በክልሉ የሚገኙ ታጣቂዎች፣ ፖለቲከኞችና ሌሎችም ወገኖች አጀንዳዎቻቸውን ማቅረብ እንደሚችሉ ተጠቆመ

– በትግራይ ክልል የምክክር ሂደቱን ለማከናወን ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑም ተገለጸ

አዲስ አበባ፡- በአማራ ክልል የሚገኙ ታጣቂዎች፣ ፖለቲከኞችና ሌሎችም ወገኖች አጀንዳዎቻቸውን ማቅረብ እንደሚችሉ ተጠቆመ። በክልሉ የተካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብና በሀገራዊ ምክክር ጉባዔ የሚሳተፉ ተወካዮችን የማስመረጥ ሂደት ስኬታማ እንደነበር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የክልሉ አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ሚያዝያ አራት ቢጠናቀቅም በሂደቱ ያልተሳተፉ ታጣቂዎች፣ ፖለቲከኞችና ሌሎችም ወገኖች አሁንም አጀንዳዎችን ማቅረብ ይችላሉ ።

በክልሉ የጸጥታ ስጋቶች እና ግጭቶች ባሉበት ሁኔታ የተካሄደ የአጀንዳ ማሰባሰብና በሀገራዊ ምክክር ጉባዔ የሚሳተፉ ተወካዮችን የማስመረጥ ሂደት ስኬታማነት ያመለከቱት አቶ ጥበቡ፤ ተሳታፊዎችን መድረኩ ላይ እንዲገኙ ለማስቻል ሁሉንም የትራንስፖርት አማራጭ በመጠቀም የማጓጓዝ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።

በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ወገኖች በሂደቱ ላይ የሚሳተፉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ሲሠራ እንደነበር ጠቁመው ፤ እነዚህ ወገኖች አሉን የሚሏቸውን አጀንዳዎች ወደ ምክክር  እንዲያመጡ ይፋዊ ጥያቄ መቅረቡን አመልክተዋል። በነበረው አጭር ጊዜ ጉዳዩን ማሳካት እንዳልተቻለም አስታውቀዋል።

ከዚህም ባለፈ በእስር ላይ ያሉ የሃሳብ መሪዎችና ፖለቲከኞች በምክር ሂደቱ ላይ የሚሳተፉበት ሁኔታ እንዲኖር ኮሚሽኑ ለክልሉ መንግሥት ይፋዊ ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር አስታውሰው፤ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ውጤት ባይገኝበትም ሂደቱ መጀመሩ በራሱ በመልካም የሚነሳ እንደሆነ አስታውቀዋል።

የክልሉ አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ሚያዝያ አራት ቢጠናቀቅም በሂደቱ ያልተሳተፉ ታጣቂዎች፣ ፖለቲከኞችና ሌሎችም ወገኖች አሁንም አጀንዳዎችን ማቅረብ እንደሚችሉ አስታውቀዋል፤ እነዚህ ወገኖች በቀጣይነት በሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር ላይም ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማድረግ ጥረቶች መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

በሂደቱ እስካሁን ያልተካተተውን የትግራይ ክልል ለማካተት ከተለያዩ ባለድርሻዎች ጋር ውይይቶች ሲከናወኑ እንደነበር አመልክተው፤ አዲስ ከተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት የሚያስችሉ ግንኑነቶችን እየተፈጠሩ እንደሆነ አስታውቀዋል ።

አዲሱ አስተዳደር ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር መግባባት ከደረሱባቸው ጉዳዮች አንዱ ምክክሩን አሳታፊና አካታች በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ማድረግ እንደሆነም ጠቁመዋል ። በቀጣይም ኮሚሽኑና ጊዜያዊ አስተዳደሩ ተገናኝተው በጉዳዩ ላይ ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ብለዋል።

ኮሚሽኑ ቀሪ ተግባራትን ለማጠናቀቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን አመልክተው፤ በግንቦት ወር መጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ በፌዴራል ደረጃ የአጀንዳ ማሰባሰብ ለማከናወን ዝግጅቶች በመጠናቀቅ ላይ እንደሆኑም ጠቁመዋል ።

በተጨማሪ ለአጀንዳ ቀረጻው ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እስካሁን የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን የማደራጀትና የማጠናቀር ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አመልክተዋል።

በአማራ ክልል የክልሉን አጀንዳ የማሰባሰብና በሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን የመምረጥ ሂደት ከመጋቢት 27 እስከ ሚያዚያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።

በፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You