ማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት የመክፈል አቅምን መሠረት ባደረገ መዋጮ እንዲተገበር መደረጉ ተገለጸ

አዳማ፡- በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት እንደሀገር ከተተገበረ ወዲህ የመክፈል አቅምን መሰረት ያደረገ መዋጮ ተግባራዊ መደረጉን አስታወቀ። የተዘረጋው ሥርአት በርካታ መክፈል የማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በጤና መድህን ስርአት ተጠቃሚ ማድረጉን አመለከተ።

የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ከትናንት ጀምሮ በአዳማ ከተማ በደንበል ቪው ሆቴል እያደረገ በሚገኘው የዘጠኝ ወር እቅድ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ተስፋዬ ወርቁ እንደገለጹት፤ የተዘረጋው የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል።

በተያዘው በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ ከ13 ሚሊዮን በላይ አባወራዎችና እማወራዎችን በመመዝገብ ጥቅል ምጣኔው 83 በመቶ፤ የአባልነት እድሳት ደግሞ 94 በመቶ ደርሳል፤ በጥቅሉም 60 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል ብለዋል ።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በጤናው ዘርፍ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ፣ ጤናማና የበለጸገ ማኅበረሰብ ለመፍጠር መንግሥት፣ የሁለተኛው ዙር የመካከለኛ ዘመን የጤና ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አዘጋጀቶ ወደ ትግበራ ገብቷል::

የጤናው ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን እቅድ ዋነኛ ግብ ለሁሉም ዜጎች የጥራት ደረጃውን የጠበቀ የጤና አገልግሎት በፍትሐዊነት ተደራሽ በማድረግ ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን ማሳካት እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

በእቅዱ ከተቀረጹ የሪፎርም አጀንዳዎች ውስጥ አንዱ የጤና ክብካቤ የፋይናንስ ሥርዓትን ማሻሻል እንደሆነ ጠቁመው፤ በጤና ክብካቤ የፋይናንስ ሥርዓት ማሻሻያ ፕሮግራም ትኩረት ከተሰጣቸው የሪፎርም አጀንዳዎች ውስጥ የጤና መድኅን ሥርዓትን መተግበር አንዱና ዋነኛው እንደሆነ ገልጸዋል ፡፡

አብዛኛዎቹ ወረዳዎች የመክፈል አቅምን መሰረት ያደረገ የማኅብረሰብ አቀፍ የጤና መድህን መዋጮ ትግበራ ጀምረዋል” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለስኬቱ መመዝገብ የአመራር ቁርጠኝነት አንዱ ምክንያት መሆኑን አንስተዋል። በተያዘው በጀት ዓመት 82 የሚደርሱ ወረዳዎች ከ100 በመቶ የአባልነት ሽፋን ማስመዝገብ መቻላቸውን ጠቅሰዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ፤ በ9 ወራት ውስጥ የታዩ ተግዳሮቶች መኖራቸውን በማንሳት ከነዚህ ውስጥ በከፍተኛ የገቢ እርከን ላይ የተመደቡ እማወራና አባውራዎችን በጤና መድህን አገልግሎት ሥርአት ውስጥ አባል ከማድረግ አንጻር ያለው አፈጻጸም በጣም ዝቅተኛ መሆኑን አመልክተዋል ።

የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድን የአባልነት ምዝገባና እድሳት ሽፋን ዝቅተኛ መሆኑ፣ የአባላት ምዝገባና እድሳት አፈጻጸም በተቀመጠለት የጊዜ ስሌዳ አለመጠናቀቁ፣ ከአባላት የሚሰበሰብ መጥጮ በወቅቱ ባንክ ገቢ ያለመደረጉ፣ ሁሉም ክልሎች ዓመታዊ የፋይናንስ ኦዲት ያለማስድረግና በኦዲት የሚገኝ የገንዘብ ጉድለት በወቅቱ አለማስመለስና ርምጃ ያለመውስድ፣ የአባላትና የመዋጮ መረጃ ጥራት ውስንነት ልሎች በበጀት ዓመቱ የተስተዋሉ ችግሮች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

“የጤና መድህን አገልግሎት አባላት ቃል የተገባላቸውን የጤና አገልግሎት በሙሉ ማግኘታቸውን ማረጋገጥ ይኖርበታል” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ተስፋዬ፤ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነትንና ጥራትን በማሻሻል፣ እንደ ሀገር ጤናማ፤ አምራችና የበለጸገ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የተያዘውን ራዕይ እውን ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።

በዘጠኝ ወር አፈጻጸም ግምገማው ላይ የቀረበው ሪፖርት ላይ የተመለከተው መረጃ እንደሚጠቁመው፤ በዘንድሮው ዓመት ከተናጠል የክልሎች ድጎማና ከአባላት መዋጮ 14 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ የተሰበሰበ ሲሆን 5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ክፍያ ተፈጽሟል።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You