
በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በማክሮ ኢኮኖሚ መመዘኛው በተለያዩ ዘርፎች ለውጦች መመዝገባቸውን መንግሥት አስታውቋል። እነዚህ ለውጥ ከታየባቸው ዘርፎች መካከል የፋይናንስ ዘርፉ አንዱ ነው። በፋይናንስ ዘርፉ ከታዩ ለውጦች መካከልም ባንኮች የሰጡት ብድር ይጠቀሳል።
ቀደም ሲል ለግሉ ዘርፍ ይቀርብ የነበረው የብድር መጠን አሁን ካለው ጋር ሲነፃፀር ትልቅ ልዩነት እንዳለው አንድ መረጃ አመልክቷል። በመረጃው እንተጠቆመው፤ ከሰባት ዓመታት በፊት ንግድ ባንክ ከሚያቀርበው የብድር መጠን 80 በመቶ የሚሆነው የሚውለው ለመንግሥት የልማት ተቋማት ነበር። ይህ ሁኔታ አሁን ተለውጦ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው ብድር ለግሉ ዘርፉ እየቀረበ ነው።
ይህ ትልቅ ለውጥ ነው፤ ቀደም ሲል አብዛኛው ብድር ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይሰጥ ከነበረበት ሁኔታ ወደ ግሉ ዘርፍ መዞሩ በእርግጥም ትልቅ ለውጥ ነው። ለግሉ ዘርፍ የተሰጠው ብድር ለምን ለምን ዋለ የሚለው ሲታይ ግን አሁንም በብድር አሰጣጡ ላይ በትኩረት መሥራት ያለበት ሁኔታ እንዳለ ያስገነዝባል።
በሌላ መረጃ እንደተጠቆመው፤ በ2017 በጀት ዓመት ስምንት ወራት ባንኮች 473 ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ብድር መስጠታቸው የተጠቆመ ሲሆን፤ ባለፈው በጀት ዓመት በዚህ ወቅት 292 ቢሊዮን እንደነበር ተመላክቷል። ይህ ብድር የት ነበር የሄደው ሲባል 76 በመቶውን የወሰደው የግል ዘርፍ ነው። የመንግሥት ልማት ድርጅቶች 23 በመቶውን ወስደዋል።
ለግሉ ዘርፍ እየተለቀቀ ያለው ብድር ወዴት ነው የሚሄደው ተብሎ አሁንም ሲጠየቅ ግብርና 23 በመቶ ፣ ማኑፋክቸሪንግ 13 በመቶ ከመውሰዳቸው በስተቀር፤ ትልቁን ብድር እየወሰደ ያለው የንግዱ ዘርፍ ነው።
ይህ ሁኔታ በብድር አለቃቀቅ ላይ አሁንም መታየት ያለበት ነገር እንዳለ እንደሚያስገነዝብ፣ የሀገር የትኩረት አቅጣጫ የሆኑት ማኑፋክቸሪንግና ግብርና ከትራንስፎርሜሽን አኳያ ያላቸውን ሚና ታሳቢ ያደረገ ብድር መለቀቅ እንዳለበት ያመላከተ ነው። ለግሉ ዘርፍ ብድር እየቀረበ ባለበት አሠራር ላይ ባንኮች ማሻሻያዎችን እንዲያደርጉም እየተጠየቀ ይገኛል፡፡
ባንኮች ፋይናንስ በማቅረብ በኩል ከፍተኛ መሻሻል ማሳየታቸው አንድ ትልቅ ለውጥ ሲሆን፣ የሚሰጡት ብድር ወደ አገልግሎት ዘርፍ እያደላ ያለበትን ሁኔታም በመቀየር ሁሉንም ዘርፎች በተለይ ግብርናና ማኑፋክቸሪንግ ታሳቢ እንዲያደርግ መሥራት ይኖርባቸዋል።
መንግሥትም በተለይ በግብርናው ዘርፍ ብድር አቅርቦት ላይ ለውጥ እንዲመጣ ብዙ ሠርቶ ለውጥ ማምጣት እንደጀመረ ሁሉ ለግብርናና ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚቀርበው ብድር የበለጠ እንዲጨምር ማድረግ ላይ አሁንም በተጠናከረ መልኩ መሥራት፣ ባንኮች በእዚህ ላይ እንዲሠሩ ማድረግም ይኖርበታል።
እንደሚታወቀው ልማቱ ሰፊ እንደመሆኑ የፋይናንስ ፍላጎቱም ከፍተኛ ነው፤ ሁሉም ዘርፎችና አገልግሎቶች የፋይናንስ ጥያቄ ያነሳሉ። አብዛኛውን የብድር አገልግሎት የግሉ ዘርፍ ለዚያውም ከማኑፋክቸሪንግና ግብርና ውጪ ያለው የንግዱ ዘርፍ እያገኘም የፋይናንስ ያለህ ሲል ይደመጣል።
ግብርናው መንግሥት ባደረገው ጥረት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተወሰነ መልኩም ቢሆን የፋይናንስ አቅርቦት ማግኘት የጀመረ ቢሆንም፣ አሁንም ዘርፉ ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት ግብርናውን ለማዘመን የሚያስችለው በቂ የፋይናንስ አቅርቦት ያስፈልገዋል። ኢንዱስትሪውም እንደዚያው ነው።
እንደ ሀገር የተያዘው ልማት በእጅጉ የፋይናንስ አቅርቦት እንደሚያስፈልገው ማንም ይገነዘበዋል። ለእዚህ የሚውል ፋይናነስ ማፈላለግ የግድ ይሆናል።
ቁጠባ ለኢንቨስትመንት መስፋፋት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ይገለጻል። ቁጠባን ማብረታታት አንዱ መንገድ ነው። ዜጎች ቁጠባ የሚያጎለብቱባቸው መንገዶች ከመቼውም ጊዜ በላይ መስፋት ይኖርባቸዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ሥራ የገቡትና የፋይናንስ ዘርፉን እንደሚያነቃቁ የሚጠበቁት እንደ ሰነደ መዋእለ ንዋዮች ገበያ / ካፒታል ገበያ/ እና ኢንቨስትመንት ባንኮች ባሉት ተቋማት ላይ የተጀመረው ሥራም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ይህ ሲሆን የፋይናንስ ፍላጎቱን የመመለስ አቅሙ እየጨመረ ይመጣል።
ፋይናንስን ውጤታማ በሆነ መልኩ መጠቀምም ሌላው ሥራ መሆን ይኖርበታል። ጤናማ የፋይናንስ ስርዓት በመዘርጋት ሀገራዊ ልማቱን ያማከለ የብድር አገልግሎት እንዲኖር መሥራት ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 3 ቀን 2017 ዓ.ም