
የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በመፈረሙ የትግራይ ሕዝብ እረፍት አግኝቷል። የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ተመስርቷል። የፌዴራል መንግሥት እንደ መብራት፣ ቴሌኮም እና ባንክ ያሉ መሠረተ ልማቶችን በመጠገን መንግሥታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥራዎች እንዲከናወኑ እንዲሁም ያልተገደበ የሰብዓዊ ርዳታ አቅርቦት ተደራሽ እንዲሆኑ አድርጓል። መንግሥት ኃላፊነቱን በአግባቡ በመወጣት ለሰላምና ለስምምነቱ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር አሳይቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አሕመድ ዐቢይ (ዶ/ር) ሌ/ ጄነራል ታደሰ ወረደ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ሆነው መሾማቸውን አስመልክተው በማህበራዊ ድረ ገጽ ባጋሩት ጽሑፍ፤ ላለፈው አንድ ወር ገደማ የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት፣ የፕሪቶርያን ስምምነት እና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡን ምክር በማከል ሰፊ ውይይቶች ሲካሄዱ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
የአቶ ጌታቸው ረዳ የሥልጣን ዘመን በሕጉ መሠረት ሲያበቃ፤ የሚቀሩ ቁልፍ ሥራዎችን ለማከናወን ጊዜያዊ አስተዳደሩ መቀጠል አለበት የሚል ድምዳሜ ላይ በመደረሱ ማን ሽግግሩን መርቶ ከግብ ሊያደርስ ይችላል የሚለው ታይቶ ሌ/ጄነራል ታደሰ ወደ ቦታው መጥቷል። በጠቅላይ ሚኒስትሩም እንደተገለጸው፤ ጄኔራል ታደሰ ባለፋት ሁለት ዓመታት የቀድሞ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት፣ ጌታቸው ረዳ ምክትል ሆነው ያገለገሉ ሰው በመሆናቸው፤ ባለፉት በአስተዳደሩ ውስጥ የነበሩ ጥንካሬዎችን እና ድክመቶችን ጠንቅቀው የሚያውቁ ሰው ናቸው።
ሌ/ጄነራል ታደሰ የተረከቡትን ታሪካዊ ኃላፊነት የተወጡበት የሕዝብ ሰቆቃ እስከወዲያኛው እንዲያበቃ ለማድረግ ከሠሩበት ስማቸውን በደማቅ ቀለም ጽፈው በታሪክ ተወዳሽና ተጠቃሽ ይሆናሉ። በአንጻሩ በቀድሞ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ በነበረው መከፋፈል ውስጥ የነበረው ፖለቲካዊ ሥልጣንን እና ወታደራዊ አገዛዝን የመቀላቀል አዝማሚያ እንዲቀጥል መደላደልን የሚፈጥሩ ከሆነ ክልሉ ወደ ሌላ አለመረጋጋት ውስጥ እንዲገባ በር የሚከፍቱ ይሆናል ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሌ/ጄነራሉን ሹመት አስመልክተው ያስተላለፉትን አጭር መልዕክት የቋጩበት መንገድ መንግሥት ያለውን ስጋት የሚያመላክት ይመስላል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳባቸውን የቋጩት፤ የትግራይ ሕዝብ የጠማውን ሰላም እና ልማት፣ እንደ ሌሎች ወንድሞቹ ወጥቶ የመግባት መሻት ስናሳካ፣ ለኢትዮጵያም ለአፍሪካም እጅግ ጠቃሚ የሆነ ነገር ሠርቶ ለማለፍ ታሪክ የሰጣቸውን ዕድል እንደሚጠቀሙበት ተስፋ አደርጋለሁ ብለው ነው። አዲሱ ሰው ምርጫው በእጃቸው ነው።
ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ሚያዝያ 1 ቀን 2017 ባደረገው ስብሰባ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለማዊ ሁኔታዎችን ገምግሞ ባወጠው መግለጫ፤ የትግራይ ሕዝብ የሚፈልገውን ያህል ሰላም አለማግኘቱን ጠቅሷል። ሕዝቡ የተሟላ ሰላም ያላገኘው በአንዳንድ ወገኖች የተለየ ዓላማ ምክንያት መሆኑንም ይገልጻል።
የፕሪቶሪያውን ስምምነት በመጣስ የኃይል ርምጃን አማራጭ አድርጎ በመንቀሳቀስ፣ ከውጭ ኃይሎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር እና ጠብ አጫሪ ፕሮፓጋንዳዎችን ለመንዛት በሚሞክሩበት ወቅት በታሪክ አጋጣሚ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን የመምራት ዕድል የገጠመው አካል በኃይል ወደ ስልጣን መመለስን ግቡ አድርጎ የሚንቀሳቀስ ቡድንን ፍላጎት ለማስፈጸም ሳይሆን በጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ያስተናገደውን የትግራይ ሕዝብ ማዕከል አድርጎ በኃላፊነት ስሜት የተጣለበትን አደራ መወጣት አለበት።
በአቶ ጌታቸው ረዳ እግር የተተኩት ሌ/ጄነራል ታደሰ ኃላፊነቱን ሲቀበሉ፤ የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር የተልዕኮ አፈጻጸም የቃል ኪዳን ሰነድ መፈረማቸው ግልጽነት እና ተጠያቂነት እንዲኖር የሚያደርግ ነው። በቃል ኪዳን ሰነዱ በግልጽ የተቀመጡት በተለይም የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ሂደት፣ በጅምር ያለው እንዲጠናቀቅ እና በቀሪ አካባቢዎችም በፍጥነት እንዲተገበር ማድረግ፤ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ትጥቅ የመፍታት እና የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋም ተግባር በአፋጣኝ እንዲጠናቀቅ ማድረግ፣ በክልሉ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ማድረግ፣ ለሕዝብ ደኅንነት፣ ለሰላም እና ለጸጥታ ጠንቅ የሆኑ ጉልህ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ማድረግ፣ ለእዚህም ተገቢውን የቁጥጥር እና የሕግ ማስከበር ሥራ መሥራት የሚሉት አንገብጋቢ ጉዳዮች በዝርዝር መጠቀሳቸው የጊዜያዊ አስተዳደሩን ወሳኝ ሥራዎች ቆጥሮና ሰፍሮ የመስጠት ስልጡን አካሄድ ነው።
በተጨማሪም መደበኛ የልማት ሥራዎች፣ መንግሥታዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶች፣ እንዲሁም የመልሶ ግንባታ ሥራዎች እንዲሳለጡ ማድረግ፣ ከሕገ መንግሥታዊ እና ከሕጋዊ ሥርዓት፣ ከሀገር_ሉዓላዊነት እና ከፕሪቶሪያ ስምምነት ያፈነገጡ ግንኙነቶች እና እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ማድረግ፣ ክልሉ ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዝግጁ እንዲሆን ማድረግ፣ በክልሉ የሲቪክ እና የፖለቲካ መብቶች ተግባራዊ የሆኑበት፣ የፖለቲካ ብዝኃነትን የሚያስተናግድ ዴሞክራሲያዊ ዐውድ እንዲፈጠር መሥራት፣ የክልሉ ሕዝብ፣ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች እና የፖለቲካ ተዋንያን በሀገራዊ የምክክር ሂደት እንዲሳተፉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንዲሁም የክልሉ መንግሥታዊ የሚዲያ እና የኮሙኒኬሽን እንቅስቃሴዎች የሀገሪቱን ሕዝቦች ትስስር እና መልካም ግንኙነት የሚያጠናክሩ፣ ሕግ እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን የሚያስከብሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ የሚሉት ተግባራትም ሌ/ጄነራል ታደሰ አስተዳደር ኮምፓሶች ናቸው።
ሌ/ጄነራሉ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት በመሆን ሥራቸውን ሲጀምሩ፤ የተዘረዘሩትን ኃላፊነቶች በታማኝነት ለመወጣት ቃል ገብተው ፊርማቸውን ማኖራቸው በፌዴራል መንግሥቱም ሆነ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዓይን አስተዳደራቸው የሚመዘንበት ሚዛን በአደባባይ መረጋገጥ የሚችል አድርጎታል። ለእዚህ አንዱ ማሳያ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቭን ሆሴ ማሲንጋ አዲሱ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ሌ/ጀኔራል ታደሰ ወረደ ከሰሞኑ በተካሄደው ይፋዊ የሥልጣን ርክክብ ወቅት የፈረሙትን “የተልዕኮ አፈጻጸም የቃል ኪዳን ሰነድ” አክብረው እንዲያስከብሩ ከአደራ ጭምር ምክራቸውን መለገሳቸው ነው።
በሌላ በኩል መንግሥት አቶ ጌታቸው ረዳ ላለፉት ሁለት ዓመታት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር በመሆን ላበረከቱት አስተዋጽኦ በአደባባይ ምስጋና በማቅረብ በክብር መሸኘቱ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው። በርካቶች ትግራይ ክልል ውስጥ በነበረው ገመድ ጉተታ የተፈጠረው ውጥረት በየትኛውም ሰዓት ወደ ኃይል ርምጃ ሊሸጋገር ይችላል የሚል ስጋት ነበራቸው። ፌዴራል መንግሥት ነገሩን በስክነትና በብስለት በመመልከት ያለ አንዳች ኮሽታ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር እንዲካሄድ ያደረገበት መንገድ የሚደነቅ ነው። የቀድሞ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት እና ተተኪው ተሿሚ በአደባባይ የኃላፊነት ርክክብ ማድረጋቸው ለመላው ኢትዮጵያውያን ትልቅ ትርጉም ያለው የዴሞክራሲ እምርታ ነው።
መግነጢስ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 15 ቀን 2017 ዓ.ም