በካዛንቺስ የተገኘው ውጤት በእጅጉ የሚያኮራ ሥራ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጹ

የካዛንቺስ ኮሪዶር ልማት በይፋ ተመረቀ

አዲስ አበባ፦ በካዛንቺስ ኮሪዶር ልማት የተገኘው ውጤት በእጅጉ የሚያኮራ ሥራ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር ) ገለጹ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የካዛንቺስ የኮሪዶር ልማት ሥራን በይፋ መርቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር ) ትናንት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሰው የድካሙንና የላቡን ፍሬ ይበላል የሚለው ሃሳብ በካዛንቺስ ሥራ ግልጥ ብሎ ይታያል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ካዛንቺስ የነበረው መልክ ዛሬ ከምናየው ጋር በእጅጉ የተራራቀ ነው፡፡ ለእይታ ፣ ለኑሮና በብዙ መልኩ ለሰው ልጅ ምቹ የማይባል አካባቢ እንደነበር አውስተዋል፡፡

የሁለተኛው ዙር የኮሪዶር ልማት ካዛንቺስን ያካተተ ሆኖ መጀመሩን ገልጸው፤ በጥቂት ወራት ውስጥም በካዛንቺስ የተገኘው ውጤት በእጅጉ የሚያኮራ ሥራ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከካዛንቺስ የተነሱ ወገኖች ያሉበትን ሰፈር መመልከታቸውን አስታውሰው፤ ቀደም ሲል ሲኖሩበት የነበረው ከአዲሱ የኑሮ ልምምድና የአኗኗር ዘዬ አኳያ ሲታይ በእጅጉ የተሻለ መሆኑን ገልጸዋል።

አካባቢው ለልጆቻቸው መማሪያ፣ ወጥቶ መግቢያ ፣ መጫወቻ እና በርካታ ነገሮችን የያዘ ቢሆንም፤ ያለቀ ሥራ ባለመሆኑ ከእዚህ በላይ መዘመን እና መሻሻል ይችላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ግን ከነበራቸው ኑሮ እና ሰፈር አንጻር ፍጹም ሊወዳደር አይችልም፡፡ እድል አግኝቼ ያነጋገርኳቸው ሰዎች ያረጋገጡልኝም ይህንን ነው፡፡ በብዙ መልኩ አሁን ያለው ሁኔታ የተሻለ መሆኑን ገልጸውልኛል ብለዋል፡፡

ለተነሺዎች የተሻለ ቦታ ከተዘጋጀ በኋላ ካዛንቺስን እንዲህ ባለ መልክ የተሻለ አድርጎ መሥራት በጣም አስፈላጊ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በኮሪዶር ልማት የካዛንቺስን ለውጥ ሰዎች ማየት ያለባቸው ለራሳቸው ካላቸው ክብር፣ ሰዎች ስለእነሱ ካላቸው እይታ አንጻር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ካዛንቺስ ከእዚህ ቀደም የነበረ ሁኔታ ለረጅም ጊዜ ጥርሱን ሳይፍቅ የቆየ ሰው የሚያሳየው ዓይነት ፈገግታ፤ ለረጅም ጊዜ ማበጠሪያ ጸጉሩን ሳይነካው የቆየ ሰው በጸጉሩ ላይ የሚታየው ዓይነት ገጽታ፤ ለረጅም ጊዜ ሳይታጠብ ያልታጠበ ልብስ ለብሶ የምናየው ዓይነት ምልክት ነበረች፡፡ ዛሬ ታጥባና አምራ ባለ ግርማ ሞገስ ሆና ማየት ለእኛ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ለሕዝባችንም ትልቅ ኩራት መሆን አለበት ነው ያሉት፡፡

በየትኛውም ሀገር የሚታየው ዘመናዊነት፣ ለውጥና መሻሻል የሚገለጸው በእዚህ መንገድ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የዘመኑ የሚባሉ ከተሞች አረንጓዴና ንጹህ የሆኑ ከተሞች መሆናቸውን አብራርተዋል።

የከተማችን ነዋሪዎች መገንዘብ ያለባቸው ከነበርንበት አውድ ሁኔታ ወደ ሚያምረው ሁኔታ ለመውጣት እልህ አስጨራሽ ትጋት ይጠይቃል ሲሉም ገልጸዋል።

ሀገራችንን ለማሳደግና ልጆቻችን ተስፈኞች እንዲሆኑ የበለጸገች ሀገር መሥራት እንዲችሉ የተከፈለ ዋጋ መሆኑንም መረዳት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሀገራችንን የመገንባት፣ የማነጽ ፣የማስዋብ ሥራው ተስፋችንን፣ ሕልማችንንና ንግግራችንን ወደ መሬት አውርዶ የማሳየቱ ጉዳይ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

ለእዚህም በየደረጃው ያሉ አመራሮች በትጋት በመፍጠርና በመፍጠን መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

በአሁኑ ወቅት ትጋት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ በትጋት አንድ ደረጃ ስንደርስ የሚቀጥለውን ማለም እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

የኮሪዶር ልማቱ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኩራት መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በእዚህ ዘመን የዘመኑ የሚባሉት ከተሞች አረንጓዴና ንጹህ ሆነው ጥሩ የአየር ሁኔታ ያላቸው ናቸው፤ ውሃ ንጹህ ሆኖ ሳይሸት የሚፈስባቸው፤ ሳር በቅሎ የሚታይባቸው፣ ልጆች የሚጫወቱባቸው መስኮች ሲኖሩ ያ የዘመነ ከተማ ያሰኛል ሲሉ አብራርተዋል።

በጣም የሚያስደስተው ነገር ሥራው የተሠራው በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው። የከተማችን ነዋሪዎች መገንዘብ ያለባቸው አንድን ነገር አፍርሶ ሌላ መገንባት ገንዘብ፣ ኅብረት፣ ቁርጠኝነትና ጊዜ ማስፈለጉን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከነበርንበት አውድ ከነበርንበት ሁኔታ ወደእዚህ የሚያምር ሁኔታ መለወጥ እልህ አስጨራሽ ትጋት ጠይቋል። ያ ሥራ ያ ትጋት ደግሞ ጉሰማ እንደሚኖረው ነው የገለጹት፡፡

ይህ ሥራ መቀጠል አለበት፤ ሀገራችንን የመገንባት የማነጽ የማስዋብ የማሳመር ተስፋችን ሕልማችን ንግግራችንን ወደ መሬት አውርዶ የማሳየቱ ጉዳይ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ እንዲሆን በየደረጃው ያሉ አመራሮች መጠንቀቅ ያለባቸው እርካታ የሚባል በሽታ እግር እጃቸውን አስሮ እንዳይንቀሳቀሱ ሊያደርጋቸው አይገባም። መርካት በሽታም እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ተግተን ሠርተን አንድ ደረጃ ስንደርስ የሚቀጥለውን ማለም እና መሥራት እንጂ መቆም ተገቢ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጊዜ የለንም፤ የተሰጠንን ጊዜ አክብረን የምንፈጥር፣ የምንፈጥን ካልሆነ በቀር የምናስበውን ብልፅግና ልናረጋግጥ አንችልም ነው ያሉት፡፡

የኮሪዶር ልማት ሥራው ከእዚህ ቀደም ግራ የገባው ወይም ያልገባው ሰው አሁን ካዛንቺስ መጥቶ ሲያይ ጥላቻ ከሌለው በቀር ሀገሩን የሚወድ ዜጋ ከሆነ በቀና መንገድ ማየትና መደገፍ እንደሚጠበቅበት አመልክተው፤ ምክንያቱም ይሄ ለማንም ሳይሆን ለሁላችንም ነው፡፡ ለልጆቻችን የሚተርፍ እንደ ሀገር የምንመኘውንና ክብር የሚያጎናጽፍ ሥራ ስለሆነ በእዚህ መንገድ ኢትዮጵያውያን እንዲያዩት አደራ ለማለት እወዳለሁ ብለዋል፡፡

በጣም የሚያስደስት ሥራ ነው፤ እኛ ብዙ ደክመንበታል ለፍተንበታል ፍሬውንም ውጤቱንም እጅግ ያማረና የሚቀጥል እንደሆነ ገልጸው፤ ኢትዮጵያ በልጽጋ ልጆቻችን ተስፋ ተሞልተው ከልመና ተገላ ግለን፣ የኮራን ሕዝቦች እስከምንሆን ድረስ በተሰጠን ጊዜ በብርታትና በትጋት በመሥራት አዳዲስ ውጤቶችን እናመጣለን ብለዋል፡፡

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You