
አዲስ አበባ፡- ራሱን በየጊዜው እየገመገመ በሁለንተናዊ መስኩ እያበቃ ሀገሩን የሚወድና የተሰለፈበትን ዓላማ ጠንቅቆ የተረዳ ፕሮፌሽናል ሠራዊት መገንባቱን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት ሲያደርጉ እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በተቋሙ የተሠራው ሪፎርም በርካታ ውጤቶች ለማስመዝገብ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ማስቻሉን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ በዚህ ደረጃ ብዛትና ጥራት ያለው የፕሮፌሽናል ሠራዊት ገንብታ አታውቅም ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ሀገሩንና ሙያውን የሚወድ የሚሰጠውን ግዳጅ በአነስተኛ ኪሳራ የመፈፀም ብቃት ያለው ሃይል ተገንብቷል ብለዋል።
ሠራዊቱ ሀገርን ከብተና ከማዳን ባለፈ የሀገራችንን ሰላም ፣ ብልፅግናና ዴሞክራሲን ለማረጋገጥ እየተደረገ ባለው ጥረት ያስመዘገባቸው ድሎች በታሪክ ሲዘከር የሚኖር መሆኑንም ጠቁመው፤ በተገኙ ድሎች ባለመኩራራት የተመዘገቡ ሁለንተናዊ ድሎች አጠናክሮ ለማስቀጠልና የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብም በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል።
በተሳሳተ ስሌት ወደጫካ ገብተው የነበሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች የሰላምን መንገድ በመከተል እጃቸውን ለሠራዊቱ መስጠታቸውን የገለፁት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ በተለያየ ቦታ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ፅንፈኞች ከመቼውም ጊዜ በላይ መዳከማቸውና የሰላምን ጥሪ ባልተቀበሉት ላይ የተጀመሩት የመለቃቀም ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።
በጦር ሜዳ ማሸነፍ ያቃታቸው የሀገርና የሕዝብ ጠላቶች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የውሸት ትርክት በመፍጠር በተቋሙ ፣ በአመራሩና በሠራዊቱ ላይ የሥነልቦና ጦርነት በመክፈት ለማጠልሸት ቢሞክሩም በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት በማጣታቸው ለሠራዊታችን የሚደረገው ሕዝባዊ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
በምድር ፣ በባሕር ፣ በአየር እና በሳይበር ሃይል የተደራጀው ሠራዊታችን ዘመኑ የደረሰበት የቴክኖሎጂና የውጊያ አቅም ላይ ለማድረስ መቻሉን የገለፁት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በተሳሳተ ስሌት ውጊያ ለመክፈት የሚሞክሩ ሃይሎችን በአነስተኛ ኪሳራና በአጭር ጊዜ ለመደምሰስ የሚያስችል ሁለንተናዊ ዝግጁነት መኖሩን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በማህበራዊ ትስስር ገጹ ዘግቧል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 19 ቀን 2017 ዓ.ም