ለብሔራዊ ምክክሩ ስኬት የፖለቲካ ኃይሎች ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለእውነት እና ለእርቅ ዝግጁ ነው። ለዓመታት ሰላምን፣ ኢኮኖሚን ማህበራዊ ትስስርን በሚጎዱ ግጭቶች ውስጥ መቆየትን አይሻም። የከረሙ ችግሮች የሕዝቡን አንድነት፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እየፈተኑና እዚህም እዚያም ግጭቶችን ሲጠምቁ ይስተዋላል። በዚህ እኩይ እሳቤ ውስጥ መቆየት የሕዝቡ ምርጫ ሳይሆን የጥቂት የፖለቲካ አመለካከት ዝንፈት የገጠማቸው ቡድኖች ህልም ነው። ለዚህ ነው ከግጭት ይልቅ ሰላምን፣ ከድህነት ይልቅ ልማትን፣ ከመለያየት ይልቅ አብሮነትን የሚፈጥር የጋራ ምክክር የሚያስፈልገው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተስፋ ሰጪ ውይይቶች እያየን ነው። ሁሉንም አመለካከቶች በሰላማዊ መንገድ ለማስተናገድ የሚያስችል ሥርዓት (የምክክር መድረክ) ለመፍጠር እየተሞከረ ነው። ይህ ተግባር ፍፁምነት ባይኖረውም ፅንፍ የረገጡ መሳሳቦችን ለማቀራረብና ያረጀና የከረመ ትርክትን በገንቢ ትርክት ለመቀየር የሚያስችል አደረጃጀት የሚፈጥር ነው።

መንግሥትና የምክክር ኮሚሽኑ ለዚህ ሀገራዊ ውይይት መሠረት እያዘጋጁ ነው። ይህ ምክክር የፖለቲካ ቡድኖች የሚመክሩበት የጥቂቶች ስብሰባ ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያ መላው ሕዝቦቿን አሰባስባ በአንድነት ወደፊት የምትራመድበት ለመጪው ትውልድ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትና ልምምድ የሚበጅበት ታላቅ ትልም ነው።

በቅርቡ ኮሚሽኑ ከሁሉም ክልሎች አጀንዳዎችን ማሰባሰብ ጀምሯል። ይህ የሚያሳየው የሕዝብን ድምጽ መስማት ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ነው። በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ የኮሚሽኑ አመራሮች የተለያዩ ማኅበረሰቦችን ፍላጎቶች እና ስጋቶች ለመረዳት እየሞከሩ ነው። የሀገራዊ ምክክር ዓላማ ይህ እንደመሆኑ መጠን አካታች መድረክ እና አጀንዳን ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ሊደነቅ ይገባል።

ከሌሎቹ የኢትዮጵያ ክፍሎች በተለየ የዘገየና በርካታ ተግዳሮቶች ያሉበት ቢሆንም ባለፉት ጥቂት ቀናት በአማራ ክልል አጀንዳ ማሰባሰብ ሲካሄድ ቆይቷል። ይህ ርምጃ ለምክክሩ ስኬታማ መሆን በጣም አስፈላጊ ነው። የክልሉ ነዋሪ የዘመናት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ጥያቄዎች ተስፋና ስጋቶች እንዲሁም የሕዝቡ ድምጽ ወደ ሀገራዊው ውይይት መድረኩ እንዲመጣ ያስችላል።

ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት በአማራ ክልል ለሀገራዊ ምክክሩ ግብዓት የሚሆን አጀንዳ በማሰባሰብ ሂደት ውስጥ በርካታ ፈተናዎች እየገጠሙ ነው። ከዚህ ውስጥ አንዱና ዋነኛው ፈተና በክልሉ የግጭት መንገድ የመረጡ ተቃዋሚ ቡድኖች መኖራቸው ነው። በዚህ በያዝነው 21ኛ ክፍለ ዘመን ምርጫ ሊሆን የማይችልና ከሌሎች የፖለቲካ ቡድኖች ጋር ከመነጋገር ይልቅ የሰው ሕይወትና ደም አፋሳሽ መንገድን መርጠው ይገኛሉ። ይህ ተግባር የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን ሥራዎች በተሟላ መንገድ እንዳይሳካ ከማድረጉም ባሻገር ከመንግሥት ጋር ግጭት አለመረጋጋት ፈጥሯል።

በክልሉ እስካሁን በቀጠለው ግጭት የተነሳ ነዋሪዎች ክፉኛ ለስቃይ እየተዳረጉ ይገኛሉ። በአንዳንድ ቦታዎች ተማሪዎች ትምህርታቸውን ተረጋግተው እንዳይማሩ እና ውጤታማ እንዳይሆኑ እክል ፈጥሯል። በቅርቡ በክልሉ ተገኝተው የመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ የገጠሙ ሳንካዎችን ያነሱት የትምህርት ሚኒስትሩ ይህንን ሀቅ መናገራቸውን እናስታውሳለን። ግጭቱ ምክክሩ ላይ ጋሬጣ ከመሆን፣ ትምህርትን ከማስተጓጎል ባሻገርም ኢኮኖሚውን ክፉኛ እየጎዳው ይገኛል። አርሶ አደሮች ሰብል ለማምረት እንዳይችሉ፣ ማዳበሪያ በሚፈልጉት ልክና ጊዜ እንዳያገኙ፤ በክልሉ የሚታየው ግጭት ምክንያት እየሆነ ነው። በጥቅሉ በአካባቢው ላሉ ነዋሪዎች ሁሉ ሕይወት ከባድ ሆናለች።

ጦርነት መቼም መፍትሔ ሆኖ አያውቅም። የትጥቅ ትግል የፖለቲካ ችግሮችን አይፈታም። በርግጥ ሕዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው። ነገር ግን እነዚህ ጥያቄዎች በጠመንጃ ሊመለሱ አይችሉም። በፍፁም ቅንነት ውይይት ብቻ ነው መመለስ ያለባቸው። ተቃዋሚ ቡድኖች እና ሌሎች የፖለቲካ ተዋናዮች በጋራ ለውይይት ተቀምጠው መፍትሔ ማግኘት ይችላሉ፤ እርስ በርሳቸው መግባባት ይችላሉ። ሕዝቡንም ሆነ መላው ኢትዮጵያውያን ወደ ሰላማዊ እና ወደ ተሻለ ተስፋ መውሰድ ይችላሉ። ለዚህ ነው የምክክር ኮሚሽኑ ሥራዎችን ከሚያደናቅፉ ተግባራት መቆጠብና ለውይይቱ መስመር ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ማበርከት የሚገባው።

አሁን ብሔራዊ እርቁን እና የምክክር መድረኩን በሙሉ አቅም፣ ያለ ምንም ሳንካ ለመጀመር እድሉ አለ። ይህን መሰል ሀገር የማረጋጋት አጋጣሚ ዳግም ላይገኝበት የሚችልበት እድል አለ። ቢኖር እንኳን ይህንን አጋጣሚ ማባከን ፈፅሞ አይገባም። ሁሉም ቡድን፣ እያንዳንዱ መሪ እና እያንዳንዱ ማኅበረሰብ በዚህ ውይይት መሳተፍ አለበት። ምክክሩ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት ብቸኛው መንገድ ነው። ሥር የሰደዱ ችግሮችን ለመፍታትም ብቸኛው አማራጭ ነው።

በአማራ ክልል ለሚገኙ ኃይሎች ብቻ ሳይሆን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በዚህ ውይይት ውስጥ መሳተፍ ጥቅሙ ብዙ ነው። በመጀመሪያ እያንዳንዱ ቡድን የሚያሳስበውንና ዋና ጉዳይ ነው ብሎ የሚያቀርበውን ጥያቄና የፖለቲካ ልዩነት በግልፅ ጠረጴዛ ዙሪያ እንዲያካፍል ያስችለዋል። በዚህ መድረክ ሁሉም ሰው ጠረጴዛው ላይ መቀመጫ ይኖረዋል። በሁለተኛ ደረጃ ምክክር ማድረጉና የጋራ ውይይትን ፍቃድ መስጠቱ በተለያዩ ቡድኖች መካከል መተማመንን ለመፍጠር ይረዳል።

እንደሚታወቀው በፖለቲካ ቡድኖች መካከል ለረጅም ጊዜ ፍርሃት እና አለመተማመን አለ። ስለዚህ በምክክር መድረኩ ላይ ተሳትፎ በግልጽ ሃሳቦችን ማንሳትና መናገር እነዚህን ግድግዳዎች ለማፍረስ ይረዳል። ሶስተኛው መሠረታዊው ጥቅም የግጭትና የጦርነት አዙሪት እንዲቆም ማስቻሉ ነው። ሰዎች በውይይት ችግራቸውን መፍታት ከቻሉ የትጥቅ ትግል፣ ክቡሩን የሰው ልጅ ሕይወት ማጥፋት አያስፈልጋቸውም። በቀላሉ ውይይትና ምክክር በማድረግ መግባባትን ማምጣት ይቻላል። ለዚህ ነው የአማራ ክልል ውስጥ የትጥቅ ትግልን ምርጫቸው ያደረጉ ኃይሎች ወደ ምክክር መድረኩ ለመምጣት ፈቃደኛ መሆን አለባቸው የሚል ጠንካራ ሃሳብ ማንሳት የምፈልገው።

ይህ እድል በተለይ ለአማራ ክልል በእጅጉ ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ። ክልሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተከሰተው ግጭት ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል አንዱ ነው። ብዙ ሰዎች ቤታቸውን አጥተዋል፤ ብዙዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቀለው እርስታቸውን ለቀው እንዲወጡ ተደርገዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች ጭራሹኑ ልጆች ትምህርት ቤት መሄድ አይችሉም፤ በተመሳሳይ ገበያዎች ባዶ ናቸው። ሰዎች ተደጋጋሚ ግጭት ባለባቸው ቦታዎች በፍርሃት ይኖራሉ። ለዚህ ነው ክልሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰላም ያስፈልገዋል የምለው።

ግጭትን እንደ አማራጭ የያዙ ኃይሎች ሃሳባቸውን ወደ ጎን ትተው ምክክሩ ላይ ተሳታፊ መሆናቸው ሰላማዊ ከባቢን ከመፍጠር አንስቶ ብዙ ጥሩ ነገሮችን ያመጣል። የተፈናቀሉ ገበሬዎች ወደ እርስታቸው ይመለሳሉ። ልጆች ወደ ትምህርት ቤት ይመለሳሉ፤ ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን ይከፍታሉ፤ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ ይሰማራሉ። የትራንስፖርት አግልገሎት በሰላማዊ መንገድ ይጀምራል፤ ሕዝቡ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር መብቱ ይጠበቃል፤ የጤና አገልግሎት ይመለሳል። ቀስ በቀስም ሕይወት ወደ መደበኛው መንገድ ይመለሳል። ለዚህ ነው ሰላማዊ መንገድ ሁሌም አትራፊ የሚሆነው።

በቅርቡ በአማራ ክልል የተካሄደው አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራ በጣም ጥሩ ርምጃ ነው። የክልሉ ሕዝብ ሰላም እንደሚፈልግ አንዱ ማሳያ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል። ከዚህም ባሻገር የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጥያቄዎቹ በመድረኩ እንዲሰሙ መፈለጉን ያመለክታል። በጥቅሉ ሁሉም የሀገሪቱ ችግሮቻቸው በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ይፈልጋል። የምክክር ኮሚሽኑ እነዚህን ድምጾች በቁም ነገር ሊመለከተው ይገባል። እነዚህ አጀንዳዎች በወረቀት ላይ ያሉ ቃላት ብቻ አይደሉም፤ የሕዝቡ ተስፋዎች ናቸው። የእናቶች፣ የአባቶች፣ የተማሪዎች እና የገበሬዎች ህልሞች ናቸው።

እነዚህን የሕዝብ ድምጾች ችላ ማለት ብዙ ችግሮችን ያመጣል። ለዚህ ነው መንግሥትም እውነተኛና ሃቀኛ ሰላም ከፈለገ ድምፆቹን በጥሞና ማዳመጥ የሚኖርበት። ጠመንጃን እንደ አማራጭ የተመለከቱ ቡድኖችም በእውነት ለሕዝቡ የሚያስቡ ከሆነ ከጠመንጃ ይልቅ ውይይትን መምረጥ ይኖርባቸዋል። ይህ ሰላማዊ ኢትዮጵያን በዘላቂነት ለመገንባት ብቸኛው መንገድ ነው። ብሔራዊ ውይይት (ምክክር) ሂደቱ ቀላል አይደለም፤ ስኬት ላይ እንዲደርስ ትዕግስት ያስፈልገዋል፤ ከሁሉም ወገን ታማኝነት ያስፈልገዋል። ሰዎች ከሚናገሩት በላይ አዳማጭ መሆናቸውን ማሳየት ይኖርባቸዋል።

ለዓመታት ኢትዮጵያ በመከፋፈል ተጎድታለች። የኢትዮጵያ ሕዝብ በፖለቲካ ትግልና አለመግባባት ተጎድቷል። ይሁን እንጂ ከዚህ ችግር ውስጥ የመውጫ አሁንም እድል አለ። የሀገሪቱን አንድነት አስጠብቆ እንደገና ወደ ልማትና እድገት ለመገስገስ እድሉ አለ። ሕንፃዎች እና መንገዶች ብቻ በሰዎች መካከል መተማመን እና ፍቅር አይገነቡም፤ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህንን መረዳት አለባቸው። ትልቁን ምስል ማየት ይኖርባቸዋል። ኢትዮጵያ የአንድ ቡድን ወይም የአንድ ክልል ብቻ አይደለችም፤ የሁሉም ሀገርና መኖሪያ ነች። ይህ ቤት ጠንካራ እንዲሆን ሁሉም ሰው በጋራ መሥራት አለበት። ምክክር፣ ውይይት እና ቀናነት ደግሞ ለስኬታማነቱ ቀዳሚዎቹ መሠረቶች ናቸው።

የውይይት ሂደቱ መድረክ ነው። መድረክ ለሃሳቦች መንሸራሸር አስተማማኝ ቦታ ነው። ጥያቄዎች የሚነሱበት፣ የሕዝቡ ጥልቅ ጥያቄና ህመም የሚጋራበት እና መፍትሔ የሚያገኙበት ቦታ ነው። ይህ ሂደት መጠበቅ እና መከበር አለበት፤ በተለይ ደግሞ የተሳታፊዎች ምጣኔን መጠበቅና አካታች መሆን አለበት። በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ማንም ሰው እንደተገለለ ሊሰማው አይገባም። ይህንን ለማረጋገጥ ሚዲያዎች ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባል፤ የውይይት አጀንዳዎችን ለሕዝቡ ማሳወቅ አለባቸው።

ለሰላማዊ ሃሳቦች ቦታ መስጠት አለባቸው። የሚከፋፍሉ መልዕክቶችን ማስወገድ አለባቸው። ጋዜጠኞች ፍርሃትን ሳይሆን ተስፋን በመገንባት ላይ ማተኮር አለባቸው። ሲቪል ማኅበረሰብም መሳተፍ አለበት። የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና ሴቶች ሁሉም ሚና አላቸው።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ተሳታፊ መሆን አለበት። ቴክኒካል ድጋፍ በመስጠት፣ የገንዘብ ድጋፍ እና ሰላማዊ ተሳትፎን በማበረታታት ይህንን ሂደት መደገፍ ይችላል። እውነተኛው ምክክርና ሥራ ግን በኢትዮጵያውያን በራሳቸው መሠራት አለበት። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ነች።

በአማራ ክልል ያሉ ነፍጥን እንደ አማራጭ የሚመለከቱ ኃይሎች ይህንን ሊያስቡ ይገባል። ስለሚቀጥለው ትውልድ ማሰብ ይገባቸዋል። ምን ዓይነት ሀገር ነው ልንገነባ የምንፈልገው? በጥላቻ የተሞላች ምድር? ወይንስ በእድሎች የተሞላች ሰላማዊት ኢትዮጵያን? መልሳችን ሁለተኛው ከሆነ አሁኑኑ ርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል። ሰላምን መምረጥ ይኖርባቸዋል። ውይይት መምረጥ ሁለተኛ አማራጭ ሊሆን አይገባም።

የጦርነት ጊዜ ሊያበቃ የሰላም ጊዜ አሁን ሊሆን ያስፈልጋል። ይህ ብሔራዊ ውይይቱን አዲሱና ሰላማዊው መንገድ ነው፤ የተስፋ በር ነው። የአማራ ክልል ተቃዋሚዎችን ጨምሮ ሁሉም ቡድኖች በዚህ በር መሄድ ይገባቸዋል።

ጊዜ ማባከን አያስፈልግም። የአማራ ልጆች ትምህርት ቤቶች ያስፈልጓቸዋል። ገበሬዎች ዘር ያስፈልጋቸዋል። እናቶች ክሊኒኮች ያስፈልጋቸዋል፤ ወጣቱ ሥራ ይፈልጋል። እነዚህን ነገሮች በጦርነት ውስጥ ማሳካት አይቻልም፤ ሰላም ይፈልጋሉ። ለዚህ ነው ውይይትን፣ ሰላምን እንምረጥ የምንለው። ሰላም!!

ሰው መሆን

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You