«የሃሳብ ልዩነት ወደ ግጭትና መገዳደል ካመራ ድምር ውጤቱ ዜሮ ነው» – አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት

አዲስ አበባ፦ የሃሳብ ልዩነት ወደ ግጭትና መገዳደል ካመራ ድምር ውጤቱ ሁላችንንም ተጎጂ የሚያደርግ የዜሮ ስሌት መሆኑን የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) አመለከቱ ።

ምክትል ፕሬዚዳንቱ ትናንት የአቶ ግርማ የሽጥላ ሁለተኛ ዓመት መታሰቢያ ሥነ- ሥርዓት በሜቄዶንያ በተካሄደበት ወቅት ባስተላለፉት መልእክት፤ ከወንድማችን መሰዋት መማር ያለብን የሃሳብ ልዩነት ወደ ግጭትና መገዳደል ካመራ ድምር ውጤቱ ዜሮ መሆኑን ነው።

ዛሬም ድረስ በተጨባጭ እንደምናየው ግርማን በመግደል የተገኘ ውጤት የተጨበጠ ሥልጣንም የለም። ይልቁንም የመጣው ከፍተኛ ችግርና የሕዝብ ሰቆቃ ነው ብለዋል ።

የታሰበው የጽንፈኝነት አስተሳሰብና ከጀርባ የነበረው ሴራ ሊሳካ አልቻለም፤ ያልተሳካው ጠንካራ ስላልነበር ሳይሆን እነ ግርማ ይዘውት የነበረው ሃሳብ ከዛ በላይ ጠንካራና የሕዝቦችን ወንድማማችነትና እህትማማችነት የሚሰብክ የብርሃን ሃሳብ በመሆኑ እንደሆነ አስታውቀዋል።

ግለሰቦችን በመግደል የሚገኘው ውጤት ቤተሰቦቻቸውን ማሳዘን፤ ማደህየትና ማቆርቆዝ ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር አንድነትና እድገት ሕዝብ ከመቀጠል የሚያስቀር አይሆንም ።

የአማራ ሕዝብ በእዚህ ሁኔታ መገናኘት አልነበረበትም ያሉት ዶክተር አብዱ፤ አቶ ግርማ የተሰውበት ቀን በአማራ ክልል ያለውን ችግር የሚያሳይ፤ አሁን ያለንበት የሃሳብ ልዩነትን በግድያ ለማስተናገድ የጽንፈኝነት አስተሳሰብ እንቅስቃሴ የተጀመረበት ነው ብለዋል።

አቶ ግርማን ስንዘክር የሃሳብ ጥራትን የሃሳብ ብዝሃነትን የሕዝቦችን ግንኙነትና ወንድማማችነት መመስረት ያለበት በፍቅር በመዋደድ እንጂ በጀብደኝነትና ጠመንጃ በመወዝወዝ እንዳልሆነ በመግለጽ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ይህ ሃሳብ ዛሬም ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆንም ዋጋው እየተከፈለ የሀገርና የሕዝብ ልእልናና ወዳጅነት እንዲቀጥል እንሠራለን። አሸናፊ የምንሆነው ሁሉንም ነገር ከጠመንጃ በታች በመነጋገር በመወያየት ሲሆን ብቻ ነው። ይህ መንገድ እኛንም ሀገርንም አሸናፊ የሚያደርግ ይሆናል ብለዋል።

የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሬሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ አቶ ግርማ በሕይወት ቢለይም ይዟቸው የተነሱ ሃሳቦችን ዳር ለማድረስ መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

አቶ ግርማ የሺጥላ የአማራ ሕዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመፍታት ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በኅብረ ብሔራዊ እህትማማችነትና ወንድማማችነት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ከፍተኛ ትግል ሲያደርጉ የቆዩ መሪ ናቸውም ብለዋል።

ይህን የአቶ ግርማ የሺጥላን ሃሳብ ኢትዮጵያን በማስቀጠል እውነት አሸናፊ መሆኗን ማሳየት፤ በእሱ የተጀመሩ ጉዞዎችን በማስቀጠል የሕዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፤ለእዚህ ደግሞ እርስ በእርስ መገዳደል መቆም እንዳለበት አመልክተዋል። ለእዚህም የሃሳብ ልዩነትን በመነጋገርና በመመካከር መፍታት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You