ለሃይማኖት አባቶች ጥሪ ምላሽ መስጠት ራስን ለሰላም ማስገዛት ነው!

እያንዳንዱ ትውልድ የደረሰበትን የአስተሳሰብ ደረጃ ታሳቢ አድርጎ የራሱን ዕጣ ፈንታ ይወስናል። ትናንትን መሠረት አድርጎ ዛሬን ያበጃል፤ ነገን ይሠራል። ይህ ፍጥረታዊ መንገድ የሰው ልጅ አሁን ላለበት ሁለንተናዊ ዕድገት መሠረት የጣለ ስለመሆኑ የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች ይስማማሉ። ቀጣይ ዕጣ ፈንታውም ከዚሁ ተጨባጭ እውነታ ጋር በአንድም ይሁን በሌላ የተሳሰረ ስለመሆኑም ይናገራሉ።

በአንድ ወቅት የነበረ የትውልድ እሳቤ ከቀጣይ ትውልድ ሆኖ የመገኘት መሻት እየተገራ፤ በአዲስ አሻጋሪ አስተሳሰብ እየተቃኘ ወደ ቀጣይ ለውጥ እና የመለወጥ ሥርዓት ይሸጋጋራል። አዲሱ ትውልድ ትናንት ፈተና ለሆኑ ችግሮች መፍትሔ እየፈለገና እያፈላለገ ፤ ትናንቶችን እስከ ተግዳሮቶቻችው ተሻግሮ ዛሬን የተሻለ፤ ነገን ደግሞ ባለ ብዙ ተስፋ አድርጎ በሕይወት የተስፋ መንሰላሰል ውስጥ ያልፋል።

ትናንት ብዙ ሲነገርላቸው የነበሩ፤ ትናንትን እንደ ትናንት ያነጹ እና የገነቡ አስተሳሰቦች አርጅተው ትውልዱ ዛሬ ላይ መሆን የሚፈልገውን ሆነ ነገ ሆኖ እንዲቀጥል የሚመኘውን ፍላጎቱን ተጨባጭ ማድረግ አቅም ሲያንሳቸው፤ የእርጅናቸው መጠን ከፍላጎቱ ጋር በተቃርኖ ሲቆም፤ የጥፋት እና የውድቀት ምንጭ ሲሆኑ በውድም ይሁን በግድ ፍጥረታዊ ወደ ሆነው የመታደስ ሥርዓት መሸጋገራቸው የማይቀር ነው።

በቀደመው ዘመን /በቀደሙ ትውልዶች በሀገር ሆነ በማኅበረሰብ ግንባታ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የነበራቸው በዚህም ብዙ የተዜመላቸው፤ በብዙ ግጥም እና ዜማ አደባባዮችን የሞሉ፤ በማኅበረሰብ የማንነት ግንባታ ውስጥ ሳይቀር ከፍ ያለ ቦታ ተሰጥቷቸው የነበሩ አስተሳሰቦች እና ከአስተሳሰቡ የሚመነጩ ድርጊቶች ዋጋቸው እየገሸበ፤ ተፈላጊነታቸው እየቀነሰ ይሄዳል።

ትናንትን በማጽናት እና በመገንባት የቱንም ያህል ስፍራ ቢኖራቸውም፤ ዛሬን ዛሬ በማድረግ ሆነ፤ ነገን የተስፋ ርስት ለማድረግ በሚደረግ ሰብዓዊ መሻት ውስጥ የሚኖራቸው ማኅበረሰባዊ ፋይዳ የአዲሱን እና የመጪውን ትውልድ መሻት መሸከም እና ተጨባጭ የማድረግ ብቃት አይኖራቸውም። ከዚህ የተነሳም ዘመኑን ለሚዋጅ አስተሳሰብ እና አስተሳሰቡ ለሚሸከምም ተግባር ቦታ ይለቃሉ። ይህ የማይቀር የፍጥረት ሕግ አካል ነው።

ለዚህ አንዱ ማሳያ የሰው ልጅ በቀደሙት ዘመናት ያለፈባቸው የጦርነት ትርክቶች ናቸው። ዓለም ትናንት በተፈጠሩ እና ትናንትን አሸንፈው በወጡ የአስተሳሰብ መዛነፎች ብዙ ጦርነቶችን ለማስተናገድ የተገደደችበት ሁኔታ ተፈጥረዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቁት ጦርነቶች በተጨማሪ በሀገራት እና በሀገር ውስጥ በተካሄዱ እና ዛሬም እየተካሄዱ ባሉ ጦርነቶች የተከሰቱ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመቶች ከግምት ያለፉ ናቸው።

ዛሬ ላይ ያለው ዓለም/ትውልድ በአብዛኛው ከትናቶች በመማር ጦርነት ከሚፈጥረው ጀብደኝነት ወጥቶ፤ ከሰላም ለሚገኘው እድገት እና ልማት ትልቅ ቦታ ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው። ይህም አሁን ላይ ላለው የዓለም ኢኮኖሚ እድገት፤ የቴክኖሎጂ እመርታ ሆነ የተረጋጋ የማኅበረሰብ ግንባታ ትልቅ አቅም የፈጠረ ነው። ጦር ሰብቆ ወደ ጥፋት ከመጓዝ ይልቅ ቁጭ ብሎ መነጋገርን መሠረት ያደረገ የለውጥ አቅጣጫ ዓለምን እያሸነፈ ነው።

ግጭት እና ጦርነቶችን ማስቀረት ታሳቢ ያደረጉ ድርድሮች እና ውይይቶች ከትናንት ይልቅ ዛሬ ላይ ሰፊ ስፍራ አግኝተዋል። ለሰላም የሚከፈል ዋጋ የቱንም ያህል ውድ ቢሆን አትራፊ እንደሆነ ዓለም ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ዛሬ ላይ ተቀብሎ አስፈላጊውን ሁሉ ለመክፈል የተሻለ ዝግጅት ፈጥሯል።

የጦርነት አስከፊነት ምን ያህል እንደሆነ ለኢትዮጵያውያን ለመንገር መሞከር ለቀባሪ የማርዳት ያህል ነው፤ እንደ ሀገር ጦርነቶች በፈጠሩት ውድመት ከታላቅ ሥልጣኔ ወርደን፤ ተመልሰን መውጣት የህልም ያህል ርቀውብን ቆይተዋል። ለብዙዎች የሚተርፍ ተስፋ እና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤቶች ሆነን የራሳችንን ዛሬዎች ማሸነፍ አቅቶን የድህነት እና ኋላ ቀርነት ማሳያ ሆነን ኖረናል።

ከድህነት እና ከኋላቀርነት ጋር በተያያዘ እየከፈልነው ያለው ዋጋ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው ለተጨማሪ ግጭት እና ጦርነት እየዳረገን ነው፤ በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶች በብዙ መነቃቃት ያለሙትን ህልማቸውን ከሩቅ ተሳልመው እንዲሄዱም እያስገደዳቸው ነው።

ቃታ ተስቦ ወንድምን በመግደል ላይ የተገነባው የጠመንጃ አምላኪነት፤ ከዚህ የሚመነጨው የጀግና ጀግና ማብቂያ ያጣው የደም ጨዋታ፤ ዘመናትን ተሻግሮ የብዙ ትውልዶችን ተስፋ መናጠቁ፤ ከነበርንበት ከፍታ አውርዶ የዝቅታ ማሳያ ያደረገን መሆኑ ቀርቶ፤ ዛሬም የሆይ ሆይ ማዕከል ሆኖ የዚህን ትውልድ ተስፋ እየተናጠቀ ነው።

ከትናትን ከተቀዳው የአሁናዊ ችግሮቻችን ሁሉ መሠረት ከሆነው በጠመንጃ ልዩነትን ለመፍታት የመሞከር አምላኪነት ባሕል እና ከዚህ ከሚቀዳው የጀግና ጀግና ውዳሴያችን መውጣት ከዘመኑ ጋር ለመታረቅ አንድ ርምጃ የመራመድ ያህል ነው። ከሚገዳደረን የትናንት እርግማን /አስተሳሰብ ጥላ ነፃ ለመውጣት ያለንን ቁርጠኝነት ማሳያም ነው።

ለዚህም ነው የሃይማኖት አባቶች ጠመንጃ ይውረድ፤ ከጠመንጃ አፈሙዝ የሚቀዳ የሥልጣን መሻት ይብቃ ሲሉ አበክረው እየጠየቁ ያለው። በወንድም ላይ ቃታ በመሳብ የሚመጣ ነፃነት እንደሌለ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው እያሰሙ ያለው። ለዚህ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ ምላሽ መስጠት ከዛሬ ጋር መታረቅ፤ ከትውልዱ ተስፋ ጋር መስማማት ከሁሉም በላይ ለሰላም ማስገዛት ነው!

 

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You