
– እውቅናውን በአዝርዕት ዘርፍም ለመድገም በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል
አዲስ አበባ፡– በእንስሳት ዘርፍ የተገኘውን እውቅና በአዝርዕትም ዘርፍ ለመድገም መሥራት እንደሚያስፈልግ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን የእንስሳት ምርትና ግብዓት ጥራት ምርመራ ላቦራቶሪ አክሪዴቴሽን የዕውቅናና የምሥክር ወረቀት ርክክብ ትናንት ሲካሄድ እንደገለጹት፤ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በዘርፉ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማምጣት በኩል አበረታች ውጤቶች ማስመዝገብ ተችሏል። በእዚህ ሂደት ውስጥም የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ከዕድሜው በላይ ሠርቷል።
በእንስሳት ዘርፍ የተገኘውን እውቅና በአዝርዕትም ዘርፍ ለመድገም መሥራት እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ የተገኘውን እውቅና በመጠቀም ዘርፉን ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ ይገባልም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ለዓለም የንግድ ድርጅት አባል ስትሆን፤ የግብርና ምርቶችንና ግብዓቶችን ጥራትና ደህንነት መጠበቅ ትልቁ መስፈርት መሆኑን ያመላከቱት ሚኒስትሩ፤ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እና የግብርና ምርት ወደ መዳረሻ ሀገራት ለመላክ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
የተሻሻለው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ለምርት ጥራትና ቁጥጥር ትኩረት መሰጠቱን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ ምርት ማምረት ብቻውን በቂ ስላልሆነ የግብርና ምርቶችን ጥራትና ደህንነት የጠበቀ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ከውጭ የሚገቡ የተለያዩ የእንስሳት ተዋጽኦዎችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተሠራ ስለመሆኑ ያነሱት ሚኒስትሩ፤ የሌማት ትሩፋት መንደሮች ጥራቱንና ደህንነቱን የጠበቀ ምርት ማምረት አለባቸው ብለዋል። የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ በበኩላቸው፤ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ውስጥ የኢትዮጵያን ግብርና ምርት ተወዳዳሪ በማድረግ ከንግድ ቀጣናው የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን በምታደርገው ጥረት ውስጥ የግብርና ምርቶችና ግብዓቶች ጥራትና ደህንነት ቀዳሚ መስፈርት በመሆኑ መስፈርቱን ለማሟላት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በሀገር ውስጥ ጥራትና ደህንነቱ የተጠበቀ የግብርና ምርትና ግብዓት እንዲኖር በምርት የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር ተገቢው ጥረት እየተደረገ እንደሚገኘም ጠቁመዋል።
ተቋማት አክሬዲቴሽን እውቅና ማግኘታቸው የተሻሉና ተገልጋዮችን ለማርካት የሚስችላቸውን የአሠራር ሥርዓት እንዲከተሉና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ተመላክቷል፡፡
ማዕከሉ እውቅና ያገኘው በፋርማሲዩቲካል ፍተሻ ወሰን በ5 የፍተሻ ባሕሪያት ዘዴ፣ በኬሚካል ፍተሻ ወሰን በ2 የፍተሻ ባሕሪያት ዘዴ እንዲሁም በማክሮ ባዮሎጂ ፍተሻ ወሰን በ6 የፍተሻ ባሕሪያት ዘዴ መሆኑ ታውቋል።
ዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም