ ሴቶች ለግለሰብና ለማህበረሰብ የኑሮ መሻሻል በተሻለ መልኩ መሥራት ይችላሉ። በማህበራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት ላይ ወሳኝ ሚናም ይጫወታሉ። ደህንነቱ የተረጋገጠ፣ ጤናማና ከድህነት የጸዳ ቀጣይነት ያለው ቤተሰብና ማህበረሰብ ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።
በጤና መርሃ ግብሮች ላይ በመሳተፍ፤ የተሻለ የጤና አጠባበቅ ስልት እንዲዘረጋ፣ የእናቶች፣የሕጻናትና የሕዝብ የጤና አገልግሎት እንዲስፋፋ፤ ደህንነቱ የተጠበቀ ጤናማ ኅብረተሰብ እንዲፈጠር ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ፡፡
በፖሊሲ ቀረጻ ላይ ልጆች፣ ሕጻናት፣ እናቶችና የተገለሉ አካላት እንዲካተቱ በዳበረ አቅም መንቀሳቀስ ይችላሉ፤ መብቶችን ለማስጠበቅና ፍትሐዊነትን ለማስፈን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። በትምህርት ውጤታማነት ላይ ሊኖራቻቸው የሚችለውም አበርክቶ ቀላል አይሆንም፡፡
በትምህርት፣ በሥነ-ምግባር በጤና፣ በምጣኔ ሀብትና በማህበራዊ ደህንነት የበለጸገ፣ ርህራሄን የተላበሰ፣ ታማኝ፣ ታጋሽ ኃላፊነት መሸከም የሚችል ሀገር ተረካቢ ብቁ ዜጋ በመፍጠርና ለትውልዱ የተሻለ ነገን በማመቻቸት ዘላቂ ሰላምን ለመፍጠር የሚኖራቸው አዎንታዊ አስተዋጽኦም ከግምት በላይ ነው።
ለሰዎች መብት በመከራከር ፣ ግጭቶችን በመፍታት፣ እርቅና ይቅርታን በማበረታታት፣ ለሰላም ግንባታ ትኩረት በመስጠት፣ ሰላማዊና የተረጋጋ ኅብረተሰብ እንዲፈጠር ሊኖራቸው የሚችለው አስተዋጽኦም ታስቦበት ተግባራዊ ከሆነ ከፍተኛ እንደሚሆን ይታመ ናል።
በአጠቃላይ የሴቶችን ችሎታና ልዩ ባህሪይ በእውቀትና በክህሎት በማጎልበት፣ በማበረታታት. ሥነ-ምግባራዊና ሥነ-ልቦናዊ እገዛ በማድረግ ፣ የመሥሪያ ሜዳውን በማመቻቸት፣ ወደ አመራር እንዲወጡ መሰላሉን በመዘርጋት በሁሉም የልማት ዘርፎች ላይ እውቀታቸውን፣ጥንካሬያቸውን፣ እሴቶቻቸውን ፣ ሃብታቸውን/ ሥራ ላይ በማዋል ቤተሰባዊ ፣ማህበራዊና ሀገራዊ እድገት ማምጣት ይቻላል።
ምጣኔ ሀብትን በማሳደግ ድህነትን ለማሸነፍ ፣ ጤናማ ግንኙነቶችን በማጠናከር ግጭቶችን መፍታትና ሰላምን በተሻለ መንገድ ማስፈን ይረዳል ። በመተሳሰብ፤ በመረዳዳትና በመደጋገፍ አብሮ ሰርቶ አብሮ ማደግን ባህሉ ያደረገ፤ አብሮነትን ፣ እኩልነትን፣ አካታችነትንና መቻቻልን ያዳበረና የተረጋጋ ህብረተሰብ ለመፍጠር ሴቶችን በሁለንተናዊ መንገድ ማብቃት ወሳኝ ነው።
በእውቀትና በመልካም ሥነ- ምግባር የታነጸ ሀገር ተረካቢ ትውልድ በመቅረጽ፤ ብሩህ ነገንና እኩልነት የሰፈነበት ዘላቂ ዓለም ለመፍጠር የሴቶች ተሳትፎ ከፍተኛ እንደሆነም በተለያዩ ወቅቶች የተካሄዱ ጥናቶች በተጨባጭ ያመላክታሉ። ይህን እውነት ተረድቶ መንቀሳቀስ እንደሀገር ፣ ለጀመርነው የብልፅግና ጉዞ ስኬት ወሳኝ አቅም መፍጠር ነው።
ሙሉእመቤት ጌታቸው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 25 ቀን 2017 ዓ.ም