
- በአውደ ርዕዩ በርካታ ተስፋ ሰጪ ፈጠራዎች ታይተዋል
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያን በአፍሪካ እና በዓለም አደባባይ በኩራት እንድትቆም የሚያደርግ ትውልድ በብዛት ለማፍራት መምህራን፣ ወላጆች እና ባለድርሻ አካላት ያለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጥሪ አቀረበ። በአውደ ርዕዩ በርካታ ተስፋ ሰጪ ፈጠራዎች መታየታቸው ተጠቁሟል።
የቢሮው ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ባዘጋጀው የሳይንስ ፈጠራ አውደ ርዕይ የመዝግያ መርሀ ግብር ላይ እንደተናገሩት፤ ባለፉት ሶስት ቀናት ተማሪዎቹ ያሳዩዋቸው የፈጠራ ሥራዎች ለሀገሪቷ ተስፋ ሰጪ ናቸው። ኢትዮጵያን በአፍሪካ እና በዓለም አደባባይ በኩራት እንድትቆም የሚያደርግ ትውልድ ለማፍራትም መምህራን፣ ወላጆች እና ባለድርሻ አካላት ያለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ወላጆች ልጆቻቸው የት እንደሚውሉ፣ ምን እንደተማሩ፣ ከማን ጋር እንደሚውሉ እና በትምህርት ገበታው ምን እንደቀሰሙ ሊያውቁ ይገባል ያሉት የቢሮው ኃላፊ፤ ብቁ እና አዋቂ ትውልድን ለማፍራት በሚደረገው ጥረት እንዳይስተጓጎልና ተማሪዎች የማህበራዊ ሚዲያ ሰለባ እንዳይሆኑ ለማድረግ፤ ወላጆችና መምህራን መምከርና ማስተማር እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
የትምህርት ዘርፉ ላይ ያሉ አመራሮች መምህራኑ የሚበቅባቸውን እያደረጉ እንደሆነም ሊከታተሉ፣ ሊያደራጁ እና ሊቆጣጠሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
አውደ ርዕዩ ‹‹በፈጠራ ሥራ የተካነ ትጉህ ትውልድ ለሀገር ብልፅግና›› በሚል መሪ ቃል እንደተዘጋጀ የሚናገሩት ዘላለም (ዶ/ር)፤ የዜጎች የፈጠራ ክህሎት መዳበር፣ እርስ በእርስ መደጋገፍ እና መወዳደር ጥራት ያላቸው ፈጠራዎች እንዲመነጩ ማድረግ የሀገርን ብልፅግና ሊያረጋግጥ እንደሚችል ጠቁመዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ ፤በውድድር መካከል የሚኖር ማሸነፍ እና መሸነፍ ልምድ የሚወሰድበት ነው። አንድ መምረጥ ስለሚያስፈልግ እንጂ ሁሉም ተማሪዎችም አሸናፊዎች ናቸው። ሁሉም ተወዳዳሪዎች ለውድድሩ ድምቀት በመሆን ያላቸውን ክህሎት እና ችሎታ ለሌሎች አስተላልፈዋል። የቢሮው ድካም እና ጥረት ውጤት እያመጣ መሆኑም ታይቷል።
የአዲስ አበባ የትምህርት ቢሮ ለሀገር እና ለትውልድ ስኬት የሚቆም መሆኑን የሚገልጹት ኃላፊው፤ ሌት ተቀን በመሥራትም ኃላፊነት የሚሰማው ትውልድ ማፍራት መቻሉን ገልጸዋል።
ኃላፊው ቢሮው ከውድድር መርሃ ግብሩ በርካታ ልምዶችን ማግኘቱን ገልጸው፤ ተማሪዎቹም ከተለያየ አካባቢ የመጡ እንደመሆናቸው የተለያዩ ልምዶችን እንዲለዋወጡ እድል ያገኙበት፣ በቀጣይ በትብብር እንዲሠሩ የተዋወቁበት፣ የሥራን ክብርነት ያወቁበት፣ ወድቆ መነሳትን እና ማሸነፍንም የተማሩበት መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል።
እንዲህ ያሉ አውደ ርዕዮች ፈጠራን ለማበረታታት አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ትምህርት ቤቶችም ለሳይንሳዊ ፈጠራዎች መሠረት የሚጥሉ ችግር ፈቺ የፈጠራ ውጤቶችን የሚፈጥሩ እንዲሆኑ ቢሮው በትኩረት ይሠራል ብለዋል። አውደ ርዕዩም ተማሪዎችን ለማበረታታት የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ 10ኛውን ከተማ አቀፍ የሳይንስ የፈጠራ ሥራ አውደ ርዕይ ከሚያዚያ 16 እስከ 18 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ “በፈጠራ ሥራ የተካነ ትጉህ ትውልድ ለሀገር ብልፅግና!” በሚል መሪ ሃሳብ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የትምህርት አመራሮች ፣ የትምህርት ባለድርሻ አካላት፣ የትምህርት ባለሙያዎች፣ መምህራንና ተማሪዎች በተገኙበት በወዳጅነት ፓርክ ሲያካሂድ ቆይቷል።
መክሊት ወንድወሰን