
ኢትዮጵያ ለእንስሳት ሀብት ልማት የሚስማማ አየር ንብረት፣ ለንብ ማነብ አመቺ የሆነ ሥነ-ምህዳር፣ ሥጋ፣ እንቁላል አትክልትና ፍራፍሬ ማልማት የሚያስችል ምቹ ተፈጥሮ ያላት ሀገር ናት። ይሁን እንጂ ይህንን አቅም አልምቶ ለምግብ ዋስትናም ሆነ ለገበያ ከመጠቀም አንጻር ግልፅ ድክመት ይስተዋላል፡፡
ባለን ሀብታችን በሚገባው ልክ ተጠቅመንበታል ብለን አፏችንን ሞልተን የምንመሰክርበት ደረጃ ላይ መድረስ ላይ ብዙ ይቀረናል። ሆኖም ግን አሁን ባለው ጅምር ያለንን ሀብት ተጠቅመን አትራፊ መሆን እንደሚቻል በሌማት ቱሩፋት የታየው ውጤት አንዱ ማሳያ መሆኑን ማንሳት የግድ ይለናል።
የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚጠቁመው በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው ዓመታዊ የወተት ምርት 7 ነጥብ 1 ቢሊዮን ሊትር ሲሆን ዓመታዊ የወተት የነፍስ ወከፍ ፍጆታ ደግሞ ከ66 ሊትር አይበልጥም። ይህም ለአንድ ጤነኛ ሰው በዓመት ከሚያስፈልገው 200 ሊትር አንጻር በእጅጉ ያነሰ መጠን ነው፡፡ ኢትዮጵያ የተቀነባበሩ የወተት ውጤቶችን ከውጭ ለማስገባት በየዓመቱ በአማካኝ ከ25 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደምታወጣ መረጃው ይጠቁማል፡፡
በተያዘው የሌማት ቱሩፋት የአራት ዓመታት መርሃ-ግብር ዓመታዊ የወተት ምርትን ከስድስት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ሊትር ወደ 11 ነጥብ 7 ቢሊዮን ሊትር የማድረስ ግብ የሰነቀ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ካሉ እንቁላል ጣይ ዶሮዎች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት በአማካኝ በዓመት 40 እንቁላል ብቻ የሚጥሉ ሲሆን፤ በተለያዩ ሀገራት ግን በዘመናዊ የዶሮ ርባታ አማካኝነት በዓመት ከአንድ ዶሮ 270 እንቁላል ማምረት እንደሚቻል መረጃዎች ያሳያሉ።
የዶሮ ሥጋ ዓመታዊ ምርትን ከ90 ሺህ ወደ 240 ሺህ ቶን እንዲሁም የማር ምርትን ከ147 ሺህ ወደ 296 ሺህ ቶን ከፍ ለማድረግ ነው ሰፊ ሥራ የተጀመረው፡፡ ከዚህ አንጻር የወተት ምርታማነት ለማሳደግ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ላይ በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው፡፡ የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ እንዳስታወቀው፤ በበጀት ዓመቱ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ለመሥራት ታቅዶ ፤ በዘጠኝ ወራት አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ማሳካት ተችሏል፡፡
አጠቃላይ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሊትር ወተት ለማምረት ታቅዶ፤ በዘጠኝ ወራት 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ሊትር መሰብሰብ ተችሏል፡፡ ለተገኘው ውጤት እንደ ክልል በሌማት ትሩፋት የሚሳተፉ አካላት፣ አመራሩ እና አርሶ አደሩ ያሳዩት ቁርጠኝነት ተጠቃሽ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ እንዲሁም እንደ ክልል በበጀት ዓመቱ መቶ ሚሊዮን የዶሮ ጫጩቶች ለማሰራጨት ታቅዷል፡፡
እስከ ሶስተኛው ሩብ ዓመት ወጣቶችን፤ ሴቶችን፤ አርሶ አደሮችን በማደራጀት እና በዶሮ ልማት የተሠማሩ ባለሀብቶችን በማሳተፍ 63 ሚሊዮን የእንቁላል እና የሥጋ ጫጩቶች ተሠራጭተዋል፡፡ ከእንቁላል ምርት አንጻር በበጀት ዓመቱ አራት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ለማምረት ታቅዶ፤ በዘጠኝ ወራት ሶስት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ተመርቷል፡፡
የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ዋና ዓላማም የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥና ሀገራዊ ክብርን ማስጠበቅ ነው። ተረጂ የሚለው ቅጥያ መታወቂያችን ተፍቆ ራስን መቻል ነው። በተለይ ለሰውነት ጤና፣ ለአእምሮ እድገትና ብልፅግና አስፈላጊና ወሳኝ የሆኑ ምርቶችን በጓሮ አምርቶ የቤተሰብን የምግብ ገበታ በተመጣጠነ ምግብ መሙላትን ያለመ ነው።
የሥነ ምግብ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ የተመጣጠነ ምግብን መመገብ ሌላው ቀርቶ ቀና አስተሳሰብ፣ አርቆ ማሰብን፣ መልካምነትን ያሳድጋል። ለአዕምሮ እድገትና ብልፅግና ጠቀሜታ ያላቸው እንደ ወተት፣ እንቁላል ያሉ ምግቦችን ሕፃናት ከልጅነታቸው ጀምሮ እንዲያዘወትሩ ማድረግ በራሱ ሕፃናቱ ለትምህርት ብሩህ የሆነ አዕምሮን ያዳበሩ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል። በትምህርት አቀባበላቸው፣ በፈጠራ ሥራዎች ብቁ ሆነው እንዲያድጉ ያደርጋል። በአጠቃላይ የመቀጨጭና የመቀንጨር ችግርን ይቀርፋል።
ይሄ በእያንዳንዱ ሰው ጤና ላይ የሚያበረክተው የራሱ አስተዋጽኦ ቢኖረውም እንደ ሀገር ደግሞ ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ ነው። በትንሹ ጤናማ ዜጎችን ማፍራት ያስችላል። በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚመጣን በሽታና ለሕክምና የሚውለውን የመድኃኒት ግዢን ያስቀራል። ይሄንና መሰል ችግሮችን በመቅረፍ ረገድም ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል።
ከኢኮኖሚ አንጻር ሲቃኝ ደግሞ ለቤተሰብ ከሚመረተው ምርት ትርፉን ወደ ገበያ ሲወጣ ደግሞ የኢኮኖሚ ጠቀሜታው በዛው መጠን ያድጋል። ይሄም እንደ ሀገር በቤተሰብ ደረጃ የተጀመረውን የሌማት ቱሩፋት ከዚሁ ጋር ተያይዞ ያለውን አስቀድሞ በሽታን መከላከል የጤና ፖሊሲን የማሳልጥ አስተዋጽኦ እንዳለው ማሳያ ነው።
በተለይም በከተማም ሆነ በገጠር አካባቢ የሚገኙ ዜጎች ሥጋ፣ እንቁላል፣ ማር እና ወተት ትርፍ ምርት ሆነው በየትኛውም የገበያ ሥፍራ በብዛትና በስፋት እንዲገኙ ማልማትና መጠቀምን መሠረት ያደረገ ነው። ይህም በቤተሰብ ደረጃ በስፋት ሲመረት ለገበያ የሚተርፍ ጭምር ነው።
በአንድ በኩል የምግብ ዋስትናን ማረጋገጫ፣ በሌላ በኩል የኢኮኖሚና ጤናማ ዜጋን ለማፍራት ጭምር ያለመ ነው፤ ይሄ መርሃ-ግብሩ በ2015 ዓ.ም በአራት ዓመታት ውስጥ ሊተገበር ታስቦ የተገባበት ነው። አርብቶ አደሩና አርሶ አደሩን እንደ ድልድይ ሆኖ የሚያገለግል ገዢና ሻጭን በኢኮኖሚ የሚያስተሳስር ድልድይ ነው።
የዜጎችን ደካማ የአምራችነት ታሪክ በመቀየር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ሥርዓተ ምግብን የሚያሻሽልና የኢኮኖሚ እድገትን የማፋጠን ግብ የሰነቀ መሆኑንም ልብ ማለት ይገባል። የሌማት ትሩፋት ዘመቻው በቤተሰብ፣ ብሎም በሀገር ደረጃ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት የሚያፋጥን እንደሚሆንም ይታመናል።
እንደተባለውም አሁን አሁን እየታየ ያለው የሌማት ቱሩፋት ውጤት ከቤተሰብ ደረጃ አለፍ ብሎ ለሀገር ኢኮኖሚ ጠቀሜታ እየዋለ ጭምር መሆኑን መመልከት ተችሏል። በከተማና በገጠር ላሉ ነዋሪዎች ሰፊ የሥራ እድል የፈጠረ መሆኑን ማስተዋል ቀላል ነው። ይሄው ዛሬ በአንዳንድ አካባቢዎች በሠሩት ሥራና ባገኙት ውጤት ከሌማት ቱሩፋት ወደ ገበያ ቱሩፋት መሸጋገር ችለዋል።
መንግሥት ለአራት ዓመታት የሚተገበር የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ሲያበስር ብዙዎች እንደ ቀላል ነገር ቆጥረውት ነበር። ተሠርቶ ውጤት ይታይበታል ብለው አልገመቱም ነበር። ሆኖም ግን በእያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ በተጀመረው ትንሽ ጥረት እንኳን ዶሮ በማርባት እንቁላል ለቤተሰብ መመገብ ተችሏል።
ዛሬ እንቁላል ዋጋው ከፍ አለ ብለው ከመጨነቅ የወጡ ብዙ ቤተሰቦች ናቸው፤ ልጆቻቸውን እንቁላል እና የዶሮ ሥጋ ከመመገብ አለፍ ብለውም እንቁላል እስከ መሸጥ የደረሱት ጥቂት አይደሉም። ምንም እንኳ አቅርቦትና ፍላጎት ላይ ክፍተት መኖሩ ባይካድም እንቁላል ከገበያ የሚጠፋ ምርት ከመሆን ርቋል።
የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የረጅም ጊዜ ግብም እንቁላልን በአነስተኛ ዋጋ መገበያየት እስኪቻል ድረስ በብዛት ማምረት መቻል ነው። በሀገር ውስጥ በብዛት ሲመረት ዜጋው እንቁላል እንደ ልብ ተመጋቢ ይሆናል፤ ከዚያም ከፍ ሲል ወደ ውጭ ኤክስፖርት እስከ ማድረግ ይደርሳል። በተሠራው ሥራ የተገኘው ውጤት የሚያመላክተው ምንም ዓይነት ሥራ ከተሠራ ውጤት እንደሚገኝበት የሌማት ትሩፋት አንዱ ማሳያ ነው።
ሌላው የሌማት ትሩፋት መገለጫው የአትክልት ምርቶች ልማት ነው። አትክልቶች በእያንዳንዱ ሰው ደጃፍ ላይ የሚገኙና በቀላሉ የሚመረቱ ምርቶች ናቸው። «ምንም የጓሮ አትክልት መትከያ ቦታ የለኝም» ያሉ ሰዎች እንኳን በተለያዩ ቀላል የቤት ውስጥ ቁሳቁስ በመታገዝ በጠባብ ቦታዎች ወይም በግድግዳ ላይ በሚንጠለጠሉ ፕላስቲኮች በመጠቀም እንደ ጎመን ፣ ቆስጣ፣ ቲማቲም፤ ቃሪያ እና ሰላጣ የመሳሰሉ የጓሮ አትክልቶችን ማምረትና መጠቀም ችለዋል። የፆም ወቅት ሳይሉ ከጓሮአቸው አትክልት ቆርጠው የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ችለዋል።
የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን እንድታረጋግጥ ማስቻል፤ በተለይም በሥጋ፣ እንቁላል፣ ማር እና ወተት ቅንጦት ሳይሆን ትርፍ ምርት ሆነው እንዲገኙ ማድረግ ነው። የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች የቅንጦት ምግቦች ሳይሆኑ ከሌማት ከማይጠፉ፣ በዕለታዊ ምግቦች ማባያነት የማይታጡ ግብዓቶች ማድረግ እንደሚቻል እሙን ነው። ወተት፣ ማር፣ ሥጋ እና እንቁላል መሰል የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን በገበያ ላይ በቀላሉ ማትረፍረፍ፣ የሌማቱ በረከት ማብዛት የሚለው የብዙሃኑ እምነት ነው።
ኢትዮጵያውያን በይቻላል መንፈስ የሕዳሴ ግድብን፣ አረንጓዴ ዐሻራ፣ የኮሪደር ልማት፤ የወንዝ ዳር ፕሮጀክት እና ሌሎች በርካታ ሀገራዊ የልማት እቅዶችን እውን እያደረጉ ነው፡፡ ይህንኑ ስኬታማ ጉዞ በሌማት ቱሩፋት መርሃ-ግብር እየተደገመ ይገኛል፡፡ በሂደቱም በከተማና በገጠር ለሚኖሩ በርካታ ዜጎች በምርት እና ገበያ ትስስር የሥራ እድል ፈጥሯል፡፡
የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር ግቡን እንዲመታ የተሻሻሉ የዶሮ እና የእንስሳት ዝርያዎችን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከፍተኛ የእንቁላል ምርት የሚያመርቱ የዶሮ ዝርያዎችን በማውጣት ለኅብረተሰቡ ያቀርባል። የሥጋና ወተት እንስሳት ዝርያዎችን ለማሻሻል የውጭ ሀገራት ዝርያ ያላቸው ኮርማዎችን በማዳቀል ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ይህም ኅብረተሰቡ የራሱን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ አልፎ የኢኮኖሚ አቅሙንም የሚያሳድግበት መሆኑን ከወሬ ባለፈ በተግባር ያረጋገጠበት ነው።
ለመርሃ ግብሩ እውን መሆን ደግሞ በተለይ አመራሩ ኅብረተሰቡን በማስተባበር በቁርጠኝነት የመሥራት እና የማገዝ ኃላፊነት ወድቆበታል። የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን ያስከበረች ነፃ ሀገር እውን ማድረግን ያለመ ጭምር በመሆኑ የተጣለበት ኃላፊነትም ድርብርብ ነው። ለዚህ ደግሞ ሁሉም ሰው መተባበር በትጋት መሥራትና ሀገርንም ራስንም መጥቀም ይገባል።
የሌማት ትሩፋት የቤተሰብን ጓዳ በእንስሳት፣ በዶሮ እና በማር ምርቶች በማትረፍረፍ፣ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በስንዴ፣ አትክልትና ፍራፍሬ የተገኘውን ስኬት መድገም ነው። ኢትዮጵያ ህልም የሚመስሉ በርካታ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን እውን ማድረግ የቻለችው በዜጎቿ የተባበረ ክንድ ነው፡፡
ከዚህ አኳያ በምግብ ራስን ከመቻል በላይ የኢትዮጵያን የአምራችነት ታሪክ የመቀየር ግብ ለሰነቀው የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር ስኬታማነት ከመቼውም ጊዜ በላይ በትብብር መሥራት ይጠበቃል፡፡ ምርቱን እያጣጠሙ ልማቱን ማፋጠን ለነገ የሚባል አይደለም። ዛሬም ከጓሮአችን ወደ ገበታችን ማለት መቻል አለብን። ለዚህ ደግሞ ቀስቃሽም ሆነ ወቃሽ አያሻም።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 ቀን 2017 ዓ.ም
አዶኒስ (ከሲኤምሲ)