የኃያላኑ የኢኮኖሚ ጦርነት ለአፍሪካ የሚኖረው እድልና ስጋት

የኃያላኑ ሀገራት የንግድ ጦርነት በተጧጧፈበት በእዚህ ወቅት የአፍሪካ ታዳጊ ሀገራት እንዴት ይሆናሉ? የሚለው ጥያቄ ተገቢ እና ወቅታዊ ነው፡፡ የዓለምን ኢኮኖሚ 43 በመቶ የሚሆነውን ጠቅልለው የያዙት አሜሪካ እና ቻይና የንግድ ጦርነታቸውን ታሪፍ አንዱ በሌላው ላይ በተደጋጋሚ በመጣል ፍጥጫውን አጋግለውታል፡፡ ምሁራንም ይሄንን አካሄድ ለሁለተኛው የዓለም ኢኮኖሚ ውድቀት ሊዳርገን ይችላል ሲሉም ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡

ለምን የአሜሪካኑ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእዚህ ልክ በቻይና ላይ የታሪፍ ናዳ ጣሉ? የኃያላኑ የኢኮኖሚ ጦርነት ለአፍሪካ ያለው እድልና ስጋት ምንድነው? በሚለው ላይ የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ቆንጠንጢኖስ በርሄ (ዶ/ር) እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ እና በአውሮፓ ኅብረት ፕሮጀክት ለኢትዮጵያ መንግሥት ለሚሰጡት ድጋፍ ቡድን መሪ የሆኑትን ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር) አነጋግረናል፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ ቻይና ለአሜሪካን በዓመት 440 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሸቀጦችን ትሸጣለች፡፡ በምላሹም 145 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ቁስን ከአሜሪካ ትሸምታለች፡፡ ይሄም በኢኮኖሚስቶቹ ቋንቋ “ትሬድ ዲፊሲት” ወይም የንግድ ገበያ አለመመጣጠንን አስከትሏል፡፡ ለእዚህም ነው ፕሬዚዳንት ትራምፕ 145 በመቶ ታሪፍን በቻይና ምርቶች ላይ በመጫን ከቻይና የሚገቡ እቃዎችን ቁጥር ለመቀነስ የፈለጉት፡፡ ቻይናም በምላሹ 125 በመቶ ታሪፍ በአሜሪካ ምርቶች ላይ ጥላለች፡፡ ይህ የታሪፍ ጉዳይ እንደየአቅማቸው የተለያዩ የአፍሪካ እና የእስያ ሀገራት ላይ መጣሉን ቆንጠንጢኖስ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡

አሜሪካም ይሄንን ታሪፍ መጣል ያስፈለጋት ከተለያዩ ሀገራት የምታስገባው ቁስ ከምትልከው በማነሱ እና የሀገር ውስጥ ምርቶቿን ማሳደግ በመፈለጓ ነው፡፡ ከሌሎች ሀገራት የሚመጣውን ምርት አስቁማ የአቅርቦት ፍላጎቷን በአጭር ጊዜ ልታሳካው ትችላለች? የሚለው ጥያቄ ተገቢ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡

ቻይና የቦይንግ አውሮፕላንን ለመግዛት የተስማማችውን ውል ሰርዛለች፡፡ ቦይንግን ሊተካ የሚችል የአውሮፕላን ምርት ማምረትም ጀምራለች፡ የቦይንግ አውሮፕላንም አብዛኛው መዳረሻው እስያ ሀገራት ነው፡፡ እነዚህም ሀገራት በታሪፉ ተቆጥተው ከአሜሪካ ምርቱን መግዛት ካቆሙ ለአሜሪካ ከባድ ኪሳራ ነው። በተጨማሪም ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ የታሪፍ ተጠቂ ስለሆኑ ከቻይና ጎን ቆመዋል፡፡ ይሄም ለቻይና ትልቅ እድል ነው ይላሉ፡፡

የአፍሪካ ሀገራት የአጎዋ ተጠቃሚ ነበሩ፡፡ በእዚህም ወደ 7ሺህ የሚሆኑ ቁሶች ወደ አሜሪካ ይገባሉ። ለአብነት ደቡብ አፍሪካ ብቻዋን 25 ቢሊዮን ዶላር በዓመት ትልካለች፡፡ ነገር ግን የአሜሪካኑ ፕሬዚዳንት መስከረም ላይ ይህ እንዲቆም እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

አፍሪካ ለአሜሪካ በብዛት የምትልከው ቅመማ ቅመሞች፣ ጥራጥሬዎች እና ማዕድናት ነው፡፡ በታሪፉ ምክንያት የአሜሪካንን ገበያ አጥታለች ማለት የሌላ ሀገር ገበያ ታጣለች ማለት ግን አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ኢትዮጵያም ወደ አሜሪካ ቡና ትልካለች፡፡ የሚፎካከሯት ሀገራትም ብራዚል እና ቬትናም ናቸው። እነሱ በጣም የታሪፍ ጫና ተደርጎባቸዋል፡፡ ከእዚህ አኳያም ኢትዮጵያ ከቡና አንጻር ብዙ ስጋት ላይኖርባት ይችላል፡፡ አበባ ምርት ላይ ግን ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል ነው ያሉት፡፡

ለአፍሪካ ከአውሮፓውያን የተደረገላቸው ድጋፍ ትንሽም ቢሆን ፈቀቅ አላደረጋቸውም፤ ቻይና ግን በአፍሪካ ውስጥ ብዙ ግድቦችን፣ ድልድዮችን እና የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸውን ፕሮጀክቶች በመሥራታቸው አሁንም ደግሞ በተጣለባቸው የታሪፍ ጭማሪ ምክንያት የበለጠ ወዳጅነታቸው ሊጨምር ይችላል የሚል ግምት እንዳለም ምሁሩ ይናገራሉ፡፡

ቻይና እንደ አጎዋ አይነት አሠራር ጀምራለች፡፡ በተጨማሪም የአፍሪካ የነጻ የንግድ ቀጣና ላይ መግባት ከቻለች አሜሪካንን ከንግድ ጨዋታው ታስወጣታለች። በአጠቃላይ የንግድ ጦርነቱ ለአፍሪካ ሀገራት እድል እና ስጋት ስለሚኖረው ሀገራቱ በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ ጥናት አካሂደው ጫናውን ሊከላከሉ የሚችሉበትን መንገድ መፈለግ እንደሚገባቸው ቆንጠንጢኖስ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዓለም ላይ የሚደረጉ የንግድ ሥርዓት ላይ አሜሪካን እና ቻይና የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዙ ይናገራሉ። በእነዚህ ኃያላን የንግድ ጦርነት እንደ አፍሪካ ሀገራት ያሉ ታዳጊ ሀገሮች እድልም ፣ ስጋትም ይኖርባቸዋል፡፡ ከስጋቱ አንዱ የዋጋ ንረት ሊከሰት ይችላል፡፡ ማለትም የቻይና ምርት ወደ አሜሪካን ሀገር ሲገባ ውድ ይሆናል፤ ይሄንንም ተከትሎ በቻይና ሀገር የሚመረቱ ምርቶች ላይም ጭማሪ ሊታይ ይችላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ብቻ ከ10 እስከ 30 በመቶ ጭማሪው ታይቷል፡፡ ይሄ ጭማሪ ደግሞ በእዚያው ሀገር ላይ ብቻ የሚያበቃ አይሆንም። ከአሜሪካ ምርቶች ወደ ኢትዮጵያም ሆነ ወደ ሌሎች ሀገራት ሲገቡ ጭማሪው እንደተጠበቀ ይሆናል፡፡

የአሜሪካ ትላልቅ ኩባንያዎች መገኛቸው ቻይና ነው፡፡ ሁለቱም ከፍተኛ የቴክኖሎጂ አምራቾች ናቸው። በእዚህ የንግድ ጦርነት ሳቢያ የሚያመርቷቸው ምርት       ላይ የዋጋ ጭማሪ ይከሰታል፡፡ ኢትዮጵያም ትልቋ የንግድ አጋሯ ቻይና ስለሆነች የችግሩ ሰለባ ልትሆን ትችላለች። ከኢትዮጵያ የሚላኩ ምርቶች ከሌሎች ሀገራት በሚገቡ ግብአት የሚመረቱ (ፕሮሰስ) የሚደረጉ ስለሆነ የወጪ ንግዳችንም ፈተና ሊገጥመው እንደሚችልም ይናገራሉ።

በሌላኛው ጎን ደግሞ ኢትዮጵያ እና አፍሪካ ከእዚህ የንግድ ጦርነት ሊያተርፉ ይችላሉ የሚሉት ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር) ፤በሁለቱ ሀገራት የሚታየው ታሪፍ ጭማሪ ወደ ኮታ የሚገባ ከሆነ ከቻይና ወደ አሜሪካ በውድ ሲገቡ የነበሩ ምርቶች አማራጭ የገበያ መገኛቸውን አፍሪካ ያደርጋሉ፡፡ ሀገራቱ ደግሞ ምርቶቹን እንዲጠቀሙ የዋጋ ቅናሽ ሊደረግባቸው ይችላል፡፡ ኢትዮጵያም በአፍሪካ የግዙፍ ኢኮኖሚ እና የብዙ ሕዝብ መገኛ በመሆኗ ለምርቶቹ የተሻለ የገበያ መዳረሻቸው ትሆናለች ነው ያሉት፡፡

የአፍሪካ መንግሥታትም ለሁለቱ ኃያላን ሀገራት ወገንተኛ ሳይሆኑ ስጋቶቹን እና እድሎቹን በሚገባ በማጤንና በማስላት ሀገራቸውን ተጠቃሚ ለማድረግ ሊሠሩ ይገባል፡፡ ጦርነቱም የሀገራቱ ብቻ ሳይሆን የሁለት ርዕዮተ ዓለም ጦርነት በመሆኑ ጥቅማቸውንም ከሚያከብር ፖሊሲ ጋር ብቻ ሊወግኑ እንደሚገባም ጉቱ (ዶ/ር) አሳስበዋል፡፡

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You