ለሰዎች የደስታ ምንጭ በመሆን ሀሴት እናድርግ

የሰው ልጆች በአንድም በሌላም መልኩ መሙላት የሚፈልጉት ጉድለት አላቸው። ይሄ ጉድለታቸው ደግሞ በራሳቸው መንገድ የማይሞሉት፤ ይልቁንም የሰዎች ድጋፍና እገዛን የሚሹበት፤ ይሄን መሻታቸውን ሲያገኙም ጉድለታቸውን መሙላት የሚችሉበት፤ ጉድለታቸውን መሙላት ሲችሉም የደስታን ስሜት ማጣጣም የሚችሉበት የተሰናስሎ ዑደት ውስጥ የሚገቡበት ተፈጥሯዊ መንገድ አለው።

ከእዚህ አኳያ ዛሬ ላይ ብዙ ሰዎች በብዙ መልኩ ጉድለታቸውን በመሙላት ውስጥ የሚገኝ ደስታን ይሻሉ። ይሄ ደስታቸው ጤና ርቋቸው፣ ጤናን በማግኘት ውስጥ፤ ሰላም ርቋቸው፣ ሰላምን በማግኘት ውስጥ፤ ፍቅር ርቋቸው፣ ፍቅርን በማግኘት ውስጥ፤ ሀብት ርቋቸው፣ ሀብት ንብረት በማግኘት ውስጥ፣ ደጋፊ ናፍቋቸው፣ ደጋፊ በማግኘት ውስጥ፣ ፍትህ ርቋቸው፣ ፍትህ በማግኘት ውስጥ፤… የሚጎናጸፉት ሊሆን ይችላል።

እነዚህ ሁሉ የሰው ልጆች ደስታን የመናፈቅ ሁነቶች ምላሽ ሊያገኙ የሚችሉት ደግሞ፤ አንድም በእምነት ውስጥ በሚገኝ የተስፋ ጽናት ሲሆን፤ ከእዚህ ባሻገር ያለው ግን በራሱ በሰው ልጅ አጋርነት ላይ ተመስርቶ የሚመጣ ነው። የሰው ልል ደግሞ የምድራዊ ደስታው፣ አብሮነት ከሚኖረው፣ ከሚያወራው፣ ብዙ ማህበራዊና ሥነልቡናዊ ጉዳዮችን ከሚጋራው ከራሱ ከሰው ልጅ የሚያገኘው ነው።

ለሰዎች በፈጣሪው ከተሰጠው ትዕዛዝም አንዱ ይሄው ነው። ምክንያቱም ሰው ከሰው እንዲዋደድ፣ እንዲደጋገፍ፣ አንዱ ለአንዱ የደስታ ምንጭ እንዲሆን፤ አንዱ ለሌላኛው የዓለምን ፈተና መሻገሪያ አቅምና ስንቅ እንዲሆነው ታዟል። የትኛውም ፍጡር በምድር ላይ ባለው ዘመን ከራሱ ይልቅ ስለሌላው እንዲኖር፤ የራሱ ደስታ ሌሎችን በማስደሰት ውስጥ እንዲመነጭ ተደርጎ የተዋቀረ ነው።

ተፈጥሮን በወጉ ላጤነም፣ የትኛውም ፍጡር ስለ ራሱ መኖር አያብብም፤ አያፈራምም። ለምሳሌ፣ የትኛው ዛፍ ነው ፍሬውን ለራሱ የሚመገብ፤ የትኛው እንስሳ ነው ስጋውን አልያም ወተቱን ለራሱ የሚጠቀመው። ሁሉም ፍጡርና ተፈጥሮ የሚኖረው፣ የሚያብበው፣ የሚያፈራው ለሌሎች ነው። በተለይ ደግሞ ስለ ሰው ልጆች ደስታና መኖር ሲባል የተበጃጀ ነው።

አበቦች ቢፈኩ ሀሴትን የሚሰጡት ለሰው ልጅ ነው፤ እጽዋት ቢያፈሩ ለሰው ልጅ ምግብ ነው፤ እንስሳትም ቢሆኑ አገልግሎትና ጥቅማቸው ለሰው ልጆች ነው። ይሄ ሁሉ ጉዳይ ሲታሰብ ታዲያ፣ የሰው ልጅ ክቡርነትን፣ የሰው ልጅ ደስታና ምቾት ፈላጊነትን፣ አለፍ ሲልም የሰውን ልጅ በሌሎች ላይ ተጠግቶ የመኖርን፣ እንዲሁም የደስታና ሀሴቱ መሠረት ከራሱ ውጪ በሚመጡና በሚሆኑ ጉዳዮች ላይ የተመሠረተ መሆኑን አስረጂ ነው።

ይሄ ደስታ ደግሞ ዝም ብሎ በመሳቅ አልያም አምሮና ደምቆ በመገኘት ውስጥ የሚገለጥ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም። ምክንያቱም ደስታ ሲባል፤ ደስተኛነት አብሮ ስለሚነሳ ነው። ደስተኛነት ደግሞ ከላይ ከላይ የሚታይ ፈገግታና ውበት አይደለም። ይልቁንም ከውስጥ በሚመነጭ ልባዊ ስሜትና ሀሴት ላይ የሚመሠረት ነው። ይሄን የእውነት የሆነ ደስታ ደግሞ ከለጋስነትና ሰብዓዊነት፤ ለሌሎች ከመድረስ፤ ስለ ሌሎች ከመኖር፣ ስለ ሌሎች ራስን አሳልፎ ከመስጠት… እናገኘዋለን።

ምክንያቱም፣ ደስታ ከመስጠት የሚወለድ ነው። ስንሰጥ ለሌሎች ደስታን እንፈጥራለን፤ ሌሎች ደስ ሲላቸው ስናይ ደግሞ በተግባራችን እንረካለን፤ ሀሴትም እናደርጋለን። ስንሰጥ የምናገኝ፣ ስናስደስት የምንደሰት፣ ለሌሎች ሀሴት መሆን ስንችል ከፍ ያለ ሀሴትን የምናገኝ ከሆነ፤ እነዚህን ደስታ፣ እርካታና ሀሴት ልናገኝ የምንችለው ምን ስናደርግ ነው ብለን ማሰብና ማሰላሰል ይኖርብናል።

የመጀመሪያ የደስታና ሀሴት መፍጠሪያው አውድ ፍቅር ነው። ፍቅር የሰው ልጅ የደስታ አልፋና ኦሜጋ ነው። በፍቅር የማይወጣ ተራራ፣ የማይወረድ ቁልቁለት፣ የማይቀና መንገድ፣ የማይደለደል ገደል፣ የማይቀዘቅዝ ግለት፣ የማይፈነቀል አለት… አይኖርም። ሌላው ቀርቶ በፍቅር ኃይል ኢየሱስም ስለ ሰው ልጆች ሲል ራሱን አሳልፎ ሰጥቶስ የለ?።

እኛም ለሰው ልጆች ደስታን ፈጥረን፣ ሀሴትን ከምንጎናጸፍባቸው ጉዳዮች አንዱ ፍቅር ነው። ፍቅርን በመስጠት ውስጥ የሰዎችን ሀዘን ወደ ደስታ መለወጥ እንችላለን፤ የሰዎችን ስብራት መጠገን እንችላለን፤ ተስፋ ማለምለም እንችላለን፤ የሰዎችን የብቸኝነት መንፈስ በሙላት መተካት እንችላለን። ይሄን በማድረግ ውስጥ የእኛም ደስታ ይወለዳል፣ የእኛም ስብራት ይጠገናል፣ የእኛም ተስፋ ከፍ ይላል፤ የእኛም ጉድለት ሙሉ ይሆናል። እናም ፍቅርን በመስጠት ውስጥ ደስታን እናትርፍ።

ሌላው፣ ለሰዎች በመስጠት ደስታን የምታገኝበት ጉዳይ፣ ሰብዓዊነት ነው። ሰብዓዊነት ውስጡ ርህራሄ አለ። ሰብዓዊነት ውስጥ ስለ ሰዎች በጎ አስቦ በጎ ማድረግ አለ። ሰብዓዊነት ሰው ሆኖ የመፈጠርን ትርጉም ተገንዝቦ እንደ ሰው አስቦ መራመድና መሥራትን አስኳሉ አድርጓል። እናም ሰዎች እኛን ሲፈልጉ ብቻ ሳይሆን፤ እኛ ለሰዎች እንደምናስፈልጋቸው አምነን ሰብዓዊነታችንን ለሰዎች መግለጥ፤ ሰው የመሆናቸውን ጣዕም እንዲያጣጥሙም የድርሻችንን በመወጣት ለራሳችን ሀሴትን እንጎናጸፍ።

ፍቅርን መስጠት የቻለ፤ በሰውነት ልክ ተገኝቶ ሰብዓዊነትን መግለጥ የቻለ ማንነትን ስንላበስ ደግሞ፤ ሰዎችን በፍቅር ማገልገል፤ ስለ ሰዎች ቀና ማለት መትጋት፤ ስለ ሰዎች ደስታ መጨነቅ፤ ስለ ሰዎች ሰላም እንቅልፍ ማጣት፣ ስለ ሰዎች ፍትሕ ማሰላሰል፤… እንጀምራለን። እናም የሰዎችን ጉድለት ለመሙላትና ደስታን ለመፍጠር ጊዜያችንን፣ እውቀታችንን፣ ገንዘባችንን፣ ጉልበታችንን ሁሉ መጠቀም የዘወትር ልምምዳችን እናደርጋለን። እናም መስጠት ሌላው ስለ ደስታችን ምንጭነት ለሌሎች የምንሰጠው ጉዳይ ይሆናል ማለት ነው።

እነዚህ ለአብነት ያነሳኋቸው ነጥቦች በሰዎች ኑሮ ውስጥ አንዳች ረብ ያለው ነገር ለማኖርና ደስታን ለመስጠት አቅም ይሆናሉ ስል፤ እያንዳንዳቸው ተናጠላዊ ባህሪ አላቸው እያልኩ አይደለም። ይልቁንም አንዳቸው በአንዳቸው ውስጥ የሚኖሩም፣ የሚገለጡም ናቸው። ለምሳሌ፣ ፍቅርን ስለመስጠት ስናስብ፤ ሰው የመሆን ጉዳይ ግዘፍ ነስቶ ይከሰታል። ምክንያቱም፣ ፍቅር አንዱና ዋነኛው የሰውነት መገለጫ፤ የሰብዓዊነትም መከሰቻ መሰረት ነው።

በተመሳሳይ ፍቅር ሳይኖርህ አትራራም፤ ሰብዓዊነት ሳይጎበኝህ መስጠትም፣ መሰጠትም አትችልም። መስጠትና መሰጠት ደግሞ ያለ ስስት ከሙላት ብቻ ሳይሆን ከጉድለትም ላይ አጉድሎ መድረስን ይጠይቃል። ይሄን ለማድረግ ደግሞ ፍቅር በልብ ሊኖር፣ ሰብዓዊነትም በተግባር ሊገለጥ የግድ ይላል። ይሄ ሲሆን ከሙላታችን አንስተን፤ ከጉድለታችንም ቀንሰን ከራሳችን ይልቅ ስለ ሌሎች ማድረግን፤ በሌሎች ደስታ ውስጥ የራሳችንን ደስታ መፍጠርን ገንዘባችን እናደርጋለን።

እዚህ ጋ ልንዘነጋው የማይገባን ጉዳይ፤ የሰዎች ደስታን መፍጠር የምንችለው ሰዎች ሰው በሚያስፈልጋቸው ጊዜና ቦታ ላይ መድረስ ስንችል፤ ያጡትን እንዲያገኙ፤ የከበዳቸው እንዲቀልላቸው፤ የራቀው እንዲቀርብላቸው፤ ተስፋ በቆረጡበት ጉዳይ ዳግም ተስፋ እንዲያደርጉ ማድረግ በመቻላችን ውስጥ ነው። ምክንያቱም ይሄን አይነት ሰዎች ጉድለታቸውን በራሳቸው መሙላት ባለመቻላቸው የገቡበት ቁዘማ፣ የደረሰባቸው ስብራት፣ አልያም የተጫናቸው የሀዘን ድባብ አለ።

እኛም ሰው በመሆን በፍቅር ውስጥ በሚገለጥ መሰጠት ለእነዚህ ሰዎች ስንደርስ ሸክማቸውን አቅልለን እፎይታን፤ ጭንቀታቸውን አርቀን ደስታን እንሰጣቸዋለን። ይሄን ማድረጋችን ደግሞ መልሶ ለመንፈሳችን እርካታን፣ ለልባችንም ሀሴትን ያጎናጽፈናል። እናም ይሄን መሰል እርካታና ሀሴትን ወደ እኛ ማምጣት ከሻትን፤ ቀድመን ስለ ሰዎች ደስታ ራሳችንን እናስገዛ። ለዛሬው አበቃሁ፤ ሰላም!

በየኔነው ስሻው

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You