
ኢትዮጵያ በርካታ ታሪኮች ያላት፤ በዓለም ሥልጣኔ ፊት መሪና ተጠቃሽ ሀገር ናት። አስደናቂ፣ እጅግም አስደማሚ ኪነህንጻዎችን እና የጥበብ ውጤቶችን ቀድማ ለዓለም ያስተዋወቀች፤ ከዛም አልፋ ያበረከተች አፍሪካዊት ሀገር ናት። ጀግኖች ሕዝቦቿ የሀገራቸውን ዳር ድንበር አስከብረው፣ ነጻነቷን አስጠብቀው የኖሩ የኩሩና አትንኩኝ ባይ ሕዝቦች ሀገር መሆኗ ሁሌም በዓለም ታሪክ ውስጥ ተጠቃሽ አድርጓታል።
በተለያዩ ዘመናት የተነሱብንን፤ በቅኝ ግዛት ሊያንበረክኩን የመጡትን ኃይላት በጀግንነት አሸንፈን ታሪካችንን በወርቅ መዝገብ ያሰፈርን ጠንካራ እና ቆራጥ አርበኞች ነን። ይሄ የአርበኝነት አኩሪ ታሪካችን ነውና ምን ጊዜም ከፍ ብሎ ይውለበለባል፤ ይወደሳልም። ከዚህ አኩሪ ታሪካችን ጀርባ ግን “ምነው እነዛ ሁሉ ታሪኮቻችን ታሪክ ሆነው ቀሩ?” ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅ ህሊናችን ያስገድደናል። “በነበርንበት የሥልጣኔ ፈር ቀዳጅነት ልክ ለምን አልተራመድንም? እነዚያ ምጡቅ አእምሮዎች፣ እነዛ የጥበብ እጆች የት ገቡ?” ብለን ራሳችንን ልንጠይቅና የነበር ታሪካችንን ልናድስ ያለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ግድ ይለናል።
አሁን ዘመኑ የቴክኖሎጂ፣ የፈጠራና የፈጣሪዎች ነው። ዓለም ላይ ብዙ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ግኝቶች፤ የፈጠራ ውጤቶች እየወጡ ነው። ዓለም በፍጥነት እየተለወጠች፣ እየተራመደችና እያመለጠችን ትገኛለች። ይሄንን ቆም ብሎ ማስተዋል ያስፈልጋል። ከዓለም ጋር አብረን መራመድ እና መዘመን የግድ ይሆናል። የቀድሞውን ታሪካችንን ከማውራት በዘለለ እጆቻችንን ለፈጠራ ሥራዎች፣ አእምሯችንን ለፈጣሪነት፣ ጊዜያችንን እና ጉልበታችንን ለሥራ ልናውለው ይገባል።
የሥልጣኔ ፈር ቀዳጅነታችንን ወደ ፊት ልናራምደው፤ “ነበሩ” ከመባል ወጥተን ታሪካችን በአዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች ልናድስ የዓለም ሁኔታ ያስገድዳል። በየተሠማራንበት መስክ ውጤታማ ሆነን ሀገራችን ወደ ብልፅግና እያደረገች ላለችው ግስጋሴ በየመስኩ አርበኞች መሆን አለብን። ከ70 በመቶ በላይ ወጣት የኅብረተሰብ ክፍል ይዘን አሁንም እንደ ጭራ የኋሊት መጓዝ አይገባንም።
የቀድሞው የነጻነት ጀግንነታችንን በዛሬዪቱ ኢትዮጵያም ልንደግመው፤ በየተሰማራንበት መስክም በተግባር ልንገልፀው ይገባናል። እያንዳንዱ ሰው በየተሰማራበት ሙያና መስክ የተጣለበትን ሃላፊነት በብቃት ከተወጣ ለመስኩ አርበኛ ነው። በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሁሉም ሰው ሊነቃ እንጂ ተደላድሎ ይተኛ ዘንድ አልተፈቀደለትምና በየተሰማራንበት ሁሉ ውጤታማ ልንሆን ይገባል።
እስካሁን ድህነታችንን አውቀንና አምነን ተቀብለን አብረነው እየኖርን ነው። ዓለም የደረሰበትን እያደነቅን በ”ነበር” ታሪኮቻችን ተኮፍሰን የዓለም ጭራ ሆነን ቆይተናል። ይህ ደግሞ የትም እንደማያደርስ አይተነዋል፤ ተረድተናልም። ስለዚህ መንቃት አለብን። ብሩህ የሆኑ አእምሮዎች፣ የሚሠሩ እጆች አሉን። እነዚህን አስተባብሮ ወደ ውጤት መቀየር ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ነው። በየተሰማራበት መስክ ውጤታማና አርበኛ ሆኖ መገኘት ለነገ የሚባል ተግባር አይደለም።
በግልፅ እንደሚታወቀው፣ ሀገር በታሪክ ብቻ ሳይሆን በሚሠሩ እጆች፣ በሚፈጥሩ አዕምሮዎች፣ በቅን እና ትጉህ መሪዎች እጅ ላይ ናት። በታሪክ አጋጣሚ የዚህ ዘመን ትውልድ ይሄ ሀገርን የማሻገር ኃላፊነት በእጁ ገብቷል። በመሆኑም፣ ይሄንን ኃላፊነት በብቃት መወጣት እና ዐሻራውን በወርቅ መዝገብ ላይ ማስፈር አለበት።
አሁን ባለው ሁኔታ ክሒሎት፣ ፈጠራ፣ ፍጥነት እና ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያን ከድህነት መንጥቀው የሚያወጡ መሆናቸው ላይ ግንዛቤ ተይዞ እየተሠራ ይገኛል። ይህንን በአርበኛነት መንፈስ መወጣት ይገባል። የዘመኑ አርበኝነት መንታ ገፅታን የተላበሰ ነው። በአንድ በኩል የሀገራችንን ሉዓላዊነት፣ ነፃነትና ክብር ማስጠበቅ፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ድህነትና ኋላቀርነትን በማሸነፍ ብልፅግናን ማረጋገጥ ነው። ይሄንን መንታ አርበኝነታችንን በብቃት ልንወጣ ይገባል።
የሀገር ሉዓላዊነትን ከማስጠበቅ ባለፈ ድህነትንና ኋላቀርነትን በማሸነፍ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ኃላፊነት የአሁኑ ትውልድ ግዴታ እንጂ የማንም አይደለም።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተሠሩ ተግባራትም በፈጠራ የበሰሉ ብሩህ አዕምሮዎችን፣ የተፍታቱ እጆችን፣ በክሒሎቶቻቸው የበቁ ዜጎችን ማፍራት ተችሏል። የክሒሎት ልማት ለሀገራችን ዕድገት እና ብልፅግና ወሳኝ ነው።
ኢትዮጵያ ወራሪ ጠላትን መክተው ሉዓላዊነቷን ያስጠበቁ ጀግኖች አርበኞች እንደነበሯት ሁሉ፤ ዛሬ ደግሞ የሙያንና የክሒሎትን አቅም በመጠቀም ግብርናችንን የሚያዘምኑ፣ ለኢንዱስትሪ ዕድገት ወሳኝ መነሻ የሆኑ፣ የቱሪዝም ዘርፉን ውጤታማ የሚያደርጉ፣ ዲጂታላይዜሽንን የሚያፋጥኑ ብቁ ሙያተኞች አሏት።
የሀገርን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም ክሒሎት ወሳኝ በመሆኑ መንግሥት ዘርፉን ለማሳደግ እየሠራ ይገኛል። ባለ ብሩህ አዕምሮና በክሒሎት የዳበሩ ዜጎችን መፍጠር አለብን። ሀገር የምትበለፅገው በ”ነበር” ታሪክ አይደለም። በየመስኩ ሁሉም አርበኛ መሆን ሲችል መሆኑን መረዳት ይገባል። አዕምሮን ከፈት አድርጎ ጎርባጭና ጎታች አመከላከቶችን፤ የፖለቲካ ሽኩቻዎችን ወዲያ ገፍትሮ ለክሒሎትና ፈጠራ ሥራዎች ከፊት መሰለፍን ጊዜው ይጠይቃል። የክሒሎት ልማት ለሀገራችን ከድህነት መውጣት ፍቱን መድኃኒት መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበውና ለተግባራዊነቱ ከፊት ተሰላፊ ሊሆን ይገባል!
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም