አሜሪካ እና ዩክሬን የማዕድን ስምምነት ተፈራረሙ

አሜሪካ፤ የዩክሬንን የኃይል እና የማዕድን ሀብት በጋራ ለመጠቀም የሚያስችላትን ስምምነት ለወራት ከዘለቀ ውጥረት የተሞላበት ድርድር በኋላ ተፈራረመች። ሁለቱ ሀገራት ዩክሬን ከሩሲያ ጋር እያደረገችው ባለው ጦርነት የተጎዳው ኢኮኖሚዋ እንዲያገግም ለማድረግ የሚያስችል የመልሶ ግንባታ ኢንቨስትመንት ፈንድ ለማቋቋም ተስማምተዋል።

የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሴንት፤ ስምምነቱ ዩክሬን ውስጥ ዘላቂ ሰላም እና ብልጽግና እንዲመጣ ለማድረግ ሁለቱም ሀገራት ቁርጠኛ መሆናቸውን ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል። ከአሜሪካ ወታደራዊ ድጋፍ ለማግኘት ለምትሻው ዩክሬን አሁን የተደረገው ስምምነት ወሳኝ ተደርጎ ታይቷል።

ዩክሬን፤ እንደ ግራፋይት፣ ቲታኒየም እና ሊትየም የተባሉት ወሳኝ ማዕድናት ሰፊ ክምችት እንዳላት ይታመናል። እነዚህ ማዕድናት ለታዳሽ ኃይል፣ ለወታደራዊ ሥራዎች እና በኢንዱስትሪ መሠረተ ልማት ውስጥ ጥቅም ላይ ስለሚውሉ በእጅጉ ተፈላጊ ናቸው። ይህ የሁለቱ ሀገራት ስምምነት መፈጸሙ የተሰማው አሜሪካ የዓለምን 90 በመቶ የሚሆን ብርቅዬ ማዕድናት ክምችት ካላት ቻይና ጋር የንግድ ጦርነት ውስጥ ባለችበት በዚህ ወቅት ነው።

የአሜሪካ ግምጃ ቤት ረቡዕ ዕለት ያወጣው መግለጫ እንደሚያስረዳው አዲስ የተመሠረተው የአሜሪካ እና ዩክሬን የመልሶ ግንባታ ኢንቨስትመንት ፈንድ ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረችበት እኤአ የካቲት 2022 ጀምሮ ዋሽንግተን ለኪዬቭ ለላከችው “ከፍተኛ የፋይናንስ እና ቁሳዊ ድጋፍ” እውቅና ሰጥቷል። አሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ በቪድዮ ባወጡት መግለጫ ስምምነቱ “የዩክሬንን የዕድገት ሀብት ለመክፈት” የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል።

ስምምነቱ ይፋ የተደረገበት የቋንቋ አጠቃቀም በትራምፕ አስተዳደር ከተለመደው በበለጠ መልኩ ለዩክሬን አጋርነት ያሳየ ነው። መግለጫው፤ “የሩሲያን ሙሉ ወረራ” ያመለከተ ሲሆን “የሩሲያን ጦርነት በገንዘብ የደገፈ ወይም ግብዓቶችን ያቀረበ የትኛውም መንግሥት ወይም ሰው ከዩክሬን መልሶ ግንባታ እንደማይጠቀም” ገልጿል። እስካሁን ድረስ ስምምነቱን በተመለከተ ከክሬምሊን የተሰጠ ምላሽ የለም።

ስምምነቱን ለመፈራረም ወደ ዋሽንግተን የተጓዙት የዩክሬን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ዩሊያ ሲቪራይደንኮ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ አዲሱ ፈንድ “ዓለምአቀፍ ኢንቨስትመንትን ወደ ሀገራችን ይስባል” ብለዋል። የስምምነቱን አንቀጾች የዘረዘሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሯ፤ ፕሮጀክቱ ማዕድናት፣ ነዳጅ እና ጋዝን እንደሚያካትት የገለጹ ሲሆን፣ እነዚህ ሀብቶች የዩክሬን ንብረቶች ሆነው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የሁለቱ ሀገራት አጋርነት እኩል በእኩል እንደሚሆን፤ ስምምነቱ ግን በኪዬቭ በሚገኙ ሕግ አውጪዎች መጽደቅ እንደሚኖርበት ገልጸዋል። በስምምነቱ መሠረት አሜሪካ የአየር መከላከያ ሥርዓትን ጨምሮ የተለያዩ አዲስ ድጋፎችን ለዩክሬን እንደምታደርግም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሯ አክለዋል። ፕሬዚዳንት ትራምፕ፤ ለኪዬቭ የደህንነት ዋስትና ለመስጠት ይህንን ስምምነት መፈራረምን እንደ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ በተደጋጋሚ ግፊት ሲያደርጉ ነበር።

የስምምነቱ ረቂቅ እንደሚያመለክተው ዩክሬን በቀጣይ ከአሜሪካ ለምታገኘው የደህንነት እገዛ ምላሽ በሚሆን መልኩ፤ ካላት የተፈጥሮ ሀብት ውስጥ የተወሰነውን ዋሽንግተን እንድታገኝ ታደርጋለች። ዋሽንግተን በአሁኑ ስምምነት የምታገኘው፤ ትራምፕ ሲፈልጉ ከነበረው በብዙ ያነሰ ነው። ፕሬዚዳንቱ፤ አሜሪካ ከጦርነቱ ጅማሬ አንስቶ ለዩክሬን የሰጠችው ድጋፍ በሙሉ ተመልሶ እንዲከፈል ሲጠይቁ ነበር። የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ አሜሪካ አስቀድማ ስትጠይቅ ከነበሩት ነገሮች ውስጥ የተወሰኑት እንዲቀሩ ማድረግ ችለዋል።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት፤ ስምምነቱ የዘገየው ኪዬቭ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ለውጥ ለማድረግ እየሞከረች ስለነበረ ነው ብለዋል። እየተደረገ ለነበረው ንግግር ቅርበት ያላቸው አንድ የአሜሪካ ምንጭ፤ ዩክሬን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የተጠናቀቀው ስምምነት አንዳንድ ነጥቦች ተመልሰው እንዲታዩ መፈለጓን በመጥቀስ ረቡዕ ዕለት ተችተው ነበር። ምንጩ፤ አከራካሪ ከነበሩት ነጥቦች መካከል የፈንዱ አስተዳደር፣ የግልጽነት ጉዳይ እንዲሁም ሁሉም ፈንዶች ክትትል እንዲደረግባቸው የሚያስችሉ ርምጃዎችን የተመለከቱ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

የሁለቱ ሀገራት ተወካዮች የስምምነቱን ቴክኒካዊ ሰነድ የተፈራረሙት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ነበር። የመጀመሪያው ስምምት ባለፈው የካቲት እንዲፈረም ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም ትራምፕ ዜሌንስኪን “በሦስተኛው የዓለም ጦርነት እየቆመርክ ነው” ብለው በተቹበት የዋይት ሐውስ ንትርክ ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል።

የአሁኑ ስምምነት የተሳካው ትራምፕ እና ዜሌንስኪ በፖፕ ፍራንሲስ ቀብር ሥነ ሥርዓት ወቅት ፊት ለፊት ከተገናኙ ከቀናት በኋላ እንዲሁም ሞስኮ እና ዋሽንግተን በዩክሬን ተኩስ አቁም እንዲደረግ ሲያካሂዱት የነበረው ንግግር በተቀዛቀዘበት ወቅት ነው። ትራምፕ ከዜሌንስኪ ጋር በቫቲካን በተገናኙበት ወቅት ስምምነት ላይ እንዲደረስ እንደተጫኑ ኒውስ ኔሽን የዜና ምንጭ ተናግረው ነበር።

“ፊርማህን የምታኖርበት ስምምነት ላይ መድረስ ከቻልን በጣም ጥሩ ነገር እንደሚሆን እየነገርኩት ነበር” ብለዋል። “ምክንያቱም ሩሲያ እጅግ ትልቅ እና የበለጠ ጠንካራ ናት። ሩሲያ ወደፊት እየገሰገሰች ነው” ሲሉም ተደምጠዋል። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ስምምነቱ ዋሽንግተን ከጦርነቱ መጀመር አንስቶ ለኪዬቭ የሰጠችው በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር መልሶ እንደሚያስገኝ ተናግረዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You