ንቅናቄው ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ የምታሳካውን ድሎች በኢንዱስትሪውም ለመድገም ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል

አዲስ አበባ፡- የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ›› ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ የምታሳካውን ድሎች በኢንዱስትሪውም ለመድገም ራሱን የቻለ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል የኢትዮጵያ ታምርት የሩጫ ውድድር መርሃ ግብር ትናንት ሲካሄድ ለኢፕድ እንደገለጹት የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ዋነኛ ዓላማው የኢትዮጵያን ምርቶች ለገበያ ማስተዋወቅ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሀገሪቷ በርካታ ምርቶችን ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ እያቀረበች ነው ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ በሀገሪቱ ውስጥ የስፖርት ትጥቆችን በማምረት ሂደት ከጊዜ ወደ ጊዜ የምርቶች ጥራት እየጨመረ እንዳለም አመልክተው፤ በ‹‹የኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄም ዜጎች በሀገራቸው ምርት እንዲኮሩ ጥራት ያለው ምርት እየተመረተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ንቅናቄው ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ምርት እንዲያውቁ እና እንዲጠቀሙ ለማድረግ የራሱን ሚና እንደሚጫወትም ጠቁመው፤ ንቅናቄው ገቢ ምርትን በመተካት በኩልም ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ አምራችና ጤናማ ትውልድ ለማፍራት ስፖርታዊ ውድድሩ ትልቅ ሚና አለው። በውድድሩ የውጭ ሀገራት አምባሳደሮች፣ ክለቦችና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት በመሆኑ ንቅናቄውን ለማስተዋወቅ እድል ፈጥሯል፡፡

በንቅናቄው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ በሚደምቅበት የአትሌቲክስ ስፖርት ውድድር መካሄዱ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለማስተዋወቅ ገንቢ ሚና እንዳለውም አንስተዋል።

በውድድሩ ከ14ሺህ በላይ ዜጎች እና 34 ክለቦች እንደተሳተፉበት ገልጸው፤ መነሻና መድረሻውን መስቀል አደባባይ ላደረገው የ 10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር መካሄድ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ድርጅቶች፣ ግለሰቦችና ተወዳዳሪዎች ምስጋና አቅርበዋል።

የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ በበኩላቸው ስፖርት የማህበረሰቡ ባህል እንዲሆን ለማድረግ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የተለያዩ ማህበረሰብ አቀፍ የጎዳና ላይ ሩጫዎችም መነቃቃትን የሚፈጥሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ሩጫው የዜጎችን አንድነት በማጠናከር ረገድ ከተለያዩ አካባቢ የመጡ እና የራሳቸው ቋንቋ፣ ባህልና ሃይማኖት ያላቸው በመሆኑ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡ አዳዲስ አትሌቶችንም ለማፍራት እንደሚጠቅምም ገልጸዋል፡፡

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ መንግሥት ስፖርት ንቁ እና ብቁ ዜጋን ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው በመገንዘቡ ላለፉት ስድስት ዓመታት ብዙ ስኬታማ ሥራዎች መሥራት ችሏል፡፡ ስፖርትን ባህል ለማድረግም የተሠሩ ሥራዎችም ውጤታማ ናቸው፡፡ በስፖርት ልማት ፖሊሲ ላይ እንደተመላከተው ስፖርት ማህበረሰባዊ መሠረት እንዲኖረው ትጥቆችን እና መሣሪያዎችን በሀገር ውስጥ ማምረት እና መጠቀም ከፍተኛ ውጤት እያመጣ ይገኛል፡፡

ሚኒስትሯ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ለስፖርት ትጥቅ ትልቅ የውጭ ምንዛሬ እንደምታወጣ ገልጸው፤ አሁን በሀገር ውስጥ የስፖርት ትጥቅ በማምረት ላይ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ሲወጣ የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዜጎችም ንቁ እና ብቁ ለመሆን ለሚያደርጓቸው የስፖርት እንቅስቃሴዎች በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ትጥቆችን በአነስተኛ ዋጋ እንዲያገኙ ማስቻሉንም አስታውቀዋል፡፡

መላው የስፖርት ቤተሰብ እና ማህበራት በሀገራችን የሚመረቱትን የስፖርት ትጥቅ እና መሣሪያዎች በመጠቀም የውጭ ምንዛሬን እንዲያድኑም ጠይቀዋል፡፡ ኢንዱስትሪዎችም ለዜጎች ጥራት ያለው እና በቂ ምርት በማቅረብ እንዲያከፋፍሉ አደራ ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ላለፉት ሶስት ዓመታት ሲካሄድ መቆየቱ ይታወቃል፡፡

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You