“ከዓለም ጋር ተስማምቶ ለመቀጠል የሚያስችል የትምህርት እና የቴክኖሎጂ ኢንቨስትመንት መዘርጋት ይገባል”  – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፦ ከዓለም ጋር ተስማምቶ ለመቀጠል የሚያስችል የትምህርት እና የቴክኖሎጂ ኢንቨስትመንት መዘርጋት እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ አመለከቱ ። 14ኛው “Innovation Africa 2025” ዓለም አቀፍ ጉባዔ ትናንት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በጉባዔው ወቅት እንደገለጹት፤ አፍሪካ የወጣት ትውልድ አህጉር በመሆኗ ከዓለም ጋር ተስማምቶ ለመቀጠል የሚያስችል የትምህርት እና የቴክኖሎጂ ኢንቨስትመንት መዘርጋት ይገባል።

ዓለም አቀፍ ጉባዔው የአፍሪካን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለማፋጠን እንደሚያግዝ አመልክተው ፤ ኢትዮጵያ የትምህርት እና የክህሎት ሥልጠናን ማዕከል በማድረግ እየሠራች መሆኗን ጠቁመዋል። ለዚህም የአዳዲስ ትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ የተሻሻሉ መሠረተ ልማቶች እና ጠንካራ የዲጂታል ትስስር እየተፈጠረ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በአፍሪካ አሁንም የትምህርት እና የዲጂታላይዜሽን ጉዞን በማሳካት በኩል ቀሪ ሥራዎች አሉብን ያሉት አቶ ተመስገን፤ ለነገው ትውልድ የምናደርገውን የትምህርት እና የቴክኖሎጂ ኢንቨስትመንት በተቀናጀ እና በተቀላጠፈ መልኩ ማከናወን እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው፤ አሁን ያለንበት የዓለም ሁኔታ በጣም የተወሳሰበ በመሆኑ መጪውን ትውልድና ወጣት በትምህርት፣ በቴክኖሎጂና በክህሎት ማዘጋጀት ይጠበቃል ብለዋል።

በጉባዔው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት የትምህርት ሚኒስትሮች፣ በዓለም የሚገኙ የትምህርት አጋር ድርጅቶች ተወካዮች እንዲሁም የሀገራችን ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

ጉባዔው ለሚቀጥሉት ሁለት ቀናት የሚቆይ ይሆናል።

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2017 ዓ.ም

አማን ረሺድ

Recommended For You