
– ለልማት ሥራው ከአንድ ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል
አዲስ አበባ፡– ኢትዮጵያውያን የጎንደር ከተማን የቀደመ ክብርና ዝና ለመመለስ ለሚከናወኑ የልማት ሥራዎች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ጥሪ አቀረበ፡፡“ ኑ ጎንደርን እንሞሽር” የተሰኘ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው፤ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብሩን አስመልክተው ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ጎንደርን በማልማት የቀደመ ታሪኳን የሚመጥን ቁመና ላይ እንድትገኝ ለማድረግ እየተሠራ ነው።ለእዚህም ደግሞ መላው ኢትዮጵያውያን ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
በመጀመሪያው ምእራፍ አንድ ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ተከናውኖ መጠናቀቁን አመላክተው፤ በምእራፍ ሁለት የኮሪደር ልማት ደግሞ ከአጼ ቴዎድሮስ አውሮፕላን ማረፊያ እስከ ፒያሳ አጼ ቴዎድሮስ ሐውልት ያለውን ስፍራ እንደሚያካትት ገልጸዋል።
ለሥራው ከአንድ ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ መርሃ-ግብሩም ይህን ሀብት ለማሰባሰብ ያለመ ነው ብለዋል፡፡
የኮሪደር ልማት ይዟቸው ከመጣ በረከቶች አንዱ የሥራ ባሕል ለውጥ ነው ያሉት ከንቲባው፤ በከተማዋ በቀን ለ22 ሰዓታት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ተናግረዋል።በእዚህም ሥራውን እስከ መስከረም 2018 ዓ.ም ድረስ ለማጠናቀቅ አቅደን እየሠራን ነው ብለዋል፡፡
ብዙ ኢትዮጵያውያን በጎንደር ትናንት ኮርተው በዛሬ ቁመናዋ ያፍራሉ ያሉት ከንቲባው፤ ጥሪው ከተማዋን ወደ ቀደመ ከፍታዋ በመመለስ እንደ አባቶቻችን ልጆቻችን የሚኮሩበትን ሥራ ሠርተው ለማለፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የጎንደር ኋላ ቀርቶ መኖር ልክ እስኪመስለን ተኝተን ነበር ያሉት አቶ ቻላቸው፤ ጨለማው ላይ አብርተው፣ ከዛሬ ነገ ፈረሰ ብለን የተጨነቅንበትን ቅርስ አስጠግነው “ለካ ጎንደር ልማት ይገባታል፤ ያምርባታልም እንድንል ላደረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ማመስገን ያስፈልጋል።ጅምሩን ለመቀጠል፣ የጎንደር ወርቃማ ዘመንን ለመመለስ የተለኮሰው ብርሃን እንዳይጠፋ ከተማችሁን አብረን መልሰን እንሠራት ዘንድ “ኑ” ስንል ጥሪ አቅርበናል ብለዋል።
ጎንደር በአንድም በሌላም የቀደመ ታሪኳ ከሀገራችን ታሪክ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጋር የተቆራኘ መሆኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያውያን ያንን ታሪክ ከጎንደር ልማት ጎን በመቆም ዳግም እንዲያረጋግጡ ጠይቀዋል፡፡
የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብሩ ሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 10:00 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ሸራተን አዲስ ሆቴል እንደሚካሄድ ጠቅሰው፤ መላው ኢትዮጵያውያን፣ በሀገር ውስጥና በመላው ዓለም የሚገኙ የጎንደር ተወላጆች፣ የተለያዩ የሀገራት ኤምባሲዎችና ተቋማት እንዲሳተፉ አቶ ቻላቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16 ቀን 2017 ዓ.ም