
አዲስ አበባ፡– ቦይንግ የአፍሪካ ቢሮውን በአዲስ አበባ መክፈቱ ዓለም አቀፋዊ ራዕያችንን ለማሳካት ወሳኝ ርምጃ መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ ዓለሙ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ እያደገ የመጣ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ አቅም መፍጠሯን ጠቅሰው፤ በብሔራዊ ትራንስፖርት ካውንስል የሚመራ የዘርፉን መሠረተ-ልማት ለማዘመን፣ የትራንስፖርት ንግድ ወጪን ለመቀነስ እና አፍሪካን ለማስተሳሰር የሚያስችል የአስርት ዓመታት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በዘርፉ የ10 ዓመት የልማት እቅድ ላይም በባቡር፣ በወደብ ልማት፣ በአቪዬሽንና በስማርት ሎጂስቲክስ ዘርፍ እንደ ቦይንግ ካሉ የግል ሴክተሮች ጋር በጋራ የምንሠራበት የ74 ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት እቅድ መቀመጡን ተናግረዋል።
የቦይንግ ኩባንያ አመራር በኢትዮጵያ ላይ ባሳደረው እምነት አመስግነው ፤ይህንን አጋርነት የአውሮፕላን ክፍሎችን በማምረት፣ ስልጠናዎችን በመስጠትና በዘላቂ የአቪዬሽን ነዳጅ ላይ በትብብር በመሥራት አጋርነታችንን እናሳድግ ብለዋል፡፡
በጋራ ሆነን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ወደ ዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለት መሪነት ከፍ ማድረግ እና አዲስ አበባን የአፍሪካ የኤሮስፔስ ፈጠራ ማዕከል ማድረግ እንችላለን ሲሉም ገልጸዋል።
የቦይንግን የአፍሪካ ቢሮ በአዲስ አበባ ስንከፍት የኢትዮጵያ ሰማይ ድንበር ሳይሆን መግቢያ በር መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል ያሉት ሚኒስትሩ፤ለኢኮኖሚ ነፃነት፣ ለአህጉራዊ አንድነት፣ ለዓለም አቀፋዊ አቪዬሽን እድገት አፍሪካ ድርሻዋን እንድትወጣ በማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የቦይንግ የመካከለኛው ምሥራቅ፣ ቱርክ፣ አፍሪካና ማዕከላዊ ኤዥያ ፕሬዚዳንት ሚስተር ኩልጅት ጋታ፣ በኢትዮጵያ አሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ፣ የኢትጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰውና ሌሎች የኩባንያው አመራሮች መገኘታቸው የትራስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16 ቀን 2017 ዓ.ም