
ሰው የዘራውን ያጭዳል፤ የሠራውን ያገኛል፤ ሌላው ቀርቶ የቃሉን ፍሬ ይበላል፤ ይሉትን ዓይነት ብሂል በተለያየ አግባብ አድምጫለሁ። እነዚህ ይትባሕሎች ታዲያ እንዲያው በዘፈቀደ የሚባሉ አይደሉም። ይልቁንም ዛሬ በሳይንስ ተደግፈው ከሚከወኑ የፎክሎር፣ የባሕል፣ የሥነ ልቡና፣ የአንትሮፖሎጂ እና አጠቃላይ የሶሻል ሳይኮሎጂ ጥናቶች ባልተናነሰ መልኩ ማኅበረሰባዊ የሕይወት ኑረት ጥናት የፈጠራቸው እንጂ።
እነዚህ አባባሎች፣ በአንድ መቶ እና ከዚያ በላይ በሚሆን ገጽ ታግዘው ከሚቀርቡ የጥናት ሐቲቶች ይልቅ ጥልቅ እና ጥቅል ሃሳብን ይዘው የሚከሰቱ ናቸው። ምክንያቱም፣ አንድ ጥናት የአንድን ጉዳይ ምንነት፣ ትዕምርትና ትርጉም ለማስረዳት የሚጠቀመው የቃላት፣ የዓረፍተ ነገራት፣ የአንቀጾችና የጽሑፍ ክፍሎችን ለማስፈር የሚፈጅበት ወረቀት፤ ማኅበረሰባዊ የሕይወት ግኝት ቀመር የሆነው አባባል የሚጠቀመውን የቃል ምጣኔ እና የወረቀት ነጠላ መስመር ብቻ መመልከቱ በቂ ይመስለኛል። ከዚያ ውጭ ያለው የሐቲት ጋጋታ እንደመሆኑ ለአመክንዮ የማቀርበው ጉዳይ አይሆንም።
ለጉዳዩ ማራመጃ ብዬ ያነሳሁትን ጉዳይ ወደ ዋና ጉዳይነት እንዳይለወጥብኝ፤ እና በዚህ ላይ ማውራትም፣ መጻፍም ካለብኝ በሌላ ጊዜ መመለስ ስለምችል ወደ ዋናው ጉዳዬ ልመለስ። ይሄውም በርዕሴ እንዳስቀመጥኩት፤ በለሷን ያልጠበቀ ፍሬዋን አይበላም፤ በሚል ከነባሩ አባባል ተቀድቶ፣ የነባሩን ብሂል በአንድ አቅጣጫ ብቻ ከመመልከት በሁሉም ገጹ በማጤን ግንዛቤን ለማስያዝ ያነሳሁት ነው።
ብሂሉ “በለሷን የጠበቀ ፍሬዋን ይበላል” እንዲሉት ነው። ይሄ ማለት አንድን ነገር ሊጠቀሙበት፤ ሊገለገሉበት፣ ሊያገኙበት፤ ሊያተርፉበትና ሌላም ከዛ ነገር ማግኘት የሚሹትን ሁሉ እንዲያገኙ፤ ያንን ነገር በአግባቡ ሊጠብቁት፣ ሊንከባከቡት፣ ሊወዱትና ከፍ ያለ ሚናቸውን እንዲወጡ የግድ ይላል ማለት ነው። ይሄ ካልሆነ እና ያንን ነገር የማይጠብቁት፤ የማይንከባከቡት፤ የማይወዱት፤ ይልቁንም እንዲከስም የሚያደርጉት ተግባራት ላይ የሚሠማሩ ከሆነ፤ ከነገሩ ማግኘት የሚገባቸውን እንዳያገኙ የሚሆኑበት እድል እጅጉን የሰፋ መሆኑን የሚያመለክት ነው።
የበለሷ ጉዳይም ከዚህ አኳያ የሚታይ ነው። ምክንያቱም የበለሷን ፍሬ ለመብላት የሚቻለው፤ ለበለሷ የሚሆን ሥፍራን ከማዘጋጀት፤ በለሷን ተክሎ አስፈላጊውን እንክብካቤ ከማድረግ፤ ለፍሬ የሚሆነው አበባ በአበባነቱ እንዳይቀጭ፣ አበባውም ወደ ፍሬ ሲሸጋገር ፍሬው በእንጭጩ በተለያዩ ነገሮች እንዳይበላ በፍቅር ከሚደረግ ጥበቃ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ይሄን ማድረግ ሲቻል፤ በለሷ መልካም ፍሬን ትይዛለች፤ ባለ በለሱም ያንን መልካም ፍሬ ለማጣጣም ይችላል።
ከዚህ በተቃራኒው ከሆነ ግን፤ በለሷ ወይ በችግኟ ትቀጫለች፤ ወይ በአበባዋ ወቅት አበባዋን ታረግፋለች፤ ወይም በእሸት እያለች እሸቷን ወፎች ይበሉባታል። ይሄ ሲሆን ደግሞ ባለ በለሱ በለሷን በአግባቡ አልተንከባከበም፣ አልጠበቀም እና የበለሷን ፍሬ መብላትም፤ ማጣጣምም አይቻለውም።
ሀገርም እንዲሁ ናት። ልክ እንደ በለሷ። ዜጎቿም እንደ በለሱ ባለቤቶች ናቸው። በጠበቋት፣ በወደዷት፣ በተንከባከቧትና ባለሟት ልክ የሚጠቀሙባት። ባልጠበቋት፣ ባልተንከባከቧትና ወደው ዋጋ ባልከፈሉላት ልክም ችግርና መከራን የሚቀበሉባት ናት። ለዚህም ነው ሀገራቸውን ወደው ስለሀገራቸው እድገትና ለውጥ የሚተጉ ዜጎች በሁሉም ዘንድ በልፅገው፤ በተቃራኒው ሀገርን ከጥቅማቸው አንጻር ብቻ እየመዘኑ የሚራመዱ ዜጎች በሀገራቸው የረሃብ፣ የጦርነትና የስደት ኑሮን የኑሯቸው መገለጫ አድርገው የሚታዩት።
ዛሬ ላይ በምዕራቡ፣ በምሥራቁ፣ በመካከለኛው፣ በሩቅ ምሥራቁ፣ አፍሪካ፣ በአውሮፓ፣ በኢስያ፣… እየተባለ የዜጎች የኑሮ ሁኔታ፤ የሀገራት የእድገት ደረጃ ሲገለጽ የመለያየቱ ጉዳይም ከዚሁ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ዜጎች ሀገራቸውን ይሠራሉ። በሠሯት ሀገር መልሰው ከፍ ከፍ ይላሉ። በፍቅር ጠብቀውና ለእድገቷ ሠርተው ባሳደጓት ልክ ሀገራቸው መልሳ እያሳደገቻቸው የዓለም ገጽ ሲሆኑም፤ በጥቅማቸው ልክ እያሰቡ ብቻ ያላትን ለመቀራመት በተሯሯጡበት ልክም በገዛ ምድራቸው እርስ በርስ እየተገፋፉና እየተዋጉ የድህነትና ስደት አብነት ሲሆኑም የሚታዩት፤ ሕዝቦች እንደ በለስ የሆነችውን ሀገራቸውን በጠበቋትና በሠሯት ልክ ስለሚገለጡ ነው።
እስኪ ከዓለምም፣ ከአህጉርም፣ ከቀጣናም ሰብሰብ ብለን እንደ ሀገር ኢትዮጵያችንን እና ራሳችንን በዚሁ ማሕቀፍ ውስጥ እንመልከት። እኛ ኢትዮጵያውያን ስለ ሀገራችን ከፍታ፤ ስለ ራሳችን ገጽታ አስበን በሠራንባቸው አያሌ ዘመናት፤ ኢትዮጵያን ገናን፣ ኢትዮጵያውያንንም ኃያል ያደረጉ ፍሬያማ ተግባራትን ከውነናል። ዛሬም ድረስ በቀደሙት ሀገር ወዳድ ትጉህ አያት ቅድመ አያቶቻችንን ዘመን አይሽሬ ዐሻራዎች ለዓለም አብነታችንን እየገለጥን ለመዝለቅ ችለናል።
ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ፣ ሀገርን ሳይሆን ቡድናዊ እና ግለሰባዊ ፍላጎትን ማዕከል አድርገን በተንቀሳቀስን ቁጥር፤ ኢትዮጵያን እያሳነስን እና እያኮሰስን፤ ለራሳችን የሚሆን የማያሳፍር ታሪክ ግብር አልባ እየሆንን፤ ግዛት እየቀነስን እና የሀገር ሉዓላዊነትን አሳልፈን እየሰጠን፤ ከዚህም በላይ በሕብር ከደመቀው አንድነት ይልቅ የተገንጣይነት እሳቤን እየዘራን፤ ሀገርን ከመጠበቅ ይልቅ በሀገር ላይ ጦር እያነሳን ስንወጋ ስናደማ የኖርንባቸው አጋጣሚዎችም የበዙ ናቸው።
ዛሬም ቢሆን እነዚህ ትይዩ፣ ግን ተጻራሪ የሆኑ መንገዶቻችን አብረውን ዘልቀዋል። ለዚህ ደግሞ ያለፉት ስድስት ዓመታት ሀገራዊ መንገዳችንን እንመልከት። በአንድ በኩል የሕዝብ ብሶትና ጥያቄ አድጎ እምቢተኝነት የወለደውን ለውጥ የሚመራው መንግሥት እያደረገ ያለው “በለሷን የመጠበቅና ለፍሬ የማብቃት” ዓይነት ሀገርን ጠብቆና አበልጽጎ ለትውልድ የማሸጋገር እልህ አስጨራሽ ጉዞ አለ።
በሌላ በኩል ከግማሽ ምዕተ ዓመት የተሻገረ እሳቤን የሙጥኝ ያለ፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት ደግሞ እሳቤውን ወደ ተግባር የመለወጥ ቅዠት ውስጥ በመግባት ሀገርን ለጦርነት፤ ወገንን ለእልቂትና ስደት፤ ኢኮኖሚንም ለድቀት እየዳረገ ያለ “ሕወሓት ወለዱ አጅዳ” አለ። እነዚህ በሁለት ተጻራሪ መንገዶች እየተጓዙ፣ አንድን ሀገር በተለያየ መንገድ ለማራመድ እንቅልፍ ያጡ ኃይላት ታዲያ፤ የበለሷን ፍሬ ከመብላት አኳያም የሚጓዙበት አቅጣጫ ለየቅል ሆኖ እናገኘዋለን።
ኢትዮጵያውያን እንደ ሕዝብ እና መንግሥትም እንደ መንግሥት፣ በፍጹም የሀገርን መውደድ ስሜት ውስጥ ሆነው፤ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና፣ ክብርና ሉዓላዊነት፤ ለኢትዮጵያውያንም ዘላቂ አብሮነትና ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነት ቀን ከሌት እንቅልፍ አጥተው በጋራ ይሠራሉ። በመደመር መርህ ተቃኝተውም ትናንት የነበሩ ችግሮችን ለማረምም በጋራ የሚመክሩበትን አውድ ፈጥረዋል።
የቀደሙ መልካም ጅምሮችን በማጽናትና በማላቅ እሳቤም አያሌ የታሪክ ዐሻራዎችን አልቀው በማደስ ከወቅቱ ጋር በሚጣጣም መልኩ ለዓለም በመግለጥ ላይ ተጠምደዋል። አዳዲስ እሳቤዎችን፣ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በኢትዮጵያ ምድር በመተግበርም ሰው ተኮር ሥራዎችን እያከናወኑ፤ ሀገር ከዛሬ ባሻገር ላለው ትውልድ ያማረ ፍሬን እንድትለግስ ያለመታከት በታላቅ ትጋት እየተረባረቡ ይገኛል። ይሄን ዓይነት መንገድ ደግሞ በለሷን በብዙ አፍርታ ለባለበለሶቹ የሚበቃ ምርት እንድትሰጥ የሚያስችል ነው።
ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ፣ በለሷን ሳይሆን ፍሬዋን ብቻ ከመሻት፤ ከሃምሳ ዓመት በተሻገረው ያረጀ እሳቤ ውስጥ እየዳከሩ ላሉበት ዓላማ መሳካት የሚሆን ኢኮኖሚያዊ አቅምን መፍጠሪያነት ከመፈለግ፤ ነገ ለሚሹት ሀገር የመሽረፍ ቅዠት መልሰው ራሷኑ የሚወጉበትን ጡንቻ ለማፈርጠም የሚያገለግል የጦርም፣ የዲፕሎማሲም አቅም ለመሰብሰብ መጠጊያ ከማድረግ፤… አኳያ የሚገለጡ “ሕወሓታዊ አንጃዎችና ግብረ አበሮቻቸው” አካሄዶች አሉ።
እነዚህ አንጃዎች ትናትን በነፃነት ስም፣ ብዙ አስር ሺህ ወጣቶችን ዋጋ አስከፍለዋል። ሀገርን ወግተው የደም ምድር አድርገዋል። በሂደትም ሀገር አስገንጥለው፤ የሕዝቦችን ሕብረ ብሔራዊ አንድነት በሚሸረሽሩ ተግባራት ላይ ተሰማርተው፤ የነገ ሕልማቸውን ወደ እውነት ለመቀየር የሚያደርጉትን መንገድ ለመጥረግ ሞክረዋል። የመንገድ ጥርጊያቸውን ሳይቋጩ ሳያስቡት የደረሰባቸውንና የሕዝብ ማዕበል የፈጠረውን ለውጥ መቋቋም ቢሳናቸውም፣ ዳግም ሌላ ጦርነት፤ ዳግም ሌላ እልቂት፤ ዳግም ሌላ የደም መሬት ፈጥረው እንደ ሀገር ከፍ ያለ ዋጋን አስከፍለዋል።
ችግሮችን በሰላም መፍታት ሞት መስሎ የሚታያቸው፤ ከዚህም በላይ ሰላም ለሕዝቦች እፎይታን የሚሰጥ ቢሆንም፣ ለእነርሱ እሳት ሆኖ የሚበላቸው ስለሚመስላቸውም፤ (እውነቱም ይሄው በመሆኑ)፤ ከሁለት ዓመታት ጦርነት በኋላ በፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት እንዳይተገበር በቻሉት አቅም ሁሉ እየተቅበዘበዙ ይገኛል። ለዚህ ደግሞ በስምምነቱ እንዲፈጸሙ ግዴታ የተቀመጠላቸውን ጉዳዮች ጨምሮ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ በማድረግ ፖለቲካዊ ትርፍ ማግኛ አድርገው እየተጠቀሙባቸው ይገኛል።
በተመሳሳይ መልኩም፣ ዛሬ ላይ እነዚህ ሕወሓታዊ አንጃዎች ኢትዮጵያን ለጥቅማቸው የሚኖሩባት እንጂ ወድደዋት፣ ስለ ክብሯ ዋጋ ከፍለውላት የመኖር ፍላጎት እንደሌላቸው የሚያሳዩ በርካታ ተግባራትን እየፈጸሙ ይገኛል። ለምሳሌ፣ ቀደም ሲል ሕወሓት እና መንግሥት የሚል ትርክት ነበራቸው። ይሄ ትርክታቸው መንግሥት የሚሉት የፌዴራል መንግሥትን ቢሆንም፤ ሕወሓትን ሲጠቅሱ ግን የሀገረ ትግራይ መስራች ድርጅትነቱን ለማስረጽና ከዚሁ ጋር አንጃው ራሱን እንዲያስተሳስር ለማድረግ በማለም ነበር።
ይሄን መነሻ በማድረግም ነበር፣ እንደ አንድ የክልል ፓርቲ ሳይሆን፤ እንደ አንድ ሀገር መንግሥት እና ገዢ ፓርቲ የውጭ ግንኙነቶችን ለማድረግ፤ በተለያዩ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ መግለጫዎችን ለማውጣት ሲጣጣር የታየው። እነዚህ ጉዳዮችም በተለይ የሰሜኑ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት እና በጦርነቱ ወቅት በስፋት ይስተዋሉ ነበር።
ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ የጊዜያዊ አስተዳደር በመቋቋሙ ምክንያት እነዚህ ተግባራት ተገትተው ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ሕወሓታዊ አንጃው በዚህ መልኩ መቀጠሉ የኖረ ቅዠቱን የሚያመክን፤ ሰላማዊ አውድ መፈጠሩም ሕልውናውን የሚፈትን መስሎ ስለታየው፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ወደ ማፍረስ፤ የነበረ እኩይ ግብሩንም ወደ መከወን ተሸጋገረ። እናም ቀድሞ ሕወሓት እና የኢትዮጵያ መንግሥት ይል የነበረውን ትርክት፤ ትግራይ እና ኢትዮጵያ በሚል ተክቶ፤ አንድን ክልል ከታላቋ ሀገር ጋር ወደ ማነጻጸር ተሸጋግሮ ሀገር የመሆን ቅዠቱን በቃል ደረጃ የመተረክ አካሄድ ላይ ደርሷል።
ይሄም ብቻ አይደለም። የሀገርን ሉዓላዊነት በሚጋፋና ባላከበረ መልኩ ከውጭ የጥፋት ኃይሎች ጋር ወደመነጋገርና ወደመተባበር የሚሸጋገርበትን አውድ እየፈጠረ፤ የውጭ ዲፕሎማሲንና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ መግለጫን ወደ ማውጣት አባዜው እየተመለሰ ይገኛል። በግልጽም ኢትዮጵያን ለመውጋት፤ ኢትዮጵያን ለመገንጠል፤ ኢትዮጵያውያንን ለመበታተን በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ኢትዮጵያን ጠልነቱን እያሳየ ነው።
በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ሥልጣኔና ሀገረ መንግሥት ግንባታ ብሎም፣ ሀገረ መንግሥቱ ፀንቶ እንዲቆይ በማድረግ በኩል ከፍ ያለ ሚና ያለውን የትግራይ ሕዝብም በአስገዳጅ ሁኔታ ለዚህ እኩይ ዓላማው መሳካት እንደ መያዣ ሊጠቀመው እየሞከረ ይገኛል። ይሄን የሚቃወሙ ወጣቶችንና የኅብረተሰብ ክፍሎችንም በማፈን፣ በማሰር፣ አለፍ ሲልም በመግደል ጭምር ሕዝቡን በማስፈራራት የሃሳቡ ተገዥ እንዲሁን ባለ በሌለ አቅሙ እየተፍጨረጨረ ይገኛል።
በፌዴራል መንግሥት ለሕዝብ ልማት እንዲውል የሚመደብን በጀትም ለዚህ እኩይ ዓላማው ማስፈጸሚያ እንዲውሉ ለሚቀልባቸው ኃይሎች እያዋለም ይገኛል። ይሄ አልበቃ ብሎት፣ ለተፈናቃዮችና ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሚላክን ሰብዓዊ ድጋፍ መያዣ በማድረግ፣ ሕዝቡ እኩይ ዓላማውን በሃሳብም፣ በገንዘብም፣ በመስዋዕትነትም እንዲደግፍ እያስገደደው ይገኛል።
ይሄ ሕወሓታዊ አንጃ በእነዚህ እና ሌሎች ተግባራቱ ሲመዘን፤ በአንድ በኩል የኖረ ቅዠቱን ለመፈጸም እየተውተረተረ ስለመሆኑ መረዳት ይቻላል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ስሟን እንኳን ለመጥራት የሚጠየፋትን፤ ሰንደቅ ዓላማዋን ከጎኑ ለማኖር የማይሻትን ኢትዮጵያን፤ እንደ ሀገሩ ቆጥሮ ሳይሆን፤ ጥቅሟንና በጀቷን ፈልጎ ብቻ ያለባት ስለመሆኑ መገንዘብ ይቻላል።
በመሆኑም ይሄን መሰሉ የሕወሓታዊ አንጃ አካሄድ፤ በለሷን ያልጠበቀ ፍሬዋን አይበላም፤ እንዲሉት ዓይነት በመሆኑ፤ ካልጠበቃትና ከማይወድዳት ሀገር ፍሬን ሊጠብቅ አይገባውም። በመሆኑም ከእኩይ መንገዱ ሊታረም፤ ሀገራዊ አንድነትንና ሉዓላዊነትን ከሚጋፋ እሳቤት እንቅስቃሴው ሊገታ፤ በሕዝብ ጉሮሮ ላይ ቆሞ በሕዝብ የመቆመር አካሄዱን ሊለውጥ፤ እንደ ሀገር ኢትዮጵያን፣ እንደ ሕዝብም ኢትዮጵያውያንን አክብሮ ከኖረ የእርስ በእርስ ጦርነት ቆስቋሽነት አቅጣጫው ሊመለስ የተገባ ነው።
ለዚህ ደግሞ በለሷን ሳይጠበቅ ፍሬዋን መመኘትም፣ መጠበቅም ተገቢ አይደለም፤ ቢመኙም ማግኘት አይቻልም። እናም አንጃው እንደ አንጃ ይሄን ቆም ብሎ ሊያስብ፤ የትግራይ ወጣትና ሕዝብም በቃህ ሊለው፤ መላው ኢትዮጵያውያንም እውነቱን ተገንዝበው ሊያጤኑት፤ መንግሥት እና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻዎችም ከወዲሁ ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉት ዓይነት መፍትሔን ሊያዋልዱ የተገባ ነው። ለዛሬው አበቃሁ፤ ሰላምን ለሀገራችን፤ ፍቅርና አብሮነትም ለሕዝባችን ተመኘሁ።
ማሙሻ ከአቡርሻ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም