“የሥራ እድል የተፈጠረልን ቦታ በሊዝ ጨረታ መሸጡ በቀጣይ የሥራ ሕልማችን ላይ ስጋት ፈጥሮብናል” – የሥራ እድል የተፈጠረላቸው የወረዳ 04 ወጣቶች

> “ቦታው ለጨረታ ስለወጣ የሥራ ዕድል ፈጠራው እዚህ ላይ ተቋርጧል የሚል ሃሳብ አይኖርምም”- – ክፍለ ከተማው
> “ወጣቶቹ በልማትና በሰላም ግንባታ ያላቸው ተሳትፎ ለማህበረሰቡ አርአያ በመሆኑ ባይነሱ እንመርጣለን”–የአካባቢው ነዋሪዎች

አዲስ አበባ– በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የወረዳ 4 ነዋሪ የሆኑ የጀሀን ገላን መኪና እጥበትና አረንጓዴ ልማት ማህበር ወጣቶች፣ የሥራ እድል የተፈጠረልን ቦታ በሊዝ ጨረታ መሸጡ በቀጣይ የሥራ ሕልማችን ላይ ስጋት ፈጥሮብናል ሲሉ አቤቱታቸውን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አቀረቡ።

ቦታው ለጨረታ ስለወጣ ነገ ወጣቶችን ዜጋ አይደላችሁምና የሥራ ዕድል ፈጠራው እዚህ ላይ ተቋርጧል የሚል ሃሳብ የለም ሲሉ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የክፍለ ከተማው አመራሮች ምላሽ ሰጥተዋል።

በማህበር የተደራጁ ወጣት አዲሱ ነጋሽ፣ ኤልያስ ኑሩ፣ ሌንጮ አብደላ፣ ቶፊቅ መሃመድ እና ነስራ አብደላ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የምርመራ ቡድን ቅሬታቸውን ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ጀሀን ገላን የመኪና እጥበትና አረንጓዴ ልማት የሚል ማህበር መስርተው በተመቻቸላቸው የሥራ እድል ሲሠሩ ቆይተዋል።

የመሥሪያ ቦታቸውን በብዙ ድካምና ጥረት ለዓመታት ሲያስተካክሉትና አትክልትና ፍራፍሬ በመትከል ሲንከባከቡ ቆይተው የድካማቸውን ፍሬ ለመብላት እየተዘጋጁ ባሉበት ሁኔታ ምንም በማያውቁት ሁኔታ ያሉበት ቦታ ለጨረታ በመቅረቡ ድካማቸውም ሕልማቸውም አደጋ ላይ መውደቁን ገልጸዋል።

የዛሬ አምስት ዓመት በአቃቂ ቃሊቲ ወረዳ አራት 31 ቦታዎችን መርጦ ወጣቶችን አደራጅቶ እንደነበር የገለጹት ወጣቶቹ፣ በወቅቱ እነርሱ የመረጡት ቦታ ወንዝ ዳር የሆነና ቆሻሻ ስፍራ ሲሆን፤ ከቆሻሻነቱ የተነሳ የአካባቢው ነዋሪ በእዚያ ስፍራ ለማለፍ ይቸገር እንደነበር አስታውሰዋል። ይሁንና በቁርጠኝነት እናለማዋለን በማለት በጠየቁት መሠረት ቦታው እንደተሰጣቸው አስታውሰዋል።

ቦታው ቀድሞ ወረዳ አራት ይገኝ የነበረ ቢሆንም፤ ከስምንት ወር በፊት ወደ ወረዳ 12 የተካለለ መሆኑን የጠቆሙት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ አካባቢው የሞተ ፈረስና ውሻ እንዲሁም ፈርስና ቆዳ መጣያና የሌቦች መሸሸጊያ ከመሆኑ የተነሳ ሰዎች በእዚያ በኩል ማለፍ ይቸገሩ ነበር ብለዋል።

ቆሻሻ አለመጣልን ባሕል ለማድረግ በብዙ ጥረትና ልፋት አካባቢው ንጹህና ሰላም የሰፈነበት እንደሆነም አመልክተዋል። ሥራውን ሲያከናውኑ ቦታውን ከመፍቀድ ውጪ ለአምስት ዓመት በሙሉ ከመንግሥት ምንም ዓይነት ድጋፍ እንዳላገኙ ተናግረዋል።

ቦታው በተሻለ ሁኔታ በመጽዳቱም የአካባቢው ሰው ደስተኛ ከመሆኑም ባሻገር ማንበቢያ ስፍራም አድርጎ እየተገለገለበትም ሲሆን፤ የተከሉት አትክልትና ፍራፍሬ ፍሬ እስኪሰጣቸው ድረስ ከመኪና እጥበት በሚያገኙት ገቢ እየተዳደሩ መሆኑን አመልክተዋል።

የደከሙበት ቦታ ግን በአሁኑ ወቅት ምንም እውቅና ሳይኖራቸው፣ የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም በወጣው አዲስ ልሳን ጋዜጣ ላይ ለጨረታ መቅረቡን የጠቀሱት ወጣቶቹ፣ ይህንንም የተረዱት ጨረታውን መወዳደር የሚፈልጉ ባለሀብቶች ቦታውን ለማየት በሚመጡበት ጊዜ እንደሆነ ተናግረዋል።

ወጣቶቹ በሰፈሩ በበጎ ፈቃደኝነት የሚሳተፉ፣ ቤተሰብ የሌላቸውን ሰዎች ድጋፍ በማስተባበርና በጸጥታ ላይ በቋሚነት ለአካባቢው ሰላም መከበር ከጸጥታ ኃይሉ ጋር የሚተባበሩ መሆናቸውን አስረድተዋል። መንገድ ላይ የጸጥታን ጉዳይ ለመከታተል ፖሊስ የተከላቸው ካሜራዎችንና የኮሙኒቲ ፖሊስ ስልክ በቋሚነት ካርድ እንደሚሞሉ የገለጹት ወጣቶቹ፤ በዓል በመጣ ቁጥር ለአራት ያህል ቤተሰብ ድጋፍ እንደሚያደርጉም አብራርተዋል። ለአምስት ሰዎችም የሥራ እድል ፈጥረናል ብለዋል።

ቦታው ተላልፎ ሊሰጥ መሆኑን ሲሰሙ የሚመለከተውን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ፣ የከተማ ውበትና የአረንጓዴ ልማት ጽሕፈት ቤትን ቢጠይቁም ኃላፊው፣ እንደእዚያ አይነት ቦታ ስለመኖሩ፣ ወጣቶቹ ስለማልማታቸውና ጨረታም ስለመውጣቱ እንደማያውቁ መግለጻቸውን ጠቅሰው፤ ነገር ግን ኃላፊው ባለሙያ ልከው ቦታውን እንዲያዩ ካስደረጉ በኋላ ለወጣቶቹ የሰጧቸው “ስላለማችሁት እግዚአብሔር ይስጥልኝ” የሚል አጭር መልስ እንደሆነ ወጣቶቹ ተናግረዋል። አክለውም ማባረርም ማንሳትም የእኛ ድርሻ ነው” ሲሉ ምላሽ እንደሰጧቸውና ምላሹም ሕልምን የሚገድል አይነት እንደሆነ ተናግረዋል።

ከእድሜያችን አምስት ዓመት ተቀንሶብናል፤ ከእዚህስ በኋላ እጣ ፈንታችን ምንድን ነው ሲሉ ጠይቀው፤ በቆይታቸው ግን አካባቢውን ጽዱ በማድረግ፣ በአካባቢ ጸጥታ ላይ ከፖሊስ ጋር በመተባበር፣ ማዕድ በማጋራት እንዲሁም በተለያየ መስክ ተባባሪ በመሆን ላደረጉት እንቅስቃሴ በአቃቂ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ያሉ የተለያዩ ጽሕፈት ቤቶች የተለያየ ሰርተፍኬት እንደሰጧቸውም አስረድተዋል።

ወጣቶቹ ከአካባቢያቸው እንዳይሄዱ ፊርማ ካሰባሰቡ 300 ያህል ሰዎች መካከል አቶ አብደላ አቡበከር፣ ወይዘሮ ማርታ ታዬ፣ አቶ ኪሩቤል መለሰ ወይዘሮ ሳሙኤላ ወልደስላሴ፣ አቶ ሶሎሞን ደምመላሽ፣ አቶ ማቲያስ ሐጎስ፣ አቶ ኪዳነ ግርማ እና አቶ አይናለም ሸንተማ ሲሆኑ፤ “በጽዳቱም ሆነ በሰላሙም ብርቱ በመሆናቸው ከቦታቸው ባይነሱ እንመርጣለን” ሲሉ ተናግረዋል።

ነዋሪዎቹ ምስክርነታቸውን በሰጡበት ወቅት እንዳስረዱት፤ ቦታው የሰፈሩ ቆሻሻ ሁሉ የሚጣልበት ስፍራ ነበር። ወጣቶቹ ግን ሳይጠየፉ አጽድተው የልጆቻቸው ማንበቢያና መዋያ አድርገውላቸዋል። በመሆኑም ቅዳሜና እሑድ ልጆቻቸው መጽሐፍ ያነብባሉ። አምስትና ስድስት ዓመታት በእዚህ ቦታ ለፍተዋል፤ የተከሉትን አትክልት ሳይቀምሱ ተነሱ መባላቸው ግን አስደንግጧቸዋል።

ወጣቶቹ እኛን የአካባቢውን ሰዎች የጠቀሙንን ያህል ራሳቸውን አልጠቀሙም ያሉት ነዋሪዎቹ፤ ሰሞኑን አረንጓዴ የሆነው አካባቢ ተመንጥሮ ሕንጻ ሊሠራበት ነው መባሉን ስንሰማ የቆጠርነው ቤታችን የተደረመሰ ያህል ነው። በእርግጥ መንግሥት የሚንቀሳቀሰው በፕሮግራም ነው፤ ነገር ግን ደግሞ የእነዚህን ልጆች የሥራ ጥንካሬ በማየት መፍትሔ ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል።

ወጣቶቹ ጊዜያዊ ጥቅምን መሠረት ሳያደርጉ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብለው ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ሲሆኑ፤ ዝቅ ብሎ መሥራትንም ለአካባቢው ማኅበረሰብ ማስተማራቸውን አስረድተዋል።

በቃሊቲ ክፍለ ከተማ የወረዳ 04 ሥራና ክህሎት የአንድ ማዕከል ሥራዎች አስተባባሪ አቶ ፍቅሬ ከበደ በበኩላቸው፤ በጀሀን የመኪና እጥበትና አረንጓዴ ልማት ማህበር ስም የተደራጁ ወጣቶች በሥራ አጥነት ስለመደራጀታቸውና ሕጋዊ ስለመሆናቸው ተናግረዋል። ከእዚህ በፊት ወረዳ 12 እና ወረዳ 04 አንድ ወረዳ የነበሩ ሲሆን፤ በሪፎርሙ ለሕዝብ ምቹ አገልግሎት ለመስጠት ሲባል ወደ ወረዳ አስራ ሁለት መካለሉን ገልጸዋል።

ወጣቶች የሥራ እድል የፈጠሩበት ቦታ በፊት ከዚነት ዘይት ፋብሪካ የሚለቀቅ ፍሻስ የሚጨመርበት ወንዝና የቆሻሻ መጣያ እንደነበር የገለጹት አስተባባሪው፤ ቦታውን በማጽዳት እንዲለማ አድርገውታል። በወጣቶቹ ጥረት በከፍተኛ ደረጃ የተለወጠ ስፍራ ነው ብለዋል።

ከ2016 ህዳር አንድ ጀምሮ ወደ ወረዳ 12 እስከተጠቃለሉበት ድረስ ሕጋዊና ተጠሪነታቸው ለወረዳው ሥራና ክህሎት ጽሕፈት ቤት ሆኖ ሲሠሩ መቆየታቸውን አስተባባሪው አስረድተዋል።

በቃሊቲ ክፍለ ከተማ የወረዳ 04 ሰላምና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከበደ በለጠ በበኩላቸው፤ በሥራ ዕድል ፈጠራ ጽሕፈት ቤት ይሠሩ በነበሩበት ወቅት፤ በጀሀን ገላን የመኪና እጥበትና የአረንጓዴ ልማት በሚል የተደራጁ ወጣቶች ወደ እርሳቸው ቢሮ መጥተው እንደነበር ጠቅሰዋል።

በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ የሚያደራጀው የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ጽሕፈት ቤት ስለሆነ በወቅቱ እንዲሄዱ እንደነገሯቸውና ሄደው ምን እንደወሰዱ ግንዛቤው ባይኖራቸውም የሥራ እድል የፈጠሩበት አካባቢ አሁን ወደነበረበት ደረጃ እንዳደረሱት ገልጸዋል።

ከፍተኛ ቆሻሻ የሚጣልበት ስፍራ እንደነበር የገለጹት አቶ ከበደ፤ ቆሻሻውን በማጽዳት የአካባቢው ማህበረሰብ ጭምር የሚዝናናበት ቦታ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። አሁን የሚሠሩበት አካባቢ ወደ ወረዳ 12 የተካለለ ቢሆንም ወጣቶቹ ግን በቦታው እየሠሩ ነው። “እንደ ግለሰብ ቦታው ድረስ በመሄድ ጎብኝቼ በርቱ ብያቸዋለሁ”። ነገር ግን የአካባቢ ጥበቃና ከተማ ውበት ቦታውን ለአረንጓዴ ልማት መስጠትና አለመስጠቱን የማውቀው ነገር የለም ሲሉ አብራርተዋል።

እርሳቸው እንዳሉት፤ ቦታው ለጊዜው ቆሻሻ እየተጣለበት ክፍት ሆኖ ከሚቀመጥ ለሥራ ዕድል ፈጠራ በጊዜያዊነት ይጠቀሙ የሚል ሃሳብ ስለነበር ተደራጅተው ሥራ እየሠሩበት ይገኛሉ። መሬቱን የመውሰድ ሥልጣን ያለው የአዲስ አበባ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ስለሆነ ሲፈለግ መሬቱን ለሕጋዊ አካል ሊያስተላልፍና ሕጋዊ ሰነድ ይዘው ሲመጡ የማስለቀቅ ሥራ እንሠራለን።

ወጣቶቹ በልማትና በጸጥታው ዘርፍ ጥሩ እየሠሩ ናቸው። ከሚያገኙት ገቢ ቀንሰው እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ከተማ ለሚደረግ የድጋፍ ጥሪ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ብለዋል።

“መሬት የመንግሥትና የሕዝብ መሆኑ ይታወቃል።” ያሉት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በመሬት ልማትና አስተዳደር የመሬት ባንክና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ስዩም ደስታ በበኩላቸው፤ ከተማ አስተዳደሩ በየጊዜው የሊዝ ጨረታዎችን ያወጣል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለ5ኛ ዙር ጨረታ ወጥቶ ተጠናቅቋል ብለዋል። ቅሬታ የተነሳበት ቦታም ሁለት ብሎክ ላይ ጨረታ በኮድ ቁጥር 241 እና በኮድ ቁጥር 242 ወጥቷል። የቦታ ስፋታቸው አንድ ሺህ 225 ካሬ ሜትርና አንድ ሺህ 309 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው ቦታዎች ጨረታ ወጥተው ሰው ጎብኝቷቸዋል ብለዋል።

እንደ ቡድን መሪው ገለጻ፤ ቅሬታ አቅራቢዎች የነበራቸው ጊዜያዊ የመጠቀሚያ ፈቃድ ነው። ለጊዜያዊ መጠቀሚያ የተሰጠው ቦታ ለተሻለ ልማት ሲፈለግ እንደሚነሱ ውል ገብተዋል። ጨረታ የሚወጣው ደግሞ በፕላን መሠረት ነው። የቦታው ፕላን የሚያሳየውም ቅይጥ የመሬት አጠቃቀምን ነው።

አረንጓዴ የተባሉ ቦታዎች ፕላንና ካርታ አላቸው። ስለዚህ ይህ ቦታ ለአረንጓዴ የተተከለ ቢሆን ኖሮ መንግሥትም አይነካውም፤ በፕላኑ አረንጓዴ የሆነ ቦታ ጨረታም አይወጣበትም። ነገር ግን ቦታው ቅይጥ የተባለ ሲሆን፤ ለንግድ ወይም ለመኖሪያ የሚሆን እንደሆነ ገልጸዋል። የአረንጓዴ ቦታዎችን የሚወስነው የአዲስ አበባ ፕላን ኮሚሽን ቢሮ እንደሆነም አስታውሰዋል።

ይሁንና ቦታው ለተሻለ ልማት ስለዋለ ነገ ወደ ሥራ አጥነት ይሄዳሉ ማለት አይደለም። በሌላ ቦታ የሥራ እድል ይፈጠርላቸዋል እንጂ ዜጋ አይደላችሁም የሥራ ዕድል ፈጠራው እዚህ ላይ ተቋርጧል የሚል ነገር የለም ብለዋል። ሥራ ያልነበራቸውን ወደ ሥራ እያመጣ ያለ ተቋም ሥራ የነበረውን ሰው አፈናቅሎ ወደ ሥራ አጥነት አይመልስም። ከእዚህ አኳያም ይሠሩበት ወደነበረው ዓይነት ሥራ መመለሳቸው እንደማይቀር ቡድን መሪው ገልጸዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተሮች

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You