ፕሮጀክቱ በከተማዋ የምግብ ብክነት በመቀነስ ረገድ አስተዋፅኦ ያደርጋል

አዲስ አበባ፡- ባለድርሻ አካላትን በቅንጅት ያሰባሰበውና ኢኮ ፉድ ሲስተም የተሰኘው ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ከተማ የምግብ ሥርዓት ውስጥ ያለውን የተመጣጠነ የምግብ እጥረት በዘላቂነት ለመቅረፍና የምግብ ብክነትን በመቀነስ ረገድ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የምግብ ሳይንስ ተመራማሪና ዲቪዥን ኃላፊ እንዳለ አማረ(ዶ/ር) ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የፕሮግራሙ ዓላማ በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የምግብ ሥርዓት ምን እንደሚመስል መፈተሽና የምርምር ሃሳቦችን በማመንጨት በእዚህ መንገድ የሚሠራበትን አቅጣጫ ማመላከት ነው።

ከእዚህ በፊት በሥርዓተ ምግብ በኩል ያለውን ችግር መቅረፍ የሚያስችሉ እንደሀገር የተቀረፁ መፍትሔዎችና አቅጣጫዎች መቀመጣቸውንና ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያዘጋጀው የጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት መመሪያ መሆኑን ጠቁመዋል። ይህ ፕሮጀክትም የኢትዮጵያን የምግብ ሥርዓት ለማሸጋገር ምን እንደሚያስፈልግ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ መሆኑን ዶክተር አማረ ጠቅሰዋል።

ፕሮጀክቱ ከአይርላንዱ ጋልዌይ ዩኒቨርሲቲና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን ተግባራዊ እንደሚሆን የገለጹት ዶክተር እንዳለ፤ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የእዚህ ሥራ አካል ሆኖ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን እንደሚያከናውን ገልጸዋል።

በእዚሁ ሥራ ለኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎች የትምህርት እድል የሚያገኙበት ሁኔታ እንደሚፈጠርና ለፕሮግራሙ የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ የሚመነጨው መረጃ በትክክል በሥርዓት ምግብ በኩል ያለውን ችግር መቅረፍ የሚያስችል እንዲሆን የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግም አመልክተዋል።

አዲስ አበባ ከተማ ከሌሎች አካባቢዎች በሚመጣ የምግብ ግብአት ላይ ጥገኛ መሆኗን የተናገሩት ዶክተር እንዳለ፤ እንደ ከተማ በበቂ መጠን ምግብ አምርቶ የመጠቀም እድሉ አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል። ከእዚህ አንፃር ከተማዋ የግብርና ምርቶችን ከአጎራባች ከተሞችና ከሩቅ የሀገሪቱ ቦታዎች ለማምጣት እንደምትገደድ ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ ይህን ሂደት የማሳለጥ ሃሳብ እንደሚያመነጭና ምንአልባትም በማጓጓዝ ሂደት ውስጥ የሚታየውን ከፍተኛ የሆነ የምግብ ብክነት በመቀነስ ረገድ ሥራ ላይ ሊውል የሚችል የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፈጠራ ሃሳብ እንዲመነጭ ከማድረግ አንፃር ፕሮጀክቱ እንደሚደግፍም አስታውቀዋል።

የግብርና ምርት ብክነት ላይ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ሰው እንዴት ነው የምግብ ብክነትን የሚከላከለው የሚለውን ሃሳብም ፕሮጀክቱ እንደሚያነሳ ዶክተር እንዳለ ጠቅሰዋል። ኅብረተሰቡ ካለው የግንዛቤ እጥረት የተነሳ የምግብ ብክነት ላይ ከፍተኛ ችግር እንደሚታይና ከእዚህ አንፃር ፕሮጀክቱ ይህንንም ሃሳብ በውስጡ በማካተት ኢኖቬሽንን ማቀንቀን መሆኑንም ጠቁመዋል። ምን አይነት የፈጠራ ሃሳቦችን በእዚህ ሥራ ላይ እናምጣ የሚለውን ነገር ፕሮጀክቱ እንደሚፈትሽም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም ከሥርዓተ ምግብ ጋር ተያይዞ ለሚሠሩ ሥራዎች የእዚህ ፕሮጀክት አካል ሆኖ መረጃዎችን በማመንጨት ቴክኒካዊ ድጋፍ እያደረገ እንደሚቀጥል ዶክተር እንዳለ አስረድተዋል። የሥርዓተ ምግብ ሲታሰብ አንዱ ችግር የአቅም ግንባታ ክፍተት እንደመሆኑ፤ በሰው ኃይል ግንባታውም ላይ ፕሮጀክቱ የራሱን ሚና እንደሚወጣ ገልጸዋል።

“ኢኮ ፉድ ሲስተም” በአውሮፓ ኅብረትና በዓለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ የተደገፈ የምርምር ተነሳሽነት ሲሆን እ.ኤ.አ ከ2025 እስከ 2026 እንደሚቆይ ዶክተር እንዳለ ተናግረዋል።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You