
– ክልሎች የካሳ ክፍያን ኃላፊነት እንዲረዱና ደንቡን እንዲያከብሩ ጥረት እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፦ የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበት እና የልማት ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበት የካሳ አዋጅ ቁጥር 1336/2016 ወጥ በሆነ መልኩ ተግባራዊ እየተደረገ አለመሆኑን የከተማ መሠረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመለከተ። የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በበኩሉ፤ ክልሎች የካሳ ክፍያን ኃላፊነት እንዲረዱና ደንቡን እንዲያከብሩ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታወቀ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 26ኛ መደበኛ ስብሰባ የከተማ እና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ትናንት ባደመጠበት ወቅት፤ የከተማ መሠረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ንዑስ ሰብሳቢ ወይዘሮ ገነት ከተማ፤ ቋሚ ኮሚቴው የመስክ ምልከታ ባደረገባቸው ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አዋጁ ወጥ በሆነ መልኩ ተግባራዊ እየተደረገ እንዳልሆነ አረጋግጧል ብለዋል።
ደንብ ከማዘጋጀት፣ ለባለድርሻ አካላት ግንዛቤ ከመፍጠር እና የልማት ተነሺዎችን ስጋት በመቅረፍ የካሳ አከፋፈል ሥርዓቱ በአዋጁ መሠረት ተፈጻሚ ለማድረግ ምን እየተሠራ ነው ያሉት ወይዘሮ ገነት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተከናወነው ተግባር ውጤታማ ነው ተብሎ ስለማይወሰድ በቀጣይ አዋጁን ወጥ በሆነ መልኩ ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
የቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ እሸቱ ተመስገን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ከመንገድ ፕሮጀክቶች የወሰን ማስከበር እና በዘርፉ የተሰማሩ የመንገድ ሥራ ተቋራጮች የሚያቀርቡትን የክፍያ ጥያቄዎችን በወቅቱ ምላሽ ያለመስጠት ችግር መኖሩን አመልክተዋል።
የተሻሻለው የካሳ አዋጅ ቁጥር 1336/2016 ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ በክልሎች እና በከተማ አስተዳደሮች ወጥ በሆነ መልኩ ግንዛቤ በመፍጠርና መመሪያ በማዘጋጀት በወሰን ማስከበር ላይ የሚታዩ ችግሮች እንዲፈቱ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል ፡፡
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው፤ አዋጁን ሁሉም ክልሎች በእኩል ደረጃ ተግባራዊ አላደረጉም። አዋጁን ተግባራዊ ለማድረግ ከክልሎችና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በተለያዩ ጊዜያት ውይይት ተደርጓል። በእዚህም ክልሎች የካሳ ክፍያን ኃላፊነት እንዲረዱና ደንቡን እንዲያከብሩት ከፍተኛ ጥረቶች ተደርጓል ብለዋል።
ለፌዴራል ፕሮጀክቶች የካሳ ክፍያ ክልሎች ያላቸው ኃላፊነት ልል ነበር። ይህም ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሲያሳድር በመቆየቱ የካሳ አዋጁ በአዋጅ ቁጥር 1336/2016 እንዲሻሻል ተደርጓል ያሉት ሚኒስትሯ ፤ በእዚህም የካሳ ክፍያው የክልሎች ኃላፊነት እንዲሆን መደረጉን አመልክተዋል።
በእዚህም የተወሰኑ ክልሎች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጡ ቢሆንም፤ አንዳንድ ክልሎች ጉዳዩን ችላ የማለት ነገር ታይቶባቸዋል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ይህም አዋጁን ወጥ በሆነ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ ችግር መፍጠሩን ጠቁመዋል።
በፊት የነበረው የካሳ አዋጅ የፈጠረውን ችግር ለመፍታት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቁመው ፤ የዜጎችን መብት ማክበር የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን የመመለስ አንዱ አካል በመሆኑ የፌዴራል መንግሥት ማገዝ በሚገባው ልክ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 17 ቀን 2017 ዓ.ም