
ከግብፅ መንግሥት ጋር በምሥጢር በመሥራት ጉቦ በመቀበል ተከሰው እስር የተፈረደባቸው የቀድሞው የአሜሪካ ምክር ቤት አባል ሮበርት ሜኔንዴዝ ሚስት በባለቤታቸው የረዥም ጊዜ የሙስና ተግባራት ውስጥ ተባባሪ በመሆን ጥፋተኛ ተባሉ።
የቀድሞው የኒው ጀርሲ እንደራሴ ሚስት የሆኑት ናዲና ሜኔንዴዝ በኒው ዮርክ ዳኛ ጥፋተኛ የተባሉት ባለቤታቸው ፖለቲካዊ ውለታ ለመዋል ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ፣ ጥፍጥፍ ወርቅ እና ውድ ተሽከርካሪ ከተቀበሉባቸው እና ለዓመታት ሲፈጽሟቸው በነበሩት የጉቦ ወንጀሎች ውስጥ ተሳትፎ ነበራቸው በሚል ነው የ58 ዓመቷ ናዲን ሜኔንዴዝ ጥፋተኛ የተባሉት። ባለቤታቸውን በመደገፍ ጉቦ መቀበልን እና ፍትሕን ለማደናቀፍ መሞከርን ጨምሮ በ15 ክሶች እንደሆነ ተገልጿል።
ግለሰቧ ክስ የተመሠረተባቸው ከባለቤታቸው ጋር ከሁለት ዓመት በፊት ቢሆንም የፍርድ ሂደቱ እንዲዘገይ የተደረገው በነበራቸው የጡት ካንሰር ሕክምና ምክንያት ነው። ባለቤታቸው ሮበርት ሜኔንዴዝ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ላይ የ11 ዓመት እስር የተፈረደባቸው ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔ ለማሳለፍ ለሰኔ ወር ቀጠሮ ይዟል። በኒውዮርክ የሚገኘው የአሜሪካ ዐቃቤ ሕግ ባወጣው መግለጫ፤ ባል እና ሚስቱ “ሥልጣንን ለብልሹ ጥቅም በማዋል” ተሳታፊ በመሆን “የወንጀል አጋሮች ናቸው” ብሏል።
ጨምሮም “የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የመንግሥት ባለሥልጣናት የተሰጣቸውን ሥልጣን ለሽያጭ ማቅረብ እንደማይችሉ ግልጽ መልዕክት ያስተላለፈ ነው” ሲል ግለሰቦቹ ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀማቸውን አመልክቷል። በፍርድ ሂደቱ ወቅት ዐቃቢያነ ሕጎች ሚስት በባላቸው የጉቦ ድርጊቶች ውስጥ ወሳኝ ቦታ እንደነበራቸው የሚቀርቡ ሥጦታዎችን እና ገንዘብን የሚቀበሉት እሳቸው እንደነበሩ ለዳኛው አስረድተዋል።
ሚስት ጉቦዎችን ይቀበሉ ነበር በተባለበት ጊዜ ባለቤታቸው ሮበርት ሜኔንዴዝ ኃያል በሆነው የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ባለው የአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ውስጥ ዲሞክራቶችን ወክለው ከአምስት ዓመታት በላይ ሠርተዋል።የተከሳሿ ጠበቆች በቤታቸው ውስጥ የተገኘውን ወርቅ እና የገንዘብ ክምር “ከኃላፊነታቸው ጋር” የሚገናኝ ስለመሆኑ የሚያሳይ ማስረጃ መንግሥት አላቀረበም ሲሉ ተከራክረው፣ ጥፋተኛ መባላቸው እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።
የምክር ቤት አባሉ ሜኔንዴዝ እና ሚስታቸው በአሜሪካ ምክር ቤት ውስጥ ባላቸው ሚና የመንግሥትን ሥልጣን በመጠቀም በምሥጢር የግብፅ መንግሥት ጥቅም በሚያስጠብቅ ሰፊ ተግባራት ውስጥ በመሳተፍ መከሰሳቸውን ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።መንግሥት ኒውጀርሲ ግዛት ውስጥ በሚገኘው በግለሰቦቹ ቤት ውስጥ በ2022 በኤፍቢአይ በተደረገ ፍተሻ 100 ሺህ ዶላር ዋጋ ያላቸው የወርቅ ጥፍጥፎች እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ዶላር ማግኘቱን እንደማስረጃ አቅርቧል።
በተጨማሪም በባልና ሚስቶቹ እና በሌሎች ተባባሪዎቻቸው መካከል የተደረጉ የጽሑፍ መልዕክት ልውውጦች እና ባል የቀድሞው የምክር ቤት አባል “አንድ ኪሎ ወርቅ ስንት ያወጣል? በማለት በጉግል ላይ ያደረጉትን ፍለጋ የሚያሳዩ ማስረጃዎች ቀርበዋል። በኒውጀርሲ የቤቶች ግንባታ ድርጅት ባለቤት ፍሬድ ዳይቢስ እና ግብፃዊው ዋኤል ሃና በዚሁ ከጉቦ ቅሌት ጋር ተያያዘ ከጥንዶቹ ጋር ክስ ቀርቦባቸዋል።
ሌላ የኢንሹራንስ ደላላ የሆነው ጂሴ ኡሪቤም ከእዚሁ የጉቦ ክስ ውስጥ ስሙ የነበረ ሲሆን፤ ባለፈው ዓመት መጋቢት ላይ በተሳትፎው ጥፋተኛ መሆኑን አምኗል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 15 ቀን 2017 ዓ.ም