
ታላቁ የፋሲካ በዓል በቅዱስ መጽሀፍ ኦሪት ዘጸዓት ላይ በሰፈረው ታሪክ መነሻነት ይጀምራል። የዘመናቱ ሃይማኖታዊ ዳራዎች እንደሚጠቁሙት ከሶስት ሺህ ዓመታት በፊት የእስራኤል ሕዝቦች በግብጽ ምድር ላይ በባር ነት ተገዝተው ይኖሩ ነበር።
እነዚህ ሕዝቦች በምድረ-ግብጽ ከአራት መቶ ዓመታት በላይ ዕድሜ አስቆጥረዋል። ይህ እውነት ግን በወቅቱ ለፈርኦኑ አልተመቸም። እያደር የቁጥራቸው መብዛትና የዘራቸው መስፋት የበዛ ፍራቻ ያሳድርበት ያዘ። ይህ አይነቱ ስጋትም በከባድ ስቃይና የሥራ ብዛት እንዲያሰቃያቸው ምክንያት ሆነ።
የፈርኦኑ ጭካኔ በዚህ ብቻ አልቆመም። ከአስራኤላውያኑ ወገን ወንዶች ልጆች በሚወለዱ ጊዜ ‹‹በአስቸኳይ እንዲገደሉ›› ሲል ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፈ። የንጉሡ ቃል ሳይውል ሳያድር እንደልቡ ሆነለት። ጨቅላዎቹ ከእናታቸው ማህፀን ወጥተው ለዕቅፍ ሳይበቁ በሞት መቀጣትና መቀላት ጀመሩ። ዕልፍ የእስራኤል ሕጻናትም የጨካኙ ንጉሥ ሰይፍ አረፈባቸው።
ይህኔ እስራኤላውያኑ ወደ አምላካቸው አብዝተው ጮሁ። እግዚአብሔርም ለቅሶ ጨኸታቸውን ሰምቶ ሙሴን ወደእነሱ ዘንድ ላከላቸው። የግብጽ ፈርኦን ይህ ባወቀ ጊዜ ‹‹ሕዝቡን አለቅም፣ እግዚአብሔርንም አላውቅም›› ሲል ተገዳደረ።
እግዚአብሔርም መኖሩን ለማሳየት በግብጽ ምድር ላይ ዘጠኝ መቅሰፍቶችን አወረደ። እስራኤላውያን የሚኖሩበትን ከተማ ግን በተአምራቱ ታድጎት ቆየ። የመጨረሻው መቅሰፍት ሊወርድ ባለ ጊዜ ግን ቅጣቱ በአስራኤላውያን መንደር ጭምር ሊያልፍ ግድ ነበር።
እግዚአብሔር ግን ይህ እንዲሆን አልፈቀደም። ሕዝቡን በእኩል ላለመቅጣት ሲል በሙሴ በኩል መልዕክት ላከ። ሙሴም እንደተቀበለው ቃል ትዕዛዙን አስፈጸመ። በእያንዳንዳቸው ቤት ከሚያርዱት በግ ደሙን በቤታቸው መቃኖችና ጉበኖች ቀብተው ምልክት እንዲያኖሩና ከቤታቸው እንዳይወጡ ሲል ትዕዛዝ ሰጠ። የፋሲካ ታሪክ መነሻም ከዚህ እው ነት ይጀምራል።
በጊዜው ሁሉም እንደ አምላክ ቃል ተፈጸመ። መላዕከ ሞት በእኩለለሊት በምድሪቱ ላይ ባለፈ ጊዜ የበጉ ደም የተቀባባቸውን ቤቶች አልፏቸው ሄደ። ከሰው እስከ እንስሳ ባሉባቸው ምልክት አልባ ነፍሶች ላይ ግን ጭካኔው በረታ።
እንዲህ በሆነ ጊዜ በግብጽ ምድር ለቅሶና ጩኸት አየለ። በእስራኤል ምድር ደግሞ በታረደው በግ ደስታና እፎይታ ሆኖ ሕይወት በፍስሃ ቀጠለ። ከዚህ እውነት በኋላ አስራኤላውያን አምላካቸውን በእጅጉ አመስግነው አከበሩ። በበጉ ደም ፍሰትም ሁሉ መታለፍ ሆኖላቸው ከባርነት እስር ነጻ ወጡ።
በሕዝበ ክርስቲያን ዘንድ በታላቅ ድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል ዕለተ ፋሲካ አንዱና ዋነኛው ነው። ይህ በዓል ከአብይ ጾም መጠናቀቅ በኋላ የሚመጣ እንደመሆኑ ክርስቶስንና ትንሳኤውን በሚያውቁ ዘንድ ሁሉ ልዩ ትኩረትና አክብሮት ይቸረዋል።
እንደ ሃይማኖታዊ ድርሳናት ትርጓሜ ፋሲካ በዕብራይስጥኛ ‹‹ፔሳ›› የሚል ስያሜን ይይዛል። ይህ ቃልም ወደ አማርኛው ሲመለስ ‹‹ፋሲካ›› በሚል ቃል ይተረጎማል። ‹‹ፋሲካ ማለት ‹‹ማለፍ ወይም መሻገር›› እንደማለት ነው። እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት መውጣት በኋላ በድል ያለፉበትን ፋሲካ ታላቅ በዓል አድርገው ያከብሩታል።
ይህ በዓል ለነዚህ ሕዝቦች ከትውልድ እንዲሻገርና ለልጅ ልጅ እንዲያልፍ ሆኖ ከእግዚአብሔር የተሰጣቸው መታሰቢያ ነው። በዚህም የቂጣና የፋሲካ በዓላቸውን እያከበሩ ቀጥለዋል።
‹‹ብሉይ ኪዳን የአዲስ ኪዳን ጥላ ነው›› ተብሎ እንደተጻፈ ሁሉ የሚታረደውን የፋሲካ በግ የተካው የአዲስ ኪዳኑ እየሱስ ክርስቶስ ዘመኑ በደረሰ ጊዜ ከድንግል ማርያም ተወልዶ በክብርና ሞገስ አደገ። የአብ ቃል ይፈጸም ዘንድም ስለ ዓለም ሐጢያት ተላልፎ ተሰጠ።
ስለ ሰው ልጆች ሃጢያትና በደል ሲልም ታሰረ፣ ተገረፈ፣ በመስቀል ተከንችሮም የሞት ፅዋን ተጎነጨ። በቅዱስ መጽሀፍ አንደኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 5 ላይ እንደተጠቀሰው ‹‹ፋሲካችን የሆነው ክርስቶስ ታርዷል›› የሚል ቃል ሰፍሯል። የቅዱስ ጳውሎስ ቃልም እንዲሁ ‹‹በፋሲካችን ከርስቶስ ታረደ›› ሲል ይመሰክራል።
በአይሁዳውያን ዘመን ለፋሲካ በሰዎች እጅ ካሉት በጎች አንደኛው ተመርጦ ይታረድ ነበር። በሀዲስ ኪዳን ፋሲካ ደግሞ ይህ ተሽሮ ከሰማይ የወረደው ክርስቶስ ስለ ሰዎች ኃጢያትና በደል ሲል እንዲታረድ ሆኗል።
የፋሲካ በዓል የእየሱስ ክርስቶስን ከሞት መነሳት የሚያበስር ታላቅ የምስራች ነው። ይህ ቀንም ክርስቶስ ሞትን ድል ስለማድረጉ የሚያውጅ ትንሳኤ ሆኖ ይከበራል። እየሱስ ክርስቶስ በራሱ ሃይልና ሥልጣን መቃብር ፈንቅሎ ከሙታን መሀል ተነስቷል። ዓለም ሊሞትበት የነበረውን ሞትም ራሱ ሞቶ ድል ነስቷል። በዚህም የሰው ልጅ አዳምን ከዘላለም የሃጢያት ቅጣት አድኖታል።
እንደ ቃሉ ትርጓሜ ‹‹ትንሳኤ›› ማለት እንደ አዲስ መነሳት ማለት ነው። ፋሲካ ደግሞ ስለበዓሉ መከበር በፍስሃና ደስታ የሚገለጽ ዕለት ሆኖ ይሰየማል። በክርስትና አስተምህሮ ትንሳኤ የዕምነትና ተስፋ መሠረት ነው። በዚህም ዕለተ ፋሲካ በተለየ ዝግጅት እንዲታሰብ ሆኖ ይከበራል።
እነሆ ! ዛሬ ለሕዝበ- ክርስቲያኑ ዕለተ ፋሲካ ነው። ይህ ቀን ከሁለት ወራት ፆም ፀሎት በኋላ እንደመከበሩ በታላቅ ጉጉት የሚጠበቅና የሚናፈቅ ይሆናል። የፋሲካ በዓል አከባበር እንደ የሀገራቱ ዕምነትና ልማድ መለያየቱ ግልፅ ነው። በእኛ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ደግሞ በዓሉ በአብሮነትና በመተሳሰብ የሚገለፅ ሆኖ ዘመናትን ተሻግሯል።
ዘንድሮም ታላቁን የፋሲካ በዓል ተቀብለን ስናከብር የክርስቶስ ትህትና የተገለጸባቸውን ተግባራት በማሰብ ሊሆን ይገባል። እየሱስ ክርስቶስ ዝቅ ብሎ የደቀመዛሙርቱን እግር እንዲያጥብ ሲሆን በታናሽነቱ ታምኖበት አልነበረም ። መታዘዝን፣ ዝቅ ማለትን ለማሳየት እንጂ ። ፋሲካም በታረደው በግ እየሱስ መስዋዕትነት የሚገለጽ ተምሳሌት ነው። ይህ እውነትም ለእኛ ለሰው ልጆች በደልን ሽሮ የሐጢያት ሞትን አስቀርቶልናል። ዛሬ በዓሉን ከማክበር ባሻገር ከእኛ ሊጠበቅ የሚሻውም በእርቅና መዋደድ መልክ የሚገለጽ የአብሮነት ማሳያ ነው።
እየሱስ ክርስቶስ ፍቅርና በጎነትን ለማሳየት ስጋውን ቆርሶ ሕይወቱን አሳልፎ ሰጥቷል። ሕዝበ ክርስቲያኑም ከዚህ እውነተኛ ፍቅር በመነሳት ያለውን በመስጠትና በማካፈል ተምሳሌትነቱ ሊገልፅ ይገባል። ይህ የክቡር ነፍስና ሥጋ ስጦታ ለሰው ልጆች ሕይወት በጎነትን ፣ መስዋዕትነትን የሚመስክር ሆኖ ይገለጻል።
ይህ አይነቱ የክርስቶስ ሀቅም በዓለም ላይ ላሉ ክርስቲያኖች ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር እንደሌለ የሚጠቁም መርህ ሆኖ ዘልቋል። ክርስቶስ ዝቅ ብሎ መታዘዝን ሲያሳይ፣ በእሱ ተምሳሌት አንዱ ለሌላው በፍቅር እንዲታዘዝ ለማሳየት ነው። ይህ እውነታም በዕለተ ፋሲካ ለክርስቲያኖች ተግባር ሆኖ ይገለጽ ዘንድ ግድ ይላል።
እየሱስ ክርስቶስ በአብ ፈቃድና ትዕዛዝ ወደ ምድር ሲመጣ በእርቅና ሰላም በፍቅርና አክብሮት የተቀባ እውነትን ለሰው ልጆች ልቦና ለማድረስ ነው። የክርስትና አስተምህሮቱ እንደሚያሳየውም በይቅር ባይነት፣ በትህትና፣ በመታዘዝ ፣ በሰላምና አብሮነት ዕምነትን ማጽናት የክርስቶስ መገለጫ ሆኖ ይተረጎማል።
እነሆ! ዛሬ እየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ነስቶ ህያው የሆነበት የትንሳኤ ቀን ነው። እንደ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ሁሉም በየቤቱ በዓሉን ተቀብሎ በደስታ ያከብረዋል። ከመብላትና መጠጣት ባሻገር ግን የክርስቶስ ምሳሌ የሆኑ ማሳያዎች በተግባር ሊታዩ፣ ሊተረጉሙ ይገባል።
በዕለተ ፋሲካ ያለው ለሌለው ወገኑ ቆርሶ ሲያካፍል በመስቀል ላይ ስጋውን የቆረሰው ክርስቶስ ይታሰባል። በእርቅና ሰላም የተዋዛ፣ በአንድነት የተገመደ አብሮነት ሲፈጠር ፍጹም ፍቅር የሆነው እየሱስ ክርስቶስ ስለሌሎች ፍቅር ሕይወቱን አሳልፎ እንደሰጠ ይታወሳል። በመታዘዝና በትህትና ሠብዓዊነት ሲገለጽም ዕለተ – ፋሲካ የሀገር ትንሳኤ ሆኖ በክብር ይደምቃል። ለመላው የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ሁሉ መልካም በዓል ይሁን ።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12 ቀን 2017 ዓ.ም