
ዜና ትንታኔ
የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ይፋ ያደረገው ዓለም አቀፋዊ የጾታዊ ጥቃት ቅኝት ሪፖርት እንደሚያመላክተው በዓለማችን ከሦስት ሴቶች መካከል በአንዷ ላይ ጾታዊ ጥቃት ይደርሳል፡፡ ቁጥሩ እለት በዕለት እየጨመረ ስለመሆኑም መረጃው ያመላክታል።
እእአ በ2022 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው በዚያው ዓመት 89 ሺህ ሴቶች እና ልጃገረዶች የግድያ ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡ ከሁሉም የሚከፋው ደግሞ ጾታዊ ጥቃት ከደረሰባቸው 10 ሴቶች መካከል ወደ ፍትህ የምትሄደው አንዷ ብቻ መሆኗ ነው፡፡
ጥቃቱ በሀገራችንም ተመሳሳይ ገጽታን የተላበሰ ሲሆን፤ ችግሩን ለመከላከል የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት እና በተናጠል ሰፊ ጥረት ቢያደርጉም ጥቃቶቹን መቀነስ አልተቻለም። እውነታው ዛሬም የበርካታ ዜጎች፣ የፖለቲካ አመራሮች እና የፍትህ አካላት ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱም አሳሳቢ ሆኗል፡፡
ለችግሩ መባባስ እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱት መካከል ከሕግ ጋር የተያያዘ ክፍተት እና አስተማሪ የሆነ ቅጣት መጣል አለመቻሉ፤ እንዲሁም፣ ሕጎችን በፍጥነት በማሻሻልና አዳዲስ ሕጎችን በማውጣት ፈጥኖ ወደ ተግባር የመግባት ቁርጠኝነት ማነስ መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
ሰሞኑን የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር በቢሾፍቱ ከተማ ባዘጋጀው መድረክ ለውይይት የቀረበ ጥናትም እንዳመለከተው፣ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን በተመለከተ ያሉ የሕግ ክፍተቶችና ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እየተፈፀሙ ይገኛሉ፡፡
ጥናቱ ችግሩን ለመቀነስ ሁሉን አቀፍ ፆታዊ ጥቃትና ትንኮሳን የያዘ የተጠቃለለ ሕግ እንደሚያስፈልግም ዳስሷል፡፡ ጾታዊ ጥቃት እየተባባሰ የመጣበት ምክንያት ምንድነው፤ በተጎጂና በአጠቃላይ ማህበረሰቡ ላይ የሚያደርሰው ሥነልቦናዊና ማህበራዊ ጫናስ አለ ወይ? በሚለው እና በመፍትሄው ዙርያ የሕግ ምሁራን እና የሥነልቦና ባለሙያዎችን አነጋግረናል፡፡
የሕግ ምሁሩ ቁምላቸው ዳኘ እንደሚሉት ጾታዊ ጥቃት እየተባባሰ የመጣበት ምክንያት ከጾታዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ የተቀመጡ ሕጎች ክፍተት ያለባቸው ስለሆኑ ነው፡፡ በማሳያነት በትዳር ውስጥ ያሉ ሴቶች በትዳር አጋሮቻቸው፤ እንዲሁም በወንድ ጓደኞቻቸው የሚደርስባቸው ጥቃት በኢትዮጵያ በወንጀለኛ መቅጫው ሕግ በወንጀልነት ተመዝግቦ አይገኝም፡፡
እስከ ሞት እና እስከ የሰውነት ገጽታ ማበላሸት የሚደርሰው አሲድ መድፋት፤ ዓይን ማጥፋት የተለያዩ አካላትን ማጉደልና መግደል በተበታተነ መልኩ ቢኖርም በተለየ መልኩና ቅጣቱን በሚያከብድና ለመከላከል በሚያስችል መልኩ የተቀመጠ እንዳልሆነም ያብራራሉ።
ከዚሁ በትዳር ውስጥ ካለችና የወንድ ጓደኛ ካላት ሴት ያለ ፈቃዷ መደፈር ጋር ተያይዞ ያለው በውጭው ዓለም በከባድ የመድፈር ወንጀል የሚያስቀጣበት ሁኔታ ቢኖርም፤ በኢትዮጵያ ግን ሕብረተሰቡ በተዛባ አመለካከት እንደሚረዳው ይጠቁማሉ፡፡ ግማሹ ከድንግልናን መውሰድ ጋር አያይዞ ያየዋል፤ ግማሹ ደግሞ ትዳር ውስጥ ከሆነች አልፈልግም ማለት አትችልም የሚል ትርጉም በመስጠት እንደሚያቀለው ያነሳሉ፡፡
አስገድዶ መድፈርን በተመለከተ ወንጀሉ ልክ እንደሙስና አስረጂ ሰው በሌለበት የሚፈፀም ከመሆኑ አንፃር ሕጉ ማስረጃ መጠየቁ በራሱ ክፍተት ነውም ይላሉ፡፡ በሀሰት ክስ ትመሠርታለች ተብሎ ቢታሰብ እንኳን ሌሎች ሀገሮች ማስረጃን በተመለከተ ክሱን ወደ ተከሳሽ የማዞር ሥርዓት አላቸው፡፡ በእኛ ሀገር እሱን ማድረግ አለብን፤ ወይስ የለብንም የሚለው መታየት አለበት። ከጥቃት ፈፃሚዎች አንፃር ሳይሆን መልስተኛም ቢሆን ተጎጂዋ በሌሎች ወንጀሎች ላይ በሚቀርበው ማስረጃ የሚያሳይ ማስረጃ ካቀረበች ተከሳሹ ላይ ከበድ ያለ ቅጣት የሚጣልበትን ማየት ስለማስፈለጉም ያብራራሉ፡፡
የማስረጃ ሕጉ የማስረዳት ደረጃው ምን መሆን አለበት የሚለው በደንብ መፈተሽ እንዳለበትም ይመክራሉ፡፡ በመደበኛ የወንጀለኛ ሕጉ ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያወጣው የጥቃት አወሳሰን መመርያ መኖሩን የጠቆሙት የሕግ ምሁሩ መመሪያው የወጣው መዘበራረቅን ለማስቀረት እንደሆነም ይናገራሉ፡፡
ሆኖም ሕጉ ላይ ይሄን የተላለፈ ከፍተኛ የቅጣት መዘበራረቅ ትልቅ ክፍተት እንዳለም ይጠቁማሉ። ለአብነት እንደሚያነሱትም የፈፀመው ወንጀል በጣም አስደንጋጭ ሆኖ በገደብ የሚለቀቅ፤ እንዲሁም ከወንጀሉ ጋር ያልተመጣጠነ ቀላል ቅጣት የሚጣልበት የፍትህ ሂደት ስለመኖሩም ይገልፃሉ፡፡ ሴቶች እና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን በተመለከተ ያሉ የሕግ ክፍተቶች ላይ ጥናት ያጠናችው የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር አባል ቤተልሔም ደጉ በበኩሏ ለችግሩ መስፋፋት ምክንያት የሆኑት የሕግ ክፍተቶች ስለመሆናቸው በምሳሌ አስደግፋ ታስረዳለች፡፡
“የሕግ ማሕቀፉ ላይ የትርጉም ውሱንነት እና በማሕቀፉ ያልተካተቱ ጉዳዮች አሉ” የምትለው ቤተልሔም፣ ካልተካተቱት ውስጥ ወሲባዊ ትንኮሳ መገኘቱን ትጠቅሳለች፡፡ አስገድዶ መድፈር በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 620 ላይ በግልጽ ቢቀምጥም አስገድዶ መድፈር ምን ማለት እንደሆነ፤ ምን ዓይነት ድርጊቶችን አካትቶ እንደሚይዝ፤ ከተለመደው ውጭ በፊንጢጣና በሌሎች ቢፈጸም አስገድዶ መድፈር ነው ወይ? የሚለውን በግልጽ አለማስቀመጡን ታስረዳለች፡፡
ጾታዊ ጥቃት ከፍተኛ የሠብዓዊ መብት ጥሰት ነው የሚሉት ደግሞ በዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህርና በዲላ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የማህበራዊ ሳይንስ አማካሪ አማረ ዓለምወርቅ ናቸው፡፡ ጥቃት አንድ ሴት ላይ በግፍ፣ በማታለል፣ በማስፈራራት ወይም በሌላ መንገድ የሚፈፀም የጾታ ተግባር እንደሆነ የጠቆሙት ባለሙያው በተጎጂዎቹ ላይ እንቅልፍ የማጣት፤ የመረበሽ፤ የመጨነቅ፤ ራስን የማጥፋት እንዲሁም ከፍተኛ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት ስለማስከተሉም ያብራራሉ፡፡
በተጨማሪም ማህበራዊ ሕይወታቸው ላይ ከቤተሰብ እና ከጓደኛ ከሚያውቁት ሰው የመራቅ፤ ተገልሎ መቀመጥ መፈለግ፤ ማህበረሰቡን የመጠራጠር ስሜት እንዲሰማቸው እንደሚያደርግም ያስረዳሉ፡፡ የሕግ ምሁሩ ቁምላቸው በበኩላቸው በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን እና በሴቶችና ሕፃናት ላይ እየተፈፀመ የሚገኘውን ጾታዊ ጥቃት ለመከላከልና ለመቀነስ እንደመፍትሄ የሚያስቀምጡት ጾታዊ ጥቃትን የሚመለከት የቤተሰብ ችሎት ማቋቋምን ነው፡፡
ጾታዊ ጥቃትን ብቻ የሚመለከት ችሎት ለብቻው መቋቋም አለበት፡፡ ይሄ ካልተቋቋመ ችግሩ አይፈታም የሚል እምነት አላቸው፡፡ ከሌላው ወንጀል ተለይቶ ለብቻው ችሎት መቋቋሙ በተሻለ መልኩ ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል ያስችላል፤ የቅጣት መዘበራረቅንም ያስቀራል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
ሁሉን አቀፍ ጾታዊ ጥቃትና ትንኮሳን የያዘ የተጠቃለለ ሕግ የበለጠ ችግሩን እንደሚቀርፍም ያስረዳሉ፡፡ “ሁሉን አቀፍ ጾታዊ ጥቃትና ትንኮሳን የያዘ የተጠቃለለ ሕግ ከወንጀል ሕግ አንጻር አይመከርም‘ የሚሉት ምሁሩ ፤ ዜጎች በቀላሉ እንዲያገኝዋቸው የወንጀል ሕግ ድንጋጌዎች በአንድ ሕግ መጻፍ ላይ ተደራጅተው መገኘት እንዳለባቸው ይገልፃሉ፡፡
ሁሉን አቀፍ ጾታዊ ጥቃትና ትንኮሳን የያዘ፣ ከተጠቃለለ ሕግ ይልቅ ከጾታዊ ጥቃት ጋር ተያይዞ ያለውን የወንጀል ሕጉን ክፍተቶች በማስተካከል የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉን ቅጣት ማሻሻል እንደሚሻልም ይመክራሉ፡፡
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም