በዘመናችን ታሪክ ራሳቸውን “የዳቦ ቅርጫት” ከማስባል አልፈው ለሌሎች ጭምር “እጀ ሰፊ” ሆነዋል የሚባሉ ሀገራት በርካታ ናቸው:: እነዚህ ሀገራት “ኩራትና ራት” የሆናቸው ታላቅ በረከት ደግሞ ተዝቆ ያልቅ የማይመስለው የስንዴ ምርታቸው መሆኑ ይታወቃል::
በዓለማችን ቻይና፣ ሕንድ፣ ሩስያ ፣ አሜሪካና ፈረንሳይን ጨምሮ ካናዳ፣ አውስትራሊያና አርጀንቲና የስንዴ አምራችነቱን በዋንኛነት ተቆጣጥረውታል:: ይህን ተከትሎም አሁን ላይ የዓለምን ገበያ በግንባር ቀደምነት እየመሩት ይገኛሉ::
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ዩክሬን ከጦርነቱ በፊት ከሰሀራ በታች ለሚገኙ ሀገራት 35 በመቶ የሚሆነውን የስንዴ ምርት በማቅረብ ትታወቃለች:: ሌሎች ሀገራትም ለብዙኃን የምግብ ዋስትና የሆነውን ስንዴ በሽያጭ በማቅረብ ከፍተኛውን ደረጃ ይይዛሉ:: የስንዴ ምርት በምግብ ሰብል ራሳቸውን ላልቻሉ ሀገራት የመኖራቸው ሕልውና ነው:: በየግዜው በአነስተኛ ሽያጭና በእርዳታ ጭምር በሚያገኙት ምርት ሕይወታቸውን ለማስቀጠል ችለዋልና:: ሀገራችን ኢትዮጵያም ለዓመታት እየተመላለሰ በፈተናት የድርቅና ርሀብ ታሪክ በስንዴ ግዢና ርዳታ ክፉ ቀናትን ተሻግራለች::
ለጊዜ ምስጋና ይግባውና ይህ ያለፈ ታሪኳ በ“ነበር” መወሳት ከያዘ እነሆ! ዓመታት መቆጠር ጀምረዋል:: አሁን ላይ የኢትዮጵያ ነባራዊ ታሪክ እንደሚያስረዳው፤ ይህች ሀገር በስንዴ ምርት ራሷን ለመቻል ባደረገችው ጥረት በመኸር ወቅት ላይ ብቻ ይጠበቅ የነበረውን የአመራረት ስልት በመቀየር የበጋ መስኖ ልማትን ባህል ማድረግ ችላለች::
ይህ የአሰራር ለውጥ ውጤት ማስገኘቱም በስንዴ ምርት የምግብ ዋስናትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ተስፋን አጭሯል:: ባለፉት ዓመታት የስንዴ አመራረትን ለማሻሻል በተደረገው ጥረት በርካታ የኤክስቴንሽን ሥራዎች ተከናውነዋል:: በዘመናዊ መሣሪያዎች የተደገፉ የመስኖ ልማቶችና የተሻሻሉ የግብአት አቅርቦቶች ተካሂደዋል:: የበጋ መስኖ ልማት የሀገሪቱን የስንዴ ፍላጎት በራስ አቅምና ደረጃ ለማሳደግ ያለመና ከፍተኛ ጥረት የሚከወንበት ነው:: ባለፉት ዓመታት የበጋ መስኖ ልማትን በስንዴ ምርት ላይ ለመተግበር በነበሩ እንቅስቃሴዎች ፈተናዎች ማጋጠማቸው አልቀረም::
በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የቀደመውን አሠራር ለመቀየርና ፈጥኖ ወደ ለውጥ ለመግባት ሂደቱ ቀላል ይሉት አልነበረም:: አብዛኞቹ አርሶ አደሮች በበጋ መስኖ ልማቱ ልባቸውን የሚያሳርፍ መተማመን አልነበራቸውም:: ሃሳቡን ተቀብሎ ፈጥኖ ለመተግበርም ፍላጎታቸው በምሉዕነት አልተገለጸም:: እንዲያም ሆኖ ፈጣን ውጤትን የተላበሰው የበጋ መስኖ ልማት በስንዴ ላይ ዕውን ለመሆን አልዘገየም::
ይህ እውነት የስንዴ አምራች አካባቢዎች በሙሉ የቀደመ ታሪካቸው በበረከት እንዲሞላ ማሳያ ሆኗል:: የለውጥ ሂደቱም በርካታ አርሶ አደሮች ቀድሞ ያመርቱት ከነበረው ምርት በእጥፍ እንዲያፍሱ አስችሏል:: የልማቱ ፍሬ ከጎጥና ከአካባቢ አልፎ ስንዴን ማምረት ሞክረው ለማያውቁ አካባቢዎች ጭምር የምርታማነት መገለጫ እስከመሆን ደርሷል::
እስከዛሬ በሀገራችን የነበረው የስንዴ ታሪክ ምርቱን ከውጭ ሀገራት በግዢ መግዛትና መጠቀም ላይ ያደረገ ነበር:: በ2014 ዓ.ም በመንግሥት በተደረሰው ውሳኔ ግን “ስንዴን ከውጭ ሀገራት እጆች ከመቀበል ምርቱን ወደ ውጭ ሀገራት መላክ” ወደሚለው ቁርጠኝነት ተሸጋግሯል:: ለእዚህ ታላቅ ውሳኔ መነሻና መሠረት የሆነውም ፈጣን ለውጥ የታየበት የበጋ መስኖ ልማት ስለ መሆኑ ነጋሪ አያሻውም::
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ በስንዴ የበጋ እርሻ ልማት የመጀመሪያው ምዕራፍ ብቻ በ4 ሺህ 400 ሄክታር መሬት ላይ በተሸፈነ ዘር 16 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ለማግኘት ተችሏል:: በተመሳሳይ በሁለተኛው ምዕራፍ በነበረው ሂደትም በ 2 መቶ 8 ሺህ ሄክታር መሬት የዘር ሽፋን 8 ነጥብ 35 ሚሊዮን ኩንታል በመሰብሰብ የለውጥ ታሪክን መመዝገብ ተችሏል::
ይህ ታላቅ የለውጥ ምዕራፍ ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራሷን ለመቻል አንገት የሚሆናትን ጥንካሬ ማሳያ ሆኖ ተመዝግቧል:: ከእዚህ የለውጥ ምዕራፍ ማግስትም ሀገራችን ወደ ምዕራባውያን ጎተራዎች እጇን የመዘርጋት ታሪኳን ሽራ ለሌሎች ሀገራት ጭምር “እጀ ሰፊ” የምትሆንበትን ብርታት ማረጋገጥ ችላለች::
ለስንዴ ምርት ውጤታማነት የሚያግዙ መሳሪያዎች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ መደረጋቸው ለውጡን ያለ ዕንቅፋት ለመከወን ካስቻሉት ምክንያቶች መሀል ይጠቀሳል:: በበጋ ወቅት አርሶ አደሮች የሞተር መሳቢያን በመጠቀም፣ ወንዞችን በመጥለፍና ከከርሰ ምድር ውሃን በማውጣት ለልማት ሥራው ማዋላቸውም ለምርታማነቱ ስኬት በዋቢነት የሚነሳ ነው:: ዘመናዊ የመስኖ አሠራሮች ዕውን መሆንን ጨምሮ ለበርካታ አርሶ አደሮች የብድር አገልግሎት ማመቻቸት ፣ ተገቢነቱ ታምኖበት በተግባር መከወኑ ደግሞ የልማት መንገዱ ቀና እንዲሆን ዋንኛ ምክንያት ነበር ::
ኢትዮጵያ እንደ ፈረንጆቹ ቀመር በ2023 ከባሕር ማዶ የምታስገባውን የስንዴ ምርት ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረት ዕቅድ ይዛ ተንቀሳቅሳለች:: ይህ ዕቅድም እንደታለመለት ግብ ሆኖ ዘመኑን ሳይሻገር ዕውን መሆን ችሏል:: ለእዚህ ዓላማ ስኬታማነት ከጅማሬው በወጉ የተነደፉ ትልሞች ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አበርክተዋል::
ሀገራችን “በምግብ እህል ራስን መቻል” በሚል ቁርጠኝነት መንቀሳቀሷን ተከትሎ ሌሎች ወሳኝ ጉዳዮችን ለመተግበር የሚያስችል መሠረት ተጥሏል:: በእዚህም ከውጭ ሀገራት የሚገቡ ምርቶች በሀገር ውስጥ እንዲሟሉ መወሰኑ፣ የሀገር ውስጥ ምርቶች ወደውጭ ሀገራት እንዲላኩ መታቀዱና ሥራ ላጡ ወገኖች ሠርቶ የመኖር ዕድል መመቻቸቱ ጭምር የዕቅዱን ጥንካሬ አጉልቶ አሳይቷል::
የበጋ መስኖ ልማት በስንዴ ምርት ላይ መተግበሩ ኢትዮጵያ ከራሷም በላይ ለሌሎች ሀገራት ጭምር የምግብ ዋስትናን እንድትፈጥር የሚያስችል ነው:: አሁን ባለው ወቅታዊ መረጃ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ስንዴን በብዛትና በጥራት በማምረት ቀዳሚዋ ሀገር ሆናለች:: ይህንንም እውነት በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ዶ/ር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መድረክ ላይ በግልጽ ያረጋገጡት ሀቅ ሆኗል::
በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ የተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች በበጋ መስኖ ተጠቃሚ በመሆናቸው ያስገኘላቸውን በረከት እየመሰከሩ ነው:: በዓመት አንድ ጊዜ በአንድ የምርት አይነት ብቻ የሚታወቁት አምራቾች አሁን በበጋ መስኖ ልማት በረከታቸው ሰፍቶ ጎተራቸው ተትረፍርፏል::ለእዚህ ታላቅ ስኬት ደግሞ ከመንግሥት እጆች የሚደረጉላቸው ተፈላጊ ድጋፎች አስተዋጽኦውን አልቆታል::
ከእዚሁ ጎን ለጎንም አዲስ የአሠራር ሂደትን በመለማመድ ምርትን አፈራርቆ ለመዝራትና ፍሬያማ ውጤትን ለማግኘት መንገዱን አስፍቷል:: ሁሉም እንደሚያምነው የበጋ መስኖ ልማት የኢትዮጵያን የቀድሞ መልክ የሚቀይርና የተረጂነት ታሪኳን የሚሽር እውነት ነው:: እፍኝ ስንዴን በመለገስ ብቻ ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን ለመሙላት ለሚሹት ጥቅመኛ ሀገራትም እጅን በአፍ የሚያስጭን ታሪክን ለማሳየት በቂ እማኝ ይሆናል::
በበጋ ወራት በመስኖ ስንዴን አምርቶ በእልፍ ማፈስ አሁን ላይ የኢትዮጵያ ብርቅዬ ታሪክ አልሆነም:: በየክልሉ በሚገኙ ወረዳዎችና የገጠር ቀበሌዎች ሁሉ አሠራሩ ተተግብሮ ውጤታማነቱን ማስመስከር ይዟል:: አሁን በየትኛውም ስፍራ በሚሊዮን ኩንታሎች የሚመዘን የስንዴ በረከት ማፈስ የልፋት፣ ድካም ልዩ ሽልማት ሆኖ የአርሶ አደሩን ፍላጎት እየሞላ ነው::
ከምንም በላይ ኢትዮጵያ ሀገራችን በእዚሁ አይደበቄ እውነታ ስሟን ከአፍሪካ ሀገራት በላይ ከፍ አድርጋ ሰቅላለች:: ይህ ደማቅ ስም ደግሞ በአጋጣሚ የተገኘ ዕድል አይደለም:: ልክ እንደትናንቱ ጠንካራ ክንዶች ተጋምዶበታል፤ ላብና ዕውቀት ተከፍሎበታል::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16 ቀን 2017 ዓ.ም