የዘገየ ፍትሕን ታሪክ ያደረጉ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች

ፍርድ ቤቶች ሕግን የመተርጎም ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮ የተሰጣቸው የመንግሥት አካላት ናቸው፡፡ የእነዚህ ፍርድ ቤቶች ተደራሽ መሆን፤ አሠራራቸው መሻሻሉና ገለልተኛ መሆናቸው የሀገሪቱን የፍትሕ ሥርዓት ለማሻ ሻል ያስችላል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ይህን ታሳቢ አድርገው በስፋት ወደ ሥራ ከገቡ ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ፍርድ ቤቶቹ የመደበኛ ፍርድ ቤቶችን ጫና በመቀነስና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት በመስጠት እያገለገሉ ነው፡፡ እውነትን በማውጣትና ፍትሕ በማስፈን፣ የተከራካሪ ወገኖች ማህበራዊ መስተጋብር መልሶ እንዲያንሰራራ በማድረግ ረገድም የሚጫወቱት ሚና እየጎላ እንደመጣ ይገለጻል።

ማህበረሰቡ በመደበኛ ፍርድ ቤቶች በፍትሐ ብሔርም ሆነ በወንጀል ጉዳይ የሚያጋጥሙት እንግልትና የፍርድ መጓተት ችግሮች በባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ተፈትተው ፈጣን ውሳኔ በማግኘቱ ተጠቃሚ ስለመሆኑም የዘርፉ ባለሙያዎች ያብራራሉ።የሕግ ተመራማሪው አቶ ሚልኪ መኩሪያ እንደሚያስረዱት፤ ፍርድ ቤቶቹ የፍትሕ አሰጣጥ ሂደትን ተከትሎ የሚያጋጥሙ አለመግባባቶችን ለመፍታት ያስችላሉ፤ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች በፍትሕ አሰጣጥ ሂደቱ ተግዳሮት ሆኖ የቆየውን ሀሰተኛ ምስክርነት ይቀንሳሉ፤ የክልሉ ሕዝብ ፍትሕን በቅርበትና በእውነት ላይ ተመስርቶ እንዲያገኝም ያግዛሉ።

በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተርና የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ ፈይራ ኃይሉ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶቹ በመደበኛው ፍርድ ቤት የነበረውን ጫና እያቃለሉ እንደሚገኙ ይገልጻሉ።እሳቸው እንደሚሉት፤ ከእዚህ በፊት ለኦሮሚያ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ጉዳዮች በየዓመቱ ይጨምሩ ነበር።ባሕላዊ ፍርድ ቤቶቹ እየሰፉና ተደራሽ እየሆኑ ከመጡበት ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ግን ጉዳዮቹ በተወሰነ ደረጃ እየቀነሱ መጥተዋል።

የመጀመሪያ ደረጃ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች በ2015 ዓ.ም ለ209 ሺህ 270 እንዲሁም በ2016 ዓ.ም ደግሞ ለ287 ሺህ 165 መዝገቦች ውሳኔ መስጠት ችለዋል።ይግባኝ ሰሚ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ደግሞ በ2016 ዓ.ም ከ15ሺህ በላይ ለሚሆኑ መዝገቦች ውሳኔ ሰጥተዋል።ይህም ከ2015 ዓ.ም ከነበረው አፈጻጸም የአምስት ሺህ 933 መዝገቦች ልዩነት አለው ነው ያሉት።

ይህም ለመደበኛ ፍርድ ቤቶች የሚቀርበውን ፋይል ብዛት እንዲቀንስ በማድረጉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞች የቀረበላቸውን ጉዳይ ከመጨናነቅ ነፃ ሆነው በጥራት እንዲያዩ እገዛ ስለማድረጉ እና ፈጣን ውሳኔ እንዲሰጡ ስለማስቻሉም ያብራራሉ።

በአዳማ ባሕላዊ ፍርድ ቤት ኅብረተሰቡን በመዳኘት አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት አባ ገዳ ተስፋዬ ደቻሶ ኩምሳ በበኩላቸው፤ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶቹ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥና የዜጎችን መብት በማስከበር ረገድ ተመራጭ እየሆኑ ስለመምጣታቸው ያስረዳሉ።በተለይም ነፍሰ ጡሮች፣ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች ያለምንም እንግልትና ወጪ በአቅራቢያቸው አገልግሎት እያገኙባቸው እንደሆነም ይናገራሉ።

እንደ አቶ ፈይራ ገለጻ፤ “የባሕል ፍርድ ቤቶች መዝገቦችን ከእጃቸው የማጣራት አቅም እያጎለበቱ መምጣታቸው፤ መፍትሔ እየሰጧቸው የሚገኙ ግላዊና ማህበራዊ ችግሮች ብዙ መሆኑን የሚያረጋግጥልን ነው” ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ምስክርነት የሰጡለት ውጤታማ ተግባር ስለመሆኑም ይገልጻሉ።

የባሕላዊ ፍርድ ቤቶቹ ቁጥጥርም እየጨመረ እንደመጣ አቶ ፈይራ ይናገራሉ።በክልሉ ካሉ ሰባት ሺህ 481 ቀበሌዎች ውስጥ በስድስት ሺህ 913 ቀበሌዎች ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች እንዲሁም በ333 ወረዳዎች ደግሞ 355 ይግባኝ ሰሚ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ተቋቁመው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።ፍርድ ቤቶቹ በክልሉ አገልግሎቱን መስጠት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ መዛግብት ውሳኔ በመስጠት የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት እያገዙ ይገኛሉ።

አቶ ፈይራ “ፍርድ ቤቶቹ በማህበረሰቡ ዘንድ ለዘመናት ሲሠራባቸው የነበሩ እንጂ አዲስ አይደሉም።የገዳ ሥርዓት በውስጡ ከያዛቸው ሥርዓቶች ውስጥ የሚካተቱ ናቸው።ሥርዓቱ የማስታረቅ፣ አለመግባባቶችን በእርቅ የመጨረስ፣ የበደለን የመቅጣት እና የተበደለን የመካስ አሠራሮችን ይይዛል።ግጭቶች ሲኖሩ በማህበረሰቡ ውስጥ በባሕላዊ መልኩ፣ በእነዚህ ዓይነቶቹ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች የመጨረስ ጉዳዮች ነበሩ።ሆኖም እነዚህን የማስፈጸም እና ጉልበት እንዲኖረው የማድረግ ሥራ አልነበም” ይላሉ።

ከእዚህ አኳያ ተቀዛቅዞ የነበረው ባሕል እውቅናና የሕግ ሽፋን አግኝቶ እንደገና ወደ ሥራ በመገባቱ እና ከአምስቱ ዳኞቹ መካከል አንዷ ሴት መሆን እንዳለባትም በሕጉ በመደንገጉ ማህበረሰቡ ሙሉ እምነቱን ጥሎ እየተገለገለባቸው እንደሚገኝ ያብራራሉ።

ሀደ ሲንቄ ወርቅነሽ ጎፋ በፍርድ ቤቶቹ የዳኝነት አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።የፍርድ ቤቶቹ ተገልጋዮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ስለመምጣቱ ያስረዳሉ።በእዚህም ምክንያት ቀድሞ ከነበረው በተጨማሪ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ቀናት መጨመራቸውንም ይገልጻሉ።“ተገልጋዩ የሚመጣው በልበ ሙሉነት ተማምኖባቸው ነው።“ንብረቴን ያስመልሱልኛል፣ ከባላንጣዬ አስማምተው በሰላም እንድኖር ያደርጉልኛል፣ትክክለኛ ፍትሕ አገኝባቸዋለሁ ብሎ በማመን ነው” ይላሉ።

አባገዳ ተስፋዬ ደቻሶ እንደሚሉት፤ በባሕላዊ ፍርድ ቤት በክህደት የሰው ንብረት ዘርፎ የሚቀር ሰው የለም።ፍርድ ቤቱ ከአያትና ቅድመ አያት ጀምሮ በመወራረስ የመጣ እና ባሕልንና ዕምነትን መሠረት አድርጎ የሚሠራበት በመሆኑ ማኅበረሰቡ በእጅጉ ያከብረዋል።በፍርድ ቤቱ ተሰይመው ለሚዳኙት አባገዳዎችና ሀደ ሲንቂዎችም ከፍተኛ ክብር ይሰጣል።“በመደበኛ ፍርድ ቤት እስከ ሰበር ሰሚ ድረስ በገንዘብና በሌሎች መንገዶች ተጠቅሞ በሀሰት አስወስኖ የመጣ ቢሆንም እንኳ ባሕላዊ ፍርድ ቤት ሲቀርብ እውነቱን ይናገራል” ይላሉ።

የክልሉ ነዋሪዎች ከእዚህ ቀደም ፍትሕ ለማግኘት ሲሉ ለከፍተኛ እንግልትና ወጪ ሲዳረጉ ቆይተዋል።ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ከመደበኛና ከማህበራዊ ፍርድ ቤቶች ጎን ለጎን አገልግሎት እንዲሰጡ እና ከዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓት ጋር እንዲጣጣሙ የሚያስችል እውቅና የሚሰጣቸው አዋጅ በጨፌ ኦሮሚያ ፀድቆ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ክልል ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያ ለሚገኙ ባሕላዊ የዳኝነት ሥርዓቶች እውቅና የሚሰጥና ከዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓት ጋር እንዲጣጣሙ የማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ተመልክቷል።ይህም ፈጣን የፍትሕ ሥርዓት ተደራሽ ለማድረግ ያግዛል፤ ወጪ ቆጣቢና እንግልትን የሚያስቀር የፍትሕ ሥርዓት እንዲኖር ይረዳል ሲሉ ባለሙያዎቹ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

ሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You