
በኢራን ግዙፍ የንግድ ወደብ ላይ በደረሰ ከፍተኛ ፍንዳታ ዜናው እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ቢያንስ 14 ሰዎች ሲሞቱ፣ 750 ደግሞ መቁሰላቸውን የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ገለጹ። ፍንዳታው የደረሰው ቅዳሜ ጠዋት በባንዳር አባስ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው ሻሂድ ራጃኢ በተባለው የሀገሪቱ ግዙፍ የንግድ ወደብ ላይ ነው። በአካባቢው የሚገኙ ሕንጻዎች መስኮት እና ጣርያዎች የገነጠለ እንዲሁም መኪናዎችን ያወደመ ፍንዳታ ነበር ተብሏል።
ነዋሪዎች ፍንዳታው 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ ይሰማ ነበር ሲሉ ተናግረዋል። ከፍተኛ ፍንዳታ ከመድረሱ በፊት የእሳት ቃጠሎ ተከስቶ ነበር። ሰዎች ከአደጋው ራሳቸውን ለማትረፍ ሲሮጡ እንዲሁም በፍንዳታው የተጎዱ መሬት ላይ ወድቀው ይታያል። አንድ ከአደጋው የተረፈ ግለሰብ ለሀገሪቱ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ “መጋዘኑ ሙሉ በሙሉ በጭስ፣ አቧራ እና አመድ ተሞላ። ራሴን ያገኘሁት ጠረጴዛ ሥር ነው። ጠረጴዛው ሥር እኔ ልግባ ወይም ፍንዳታው ይወርውረኝ የማስታውሰው ነገር የለም” ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል።
ከአየር ላይ የተቀረፁ ምስሎች ቢያንስ ሦስት የተለያዩ ቦታዎች ቃጠሎው መስፋፋቱን የሚያሳዩ ሲሆን የኢራን ሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትርም እሳቱ ከኮንቴይነር ወደ ኮንቴይነር እየተስፋፋ መሆኑን አረጋግጠዋል። እሁድ እለት በአካባቢው የሚገኙ ትምህርት ቤቶች እና ቢሮዎች ተዘግተው እንዲቆዩ ተወስኗል። አንድ የግል የባሕር ኃይል ኩባንያ በእሳት ጉዳት የደረሰባቸው ኮንቴይነሮች ለባሌስቲክ ሚሳኤል ማምረቻ ጥቅም ላይ የሚውል ነዳጅ ሳይዙ አይቀሩም ብሏል።
አምብሬ የተሰኘው የደህንነት ተቋም የእሳት አደጋው “ለኢራን ባሌስቲክ ሚሳኤል ጥቅም ላይ የሚውል ነዳጅ ያለተገቢው ጥንቃቄ በመያዙ የተከሰተ” መሆኑን ተናግሯል። አምብሬ የኢራን ባንዲራን የምታውለበልብ መርከብ “ሶዲየም ፐርክሎሬት የተሰኘ የሮኬት ነዳጅ እኤአ በመጋቢት ወር 2025 አራግፋ ነበር” ብሏል። ከዚህ ቀደም ብሎ ፋይናንሻል ታይምስ ሁለት የጭነት መርከቦች ከቻይና ወደ ኢራን ነዳጅ ማጓጓዛቸውን ዘግቦ ነበር።
የሀገሪቱ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን የዓይን እማኞችን ጠቅሶ ፍንዳታው የደረሰው እሳት ከተቀሰቀሰ እና “ተቀጣጣይ ነገሮችን” ወደ ያዘእና ያልታሸገ ኮንቴይነር ከተዛመተ በኋላ መሆኑን ዘግቧል። የሀገሪቱ ጉምሩክ መሥርያ ቤት ኃላፊዎች በሀገሪቱ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ በሰጡት መግለጫ ፍንዳታው የተከሰተው ምናልባት የአደገኛ ኬሚካሎች ማከማቻ ላይ እሳት ከተቀሰቀሰ በኋላ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።
አምብሬ የሀገሪቱን ብሔራዊ አደጋ መከላከያ መሥርያ ቤት ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደተናገረው በሻሂድ ራጃኢ ወደብ ኬሚካሎች ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ እንዲቀመጡ ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር። ሻሂድ ራጃኢ ወደብ ኢራን ካሏት ዘመናዊ እና ትልቅ የንግድ ወደቦች መካከል አንዱ ነው። ወደቡ ዋነኛ የነዳጅ ጭነት ማመላለሻ በሆነችው ሆርሙዝ የባሕር ዳርቻ ላይ፣ ከባንደር አባስ በስተምዕራብ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የኢራን ባሕር ኃይል ዋና መቀመጫ አካባቢ ይገኛል።
የኢራን ብሔራዊ ነዳጅ ማምረቻ ኩባንያ ፍንዳታው ከሀገሪቱ ነዳጅ ማጣሪያ፣ የነዳጅ ማከማቻ እና ማስተላለፊያዎች ጋር “ምንም ዓይነት ግንኙነት” እንደሌለው መናገሩን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል። የኢራን ፕሬዚዳንት ማሶድ ፔዜስኪያን በአደጋው የተሰማቸውን “ጥልቅ ኀዘን” ገልጸዋል።
ሀገሪቱ በፍንዳታው ዙሪያ ምርመራ እንደምታደርግ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ ፤ ይህንን እንዲመሩ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩን ወደ ሥፍራው ልከዋል። ቅዳሜ ዕለት የደረሰው ፍንዳታ ሀገሪቱ ከአሜሪካ ጋር የኒውክሌር ፕሮግራሟን በሚመለከት ከምታደርገው ውይይት ጋር ተያይዟል። አሜሪካ ቴህራን የኒውክሌር መሣሪያዎችን እንዳትታጠቅ ለማድረግ ያለመ ድርድር ማድረግ ጀምራለች።
በኦማን አደራዳሪዎች በኩል እየተካሄደ ያለው ድርድርን ሁለቱም ሀገራት በመልካም ሁኔታ እየሄደ መሆኑን ቢናገሩን የኢራን ከፍተኛ ልዑክ ተወካይ ልዩነቶችን ለማጥበብ መሠራት ያለባቸው ነገሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል። ድርድሩ በሚቀጥለው ሳምንት ይቀጥላል ተብሏል። ኢራን የተጣለባት ማዕቀብ የሚላላ ከሆነ የኒውክሌር ፕሮግራሟን ለማጠፍ ዝግጁ መሆኗን ዩራኒየም ማበልጸጓን ግን እንደምትቀጥል ተናግራለች።
ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟ ለሰላማዊ ዜጎች ጥቅም መሆኑን ትናገራለች። ከአውሮፓውያኑ 2018 ወዲህ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል በከፍተኛ ልዑካን የተመራ ውይይት ሲደረግ ይህ የመጀመርያው ነው ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም