
አዲስ አበባ፡- ከሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ የሚከሰተው የመብት ጥሰት ትኩረት ሊሰጠው እና የሚመለከታቸው አካላት ሊወያዩበት እንደሚገባ የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት በትናንትናው እለት ‹‹ዜጎች በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) መረጃ እንዳይጭበረበሩ ትክክለኛ መረጃ የሚያገኙበት እሳቤ የሚጎላበት ቀን ሊሆን ይገባል›› በሚል መሪ ቃል የፕሬስ ነጻነትን ቀንን አክብሯል፡፡
የምክር ቤቱ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ታምራት ኃይሉ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የሀገራችን መገናኛ ብዙኃን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ የመጡ የሰው ሰራሽ አስተውሎት እድገቶችን መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይ ቴክኖሎጂውን ተከትሎ ሊሻሻሉ የሚገባቸው ህጎች፣ አሰራሮችና የሚከሰተውን የመብት ጥሰት ልምዶች ላይ በመወያየት መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ሰው ሰራሽ አስተውሎቱ በጋዜጠኝነት ሥራዎች እና ክህሎቶች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ መገምገም እንደሚገባ አስገዝበው፤ አስተውሎቱ የጋዜጠኞች የሥራ ዕድሎችን እንዴት ሊጎዳ እንደሚችል እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በሰው ሰራሽ አስተውሎቱ በሚመራ ሚዲያ ላይ ለመሥራት አዳዲስ ክህሎቶችን እንዴት እንደሚያገኙ ማቀድ ያስፈልጋልም ብለዋል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት የሐሰት ወይም አሳሳች መረጃዎችን የመፍጠር እና የማሰራጨት አቅም እንዳለው በመገንዘብ ፣ የሀሰት ዜናዎችን የመዋጋት እና በሕዝብ በመገናኛ ብዙኃን ላይ ያለውን እምነት የመጠበቅ ተግዳሮቶች ላይ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
እንደ አቶ ታምራት ገለጻ፤ በሰው ሰራሽ አስተውሎቱ የመረጃ ትንተና፣ እውነታን ማረጋገጥ፣ የይዘት ፈጠራ እና የተመልካቾችን ተሳትፎ በሚያሻሽሉ መሳሪያዎች አማካኝነት የጋዜጠኝነት ልምዶችን ለማሳደግ የሥነ ምግባር እሳቤዎች እና ደንቦች መከተል ይገባል፡፡
ሰው ሰራሽ አስተውሎት በመገናኛ ብዙኃን ውስጥ በኃላፊነት ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው፤ በተለይ የሰብአዊ መብቶችን በማክበር ግልጽነትን እና ተጠያቂነትን በማስተዋወቅ ረገድ አስፈላጊ የሆኑትን የሥነምግባር ማሕቀፎች እና የቁጥጥር ዘዴዎች መወያየት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡
የዘንድሮ የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ሲከበር የሀገራችን ጋዜጠኞች የዓለማችንን የቴክኖሎጂ እሳቤ ጠንቅቀው በመረዳት ፤ ትክክለኛ መረጃን ለህብረተሰቡ በማድረስ በኩል ያላቸውን የማይተካ ሚና እንዲያጎለብቱ እድል ለመፍጠር እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት በሥነ ምግባር የታነጸ በኃላፊነት ስሜት ሕዝብን የሚያገለግል ሚዲያ በሀገራችን እንዲጎለብት የሚሠራ ተቋም እንደሆነ ገልጸው፤ በሕግ ተመዝግበው ፈቃድ የወሰዱ ከ100 በላይ የሕዝብ ፣የንግድ፣ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙኃንንና የበይነ መረብ ሚዲያንና የጋዜጠኞች ሙያ ማህበራትን በአባልነት በመያዝ የእርስ በርስ የቁጥጥር ሥርዓትን ተግባራዊ እያደረገ የሚገኝ ተቋም እንደሆነ ይታወቃል፡፡
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 25 ቀን 2017 ዓ.ም