
ዜና ሐተታ
ከአንድ ሳምንት በፊት ካዛንቺስ ጊቢ ገብርኤል አካባቢ ጓደኛዬን እየጠበኩት ነበር። ካዛንቺስን እንደዚህ አላውቃትም፤ የማውቃት በጠባብ መንገዶቿ፣ በደሳሳ የንግድ ሱቆቿ፣ እግረኞች በመኪና መንገድ እየተላለፉ የአደጋ ተጋላጭ የሚሆኑባት የጫት እንጨት፣ ፕላስቲክ እና ሌሎች ውድቅዳቂ ቆሻሻዎች በስፋት የሚጣልባት ነበረች ። አሁን ግን ሁሉም ታሪክ የሆነ ያህል ነው።
እነዚያ በቆርቆሮ እና በሸራ የተለበዱ ያረጁና የወዳደቁ ቤቶች፤ ጠባብ የእግረኛ እና የመኪና መንገዶች፤ አካባቢው ላይ ለመንቀሳቀስ ጣር የነበሩ የሚኒ ባስ ታክሲዎች እና የወያላዎች ጩኸት ፤ በግፊያና በግርግር ውስጥ የስጋት ምንጭ የነበሩ የኪስ ነጣቂዎች አይታዩም። አሁን የነበሩ ደሳሳ የመኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ እና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት በትልልቅ ሕንፃዎች እየተተኩ ነው።
በከተማዋ እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት የካዛንቺስ ገጽታ እየተለወጠ ነው፤ ሳይሆን ተለውጠዋል፤ ነገ ሊሆን የሚችለው ደግሞ የበለጠ ያጓጓል። ሰፋፊ የተሽከርካሪ፣ የእግረኞች፣ የብስክሌት መንገዶች፣ ለአካል ጉዳተኞች ታስበው የተገነቡ ደረጃቸውን የጠበቁ መንገዶች ለአካባቢው ድምቀት ሆነዋል ።
አረንጓዴ ስፍራዎች፣ አደባባዮች፣ መጸዳጃ ቤቶች፣ ፋውንቴኖች፣ በእግር ለሚንቀሳቀሱ የከተማዋ ነዋሪዎችና ጎብኚዎች የህሊና እረፍት እና መገረምን የሚፈጥሩ ናቸው። አረፍ የሚባልባቸው ስፍራዎችም ፤ በርግጥም እንደሀገር የጀመርነው የለውጥ ጉዞ የብዙ ተጨባጭ ተስፋዎችን ባለቤት እያድረገን ስለመሆኑ ተጨማሪ ምስክር የሚጠይቅ አይደለም።
አብዛኛው ሰው ሰፊ የእግረኛ መንገድ ላይ ያለስጋት፤ በነፃነት የአካባቢውን መለወጥ መለወጡ የወለደውን መገረም ይዞ ይንቀሳቀሳል ፤ የደከመውም እስለከመገረም መንፈሱ ለዚሁ ተብሎ የተሠሩ ማረፊያ ቦታዎች ላይ ዘና ብሎ ተቀምጦ ሁኔታውን በተመስጦ ያስተውላል። በማየው ነገር የተሰማኝን ደስታ የትኛውም ሰው በቀላሉ ፊቴን አይቶ መረዳት የሚችለው ነው።
የአካባቢውን ገፅታ በሚመለከት እንደኔው በብዙ መገረም ሁኔታውን እያስተዋሉ ወዳሉት የከተማዋ ነዋሪ አቶ ዮሴፍ መንግሥቱ ተጠግቼ፤ ስለ አካባቢው ለውጥ ጠየኳቸው፤ ካዛንቺስ አንገት የሚያስደፋ ስፍራ መሆኑ ቀርቶ በኮሪዶር ልማቱ የከተማዋ ውበት እየሆነች መምጣቷ ለሳቸውም ትልቅ መገረም የፈጠረ ነው።
አዲስ አበባን እንደስሟ አዲስ ከማድረግ ባለፈ ፤ በቀጣይ የቱሪስቶች ቀልብ ልትስብ የምትችል ከተማ ስለመሆኗ ፤ ይህም የከተማዋን የኢኮኖሚ አቅም በማሳደግ ረገድ ትልቅ ሚኖ እንደሚኖረው፤ በሌሎች የዓለም ሀገራት የሚታዩ የከተማ ልማቶችን በሀገራቸው መመልከት በመቻላቸውም ተደስተዋል።
የካዛንቺስ የመኪና መንገድ የተጨናነቀና ምቹ ባለመሆኑ ሰውና መኪና ተገፋፍቶ የሚተላለፍበት እንደነበር እያስታወሱ፤ ይህም አሽከርካሪዎች እና እግረኞች ለአደጋ እንዲጋለጡ ያደርግ ነበር። አሁን ግን በአንድ ጊዜ ስድስት መኪናዎች ወደጎን ማሳለፍ የሚችል የመኪና መንገድ መገንባቱ ለመኪኖች እና ለሰዎች እንቅስቃሴ እፎይታ መፍጠሩን በተጨባጭ ታዝበዋል።
በአሁኑ ወቅት አስደሳችና ተስፋ የሚሰጡ ልማቶች እየተከናወኑ ነው። ልማቱ ለኑሮ በማይመቹ የከተማዋ አካባቢዎች ጨምሮ በመላው ሀገሪቱ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ከመገረማቸው ሳይወጡ ፤ የተሻለ ነገ በሚጠብቅ ተስፈኛ ስሜት ተሞልተው አወሩኝ።
ሌላኛዋ እዛው ያገኘኋቸው የከተማዋ ነዋሪ፤ ወይዘሮ አስባረች ብርሃኑ ናቸው፤ ልማቱ አዲስ አበባን በዘመናዊ የከተማ ፕላን በመምራት ከሌሎች ሀገራት ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ እንደሚያደርጋት ያላቸውን ተስፋ አጋርተውኛል፤ ልማቱ የመዝናኛ ቦታዎችና ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶች የሚያካትት መሆኑ መዲናዋን ማራኪና ሳቢ እያደረጋት መሆኑን ታዝበዋል፡፡
አዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ መዲናነቷን ይዛ እንድትቀጥል ምቹና ዘመናዊ መሠረተ ልማቶችን መዘርጋት እንደሚገባ፤ ቀጣዩ ትውልድ ውብ ከተማን መረከብ እንዲችል ፕሮጀክቱ ትልቅ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ማሳሰቢያ አዘል መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ከተማዋ ካለባት የመሠረተ ልማት እጥረትና የሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ ዘመናት ያስቆጠሩ መሠረተ ልማቶችን ለማዘመን፣ ለማደስና የነዋሪዎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት፤ ለዚህም የነዋሪዎች አወንታዊ ተሳትፎ ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመውኛል።
በካሳንቺስ እየተሠራ ያለው የልማት ሥራ አሁን ላለውም ሆነ ለሚመጣው ትውልድ ትልቅ ሞራል የሚሰጥ ነው። መጪው ትውልድም ያማረችና የተዋበች ሀገር እንዲረከብ የሚያደርግ መሆኑን የሚናገሩት ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ በቀለች መግረ ናቸው።
ልማቱ የሀገር ውስጥና የውጭ ዜጎች የቱሪስት ፍሰትን በማሳደግ፣ ዜጎች በጽዱ አካባቢ እንዲኖሩ በማድረግ፣ የትራንስፖርት ፍሰትን በማሳለጥ ለአካባቢው ማህበረሰብም ሆነ ለሀገር እድገት በርካታ ጠቀሜታዎችን ይዞ የመጣ መሆኑንም በመገረም ውስጥ ሆነው አጫውተውኛል።
ሁሉም ዜጋ ለሀገር እድገት በሚችለውና ባለው አቅም የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይገባል ያሉት ወይዘሮ በቀለች፤ እየተሠራ ያለው የልማት ሥራ ሁሌም ጠብቁኝ የሚልና ከጊዜ ወደጊዜ ለውጥን የሚፈልግ በመሆኑ ዜጎች በባለቤትነት ስሜት ሊጠብቁት ይገባልም ብለዋል።
በኮሪዶር ልማቱ የሥራ ዕድል የተፈጠረለት፤ በሙያው ግንበኛ ሆነው ወንድም አቸነፈ በበኩሉ፤ ከሰሜን ጎንደር መጥቶ በአዲስ አበባ የኮሪዶር ልማት ሥራ ተሳታፊ ነው። አሁን የሚያገኘው ደመወዝ ከዚህ በፊት በግንበኝነት ከሚከፈለው የተሻለ መሆኑን፤ ከሚያገኘው ገቢ ጥቂቱን እንደሚቆጥብ አመልክቷል። በኮሪዶር ልማቱ የሥራ እድል ከመፍጠርም ባለፈ ከቻይናዎች የእውቀት ልምድ እንዲቀስም እንደረዳው ተናግሯል፤ ይህም ወደፊት በሥራው ላይ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍ ያለ እንዲሆን አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስታውቋል። አሁን ላይ በካዛንቺስ የኮሪደር ልማት የእግረኛ፣ የብስክሌትና የአስፋልት መንገዶች ግንባታን አጠናቀው የፍሳሽ መስመር የመጨረሻ ሥራ ላይ እንደሚገኙ ተናግሯል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም