
ሥፍራው እጅግ ሳቢና ለዓይን ማራኪ ነው፤ ከ12 ሄክታር በላይ በሆነ እና በተንጣለለ መሬት ላይ ነው ያረፈው። ከ80 በመቶ በላይ ገጽታው በአረንጓዴ ተሸፍኗል። ቀሪው የተለያየ ቀለም ባላቸው ውብ እና ማራኪ በሆኑ አበቦች ተንቆጥቁጧል። ቦታው ላይ በሚገኘው ለምለም ሳር የለበሰ ዳገት ላይ ሆኖ ቁልቁል አዲስ አበባን መቃኘት ሀሴትን ያጭራል።
የለውጡ ፍሬ የሆነው የአንድነት ፓርክ ገጽታ ልብን በሀሴት ያጥለቀልቃል፤ መንፈስንም ያድሳል።በውስጡ የተለያዩ ሀገር በቀል እጽዋቶች፣ እንስሳቶች፣ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘውን ባለ ጥቁር ጎፈር አንበሳ ጨምሮ የዱር እንስሳቶች፣ ኢትዮጵያ በውሃ ሀብቷ የምትታወቅባቸው ፏፏቴዎች፣ ሰው ሠራሽ ዋሻዎች፣ ቅርሶች ፣ ታሪካዊ ሰነዶች፣ ኢትዮጵያን ያስተዳድሩ የነበሩ ነገሥታት ምስል እና መገልገያዎች አካቶ ይዟል። እንዲሁም የሕፃናትና የአዋቂ መዝናኛዎች፣ የንግድ ተቋማትን እና በጉብኝት የዛለ ሰውነት አረፍ ብሎ ዘና እያሉ ሻይ ቡና የሚሉባቸው የአንድ ማእከል አገልግሎት አለው። ተቋማቱ ሙሉ የምግብ እና መጠጥ አገልግሎትም ያቀርባሉ። የስጦታ እቃዎች እና የተለያዩ ነገሮችም ይሸጣሉ።
አንድነት ፓርክ ከሌሎች ፓርኮች የሚለይበት ብዙ ነገሮች አሉ። ሥፍራው በራሱ ታሪካዊ መሆኑ አንዱ መለያው እንደሆነ በሥፍራው ሲጎበኙ ያገኘናቸው ወይዘሮ ማርታ ሰይፉ ይገልጻሉ።
የእሳቸውና የባለቤታቸው ሥራ ፀባይ በአብዛኛው ውጭ ሀገር የሚያመላልስ በመሆኑ ልጆቻቸውን በክልሎች ወደሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎች ወስዶ ማስጎብኘት የሚያስችል ጊዜ እንደሌላቸው ይናገራሉ። ባላቸው ጥቂት ጊዜ ደጋግመው ፓርኩን በማስጎብኘት እየተዝናኑ ሀገራቸውንና ታሪክ እንዲያውቁ ማድረጋቸውን ነው የነገሩን።
በመዲናችን አሁን ላይ ፓርኩና በየአካባቢው እየተሠሩ ያሉ ለዓይን ሳቢና ማራኪ የልማት ሥራዎች መዲናችን ለውጥ እንዲኖራት ሀገራችንንም እንድንወድ አድርጎናል ይላሉ።
በሻይ ውስጥ የሚጨመር ናና ፣አዝመሪኖ፣ዳማከሴ አንድነት ፓርክ ብቻ ሳይሆን ልጆቻቸው የሚያጠኑበት አብርሆትም ቤተ መጻሕፍት ማየታቸውን የጠቀሱት ወይዘሮዋ፤ በተለይ አዝመሪኖ እና ናና ከምግብ ጋር በተያያዘ አገልግሎት በተጨማሪ ለዓይን ሳቢና ማራኪ በሆነ ሁኔታ በአበባ መልኩ ተተክለው በማየታቸው ተሞክሮ ቀስመው ቤታቸው መተግበራቸውንም ይገልጻሉ።
በውጭው ዓለም እንዲህ ተፈጥሯዊ ነገር ባይኖራቸውም ሀገራቸውን በብዙ አርቲፊሻል ተፈጥሮ በማስመሰል እንደሚያስውቡም አመልክተዋል።
ወጣት ሚኪያስ ንጉሱ አንድነትን፣ ወዳጅነትን፣ እንጦጦንና ሌሎች ብዙ ፓርኮችን የማየት እድል እንዳጋጠመው ይናገራል። በተለይ አንድነት ፓርክ ውስጥ ያሉት እጽዋቶች፣ እንስሳቶች፣ሙዚየሞች በአጠቃላይ የሚጎበኙ ነገሮች እጅግ ማራኪ ብዙ ኢትዮጵያውያኖች ሊማሩበት የሚችሉት ትልቅ የሀገር ሀብት የያዘ ሙዚየም ስለመሆኑ ያነሳል።
በሁለተኛው ጉብኝቱ ለመድኃኒት ቅመማ እና ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ የቅመማ ቅመምና ሌሎች እጽዋቶች ተካተው ማግኘቱን የሚጠቅሰው ሚኪያስ፤ የአሁኑ ትውልድ ሄዶ ሊማርበት እንደሚገባ ይጠቅሳል። የነገሥታቱን ታሪክና መገልገያ ማየቱ ወደ ኋላ መለስ ብሎ ታሪክን መቃኘት ፣ ለአሁንም ተስፋ የሚያጭር፣ ፍቅር የሚጨምርና አንድነት የሚያጠናክር ነው ይላል።
በዳግማዊ ምኒልክ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሦስተኛ ዓመት የፋርማሲ ተማሪ ትንሳኤ በላይ ወዳጅነት ፓርክን ጎብኝቷል። ጎብኚዎችን ሊያዝናኑ የሚችሉ ብዙ ነገሮች አሉበት፤ ጎብኚውን የሚያዝናና ምቹ ተደርጎ የተሠራ ፀአዳ፣ አረንጓዴ ፣ ሰፊ በቂ የሆኑ መዝናኛ ፣ አርቲፍሻል ሀይቅም አለው ይላል ።እሱን የመሰሉ ወጣቶችም ቢጎበኙት ታሪክም፣ መዝናናትን በአንድ ላይ ያገኙበታልና ጎብኙት ሲል ይመክራል።
መምህር አረጋህን ቦያሳ የቱሪስት መዳረሻ ልማቶች ከተማዋን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየለወጧት መምጣታቸውን ይናገራል።ሥፍራዎቹን ተማሪዎች በቡድንም በግልም አብዝተው በመጎብኘት እውቀት የሚጎበኙባቸው፣ ታሪክ የሚቀስሙባቸው በመሆናቸው ሀገርን ከመውደድ፣ ዓላማን ለስኬት ከማብቃት አኳያ ለትውልድ ትልቅ ጠቀሜታ አላቸው ብሎ ያምናል። ኅብረተሰቡ አንድነት ገብቶ በወጣ ቁጥር ኢትዮጵያን በቀላሉ ይረዳልም ይላል።
ከዘመናዊ ኢትዮጵያ ታሪክ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በሙዚየም ደረጃ ተደራጅቶ ስለመገኘታቸው የምታነሳው የአራተኛ ዓመት የኮምፒውተር ሳይንስ ተማሪ ሶሎሜ ጉልላት፤ በአካል ቀርቶ በስም የማታውቃቸውን እንስሳቶች፣ አእዋፋት ማየቷን ኢትዮጵያ ከውጭው ዓለም ጋር ገና በ16ኛው ክፍለ ዘመን የዲፕሎማሲ ግንኙነት መጀመሯን ማወቋን ትናገራለች። የአንድነት ፓርክ ቆንጆ ሊታይ ብዙ ሊጎበኝ የሚችል ነገር ያለው የመዲናዋ ሞገስ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
የአንድነት ፓርኮች ኮርፖሬሽን ኮሙኒኬሽን ባለሙያ አቶ ጌታቸው በየነ፤ ፓርኩን በክረምት ወራት፣ በበዓላትና ቅዳሜና እሁድ ጎብኚው በቀን እስከ 3 ሺህ እንደሚደርስ ያነሳሉ። በክረምት ትምህርት ቤት ሲዘጋ ሥራ የሚዘጋባቸው በዓላት ሲኖሩ ወላጅ ልጆቹን፣ ቤተሰቡን በሙሉ በመያዝ ከአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ይመጣል።የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተለያዩ ተቋማት፣ በቡድን እየመጡ ይዝናናሉ።ሙሽሮች በአምስቱም ፓርኮች የመስክ ፎቶ ይነሳሉ ይላሉ።
ፕሮግራም የሚያደርጉም አሉ። ከበዓላት ውጪ አነስተኛ ነው ከተባለ በአማካኝ በቀን አንድ ሺህ ሰው የሚጎበኘው እንደሆነም ይናገራሉ። ባለፉት ዘጠኝ ወራቶች አንድ ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ጎብኚዎችን ማስተናገዱንም ያወሳሉ። ባለፈው ዓመት በዘጠኝ ወር አንድ ነጥብ አንድ ነበር ጎብኚው ፤ዘንድሮ ከመቶ ሺህ በላይ ጭማሪ አሳይቷልም ይላሉ።
ከእዚህ ውስጥ 28 ሺህው የተለያየ ዜግነት ያላቸው የውጭ ዜጎች እንደሆኑም ያስረዳሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ጋር ለሀገራዊ ጉዳይ የሚመጡ የውጭ ሀገር መሪዎች አንድነት ፓርክን ሳይጎበኙ እንደማይመለሱም ይገልጻሉ።ፓርኩ በ2012 ዓ.ም መስከረም 29 በርካታ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት መሪዎች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ ተመርቆ ለጉብኝት ክፍት መሆኑንም ያስታውሳሉ።
አንድነት ፓርክ አድማሱን እያሰፋ ለወዳጅነት ቁጥር አንድና ሁለት ፣ለአንድነት መኪና ማቆሚያ፣ ለሳይንስ ሙዚየምና ለበርካታ ፕሮጀክቶች መሠራት ምክንያት ስለመሆኑም ይጠቅሳሉ።
በተለይ አንድነት ፓርክ አንድ ሺህ 30 መኪኖች የሚያቆመው ፓርኪንጉን ጨምሮ ሁሉን አሟልቶ መያዙ ተመራጭ እንዳደረገውም ያወሳሉ።አዲስ አበባ አሁን ላይ ሁሉም ሥፍራ የጉብኝት ስፍራ ሆኗል። የኮሪደር ልማቱ በየቦታው ተስፋፍቷል። ይሄም ሆኖ ወሳኙ የሚያገኙት አገልግሎት ነውና ጎብኚዎች ወደ አንድነት ፓርኮች ይመጣሉ ይላሉ።
በአዲስ አበባ ባህል ቱሪዝምና ኪነ ጥበብ ቢሮ የቱሪዝም መዳረሻ ልማትና የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ማስፋፋት ዳይሬክተር ሳምሶን ዓይናቸው፤ በገበታ ለሸገር ከተከናወኑት የቱሪዝም ልማት ሥራዎች አንዱ የአንድነት ፓርክ ነው፤ አንድነት ሲገነባም እንደሞዴል ሆኖ ነው። በገበታ ለሸገርም ሆነ ለሀገር የተገነቡት የቱሪዝምና መደረሻ ቦታዎች በራሳቸው መዳረሻ ለመሆን ብቻ ሳይሆን ለሌሎች በቀጣይ ለሚሠሩ የቱሪስት መዳረሻ ሥራዎችም ሞዴል እንዲሆኑ ታስቦ እንደሆነ ይገልጻሉ።
አንድነት ፓርክ ብቻ ሳይሆን፤ እንደ ሀገር የተሞክሮ መቅሰሚያ ማእከልም የሆነ ከፓርክም በላይ ፋይዳ ያለው ነውም ይላሉ። በውስጡ ታሪካዊ ቅርስ ቤቶች፣ የባሕል ማእከላቶች ይገኛሉ፤ ፓርክ ሲባል እጽዋት ዝርያዎችን እና የዱር እንስሳት ብቻ ሊገኝበት የሚችል የባህል ቅርስ ቤቶች እና ክልሎችን የሚገልጹ የባሕል ማእከላት ግንባታዎች የተከናወኑበት በመሆኑ ከፓርክም በላይ እንደሆነ ነው የገለጹት።
ከእዚህ በኋላ በከተማም ሆነ በክልል ለሚከናወኑ ለሌሎች የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች ግንባታ እንደ ሞዴል ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ለከተማችን ተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። ሰፊ የሥራ እድልም ፈጥሯል ነው ያሉት።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14 ቀን 2017 ዓ.ም