የለውጥ ጉዞው አልፋ እና ኦሜጋ!

በአንድ ሀገርም ሆነ ማኅበረሰብ ውስጥ ትውልድ በጊዜ ሂደት ውስጥ ይመጣል ይሄዳል ፤ ይህ ተፈጥሯዊ እውነታ ነው። አንዳንዱ ትውልድ ይብዛም ይነስ እንደየዘመኑ ለመጪው ትውልድ የሚከፍለው ዋጋ አለ። የቀደመው ትውልድ በከፈለው ዋጋ የተሻለ ሕይወት የመኖር እድል ያለው እንዳለ ሁሉ፤ ለሌሎች ዋጋ ከፋይ የሚሆንም አለ። ተስፋቸውን በመጪው ትውልድ ውስጥ ዋጋ አለው ማለት ነው።

ይህ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን አዲስ እውነት አይደለም። ከቀደሙት አባቶቻችን ከወረስናቸው ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ እሴቶች ውስጥ በስፋት የሚስተዋል ፤ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ ፤ የዕለት ተዕለት ሕይወታችንን ሳይቀር የገዛ ፤ ስለነጻነትም ሆነ ስለነገ ተስፋችን ስናወራም አብዝተን የምንዘክረው እውነታ ነው።

በዘመናት መካከል እንደ ሀገር ሆነ እንደ ማኅበረሰብ የመጣንበትን የሕይወት ፈተና ፣ ተግዳሮት እና ውጣውረድ አሸንፈን እዚህ የደረስነው ፣ አንድም የቀደሙት አባቶች ስለ ራሳቸውን እና ስለእኛ በከፈሉት ዋጋ ፤ አለበለዚያም እኛ ስለ ራሳችን እና ስለ መጪው ትውልድ በከፈልነው እና እየከፈልነው ባለው ዋጋ ነው። ይብዛም ይነስም ባልተከፈለ ዋጋ የሚኖር ትውልድ የለም።

እንደ አንድ ኩሩ ፤ ነጻነቱን የራሱ አድርጎ ማጽናት እንደቻለ ሕዝብ ስናወራ ፣ አባቶቻችን ስለነጻነት በከፈሉት ዋጋ ላይ ቆመን ነው። የተከፈለልን ዋጋ የቱንም ያህል ውድ እና ብዙ የሕይወት መሥዋዕትነት የጠየቀ ቢሆንም ፤ ነጻነቱ ተጨባጭ በመሆኑ የዚህ ትውልድ የክብር እና የኩራት ምንጭ ሆኗል።

የነጻነት ክብር ትውልድ ተሻጋሪ መሆኑ ፤ በትውልድ ውስጥ የነጻነትን መንፈስ እና መነቃቃት በመፍጠር ትውልዱ ለነጻነቱ ቀናኢ፣ ስለነጻነት ለሚከፈል ዋጋ ሁሌም ዝግጁ እንዲሆን አግዞታል። ይህ የቀደመው ትውልድ ብቻ ሳይሆን አሁን ያለው ትውልድም ትልቅ እሴት ነው።

ስለ ተስፋ ስናስብም የራሳችን ብሩህ ዕጣ ፈንታ/ተስፋ በቀጣይ ትውልድ ውስጥ ማየት እና ለዚህም አቅሞችን ሁሉ ዋጋ አድርጎ መስጠት የተለመደ ነው። ይህ እንደ ማኅበረሰብ ከመጣንበት የሕይወት ውጣ ውረድ የሚቀዳው ማኅበረሰባዊ እሳቤያችን ዛሬም በእያንዳንዱ ቤተሰብ ሕይወት ውስጥ በስፋት የሚታይ ነው።

ትናንት እንደሆነው ሁሉ ወላጆች ለልጆቻቸው የተሻለ ሕይወት የሚቆጥቡት አቅም የላቸውም። ለልጆች የሚከፈል የትኛውም አይነት ዋጋ ለራስ ተስፋ / ነገዎች የሚከፈል ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ይህ የትናንት ብቻ ሳይሆን የብዙ ትናንቶች ማኅበረሰባዊ የሕይወት ተሞክሯችን ነው ።

እንደማኅበረሰብ ረጅሙን ዘመን አንዱ ትውልድ ለቀጣይ ትውልድ ዋጋ እየከፈለ ቢመጣም በዘመናት ውስጥ ያለው የሕይወት ጉዟችን ብዙም ወደ ተስፋችን ፈቅ ያደረገን አልነበረም ፣ ዛሬያችን የብዙ ትውልዶችን ርብርቦሽ ቢጠይቅም ፣ እንደ ማኅበረሰብ ያለምነውን ህልም መኖር የሚያስችል አቅም አልፈጠርንም።

በየዘመኑ የራሳችንን እና የመጪ ትውልዶችን እጣ ፈንታ ለመቀየር ብዙ የለውጥ ንቅናቄዎችን ብናደርግም ፤ ለለውጥ መነቃቃታችን ብዙ ዋጋ ብንከፍልም ፤ ለረጅም ዘመናት የመጣንበት ይህ መንገድ የተስፋችን ባለቤት አላደረገንም። ትውልዶች ተስፋቸውን ተሳልመው ከማለፍ ያለፈ የታሪክ ትርክት አልፈጠርንም።

ከዚህ ተስፋን ከሩቅ እየተሳለሙ ከማለፍ አዙሪት ለመውጣት ከሁሉም በላይ ተስፋችንን ተጨባጭ ማድረግ የሚያስችል ሁለንተናዊ አቅም መፍጠር ይኖርብናል። ተስፋን ከሩቅ ስሎ እና ተሳልሞ ከማለፍ ይልቅ አቅርበን የራሳችን ለማድረግ የሚጠበቅብንን መሥዋዕትነት ሁሉ ለመከፈል መንቀሳቀስ መቻል አለብን።

ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ ራስን በሁለንተናዊ መልኩ ስለተስፋ መሥዋዕት ማድረግ የሚያስችል ቁርጠኝነት መፍጠር ፤ ጊዜያዊ ፈተናዎችን ተቋቁሞ መሻገር የሚያስችል ማኅበረሰባዊ ሥብዕና መገንባትም ይኖርብናል።

ከለመድነው ፤ የራሳችን አድርገን ከተቀበልነው የዕለት ተዕለት ሕይወት ወጥተን ፤ተስፋችን የሚጠይቀውን መሥዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀት ፤ በቤተሰብ ደረጃ ለትውልዶች የምንከፍለውን ዋጋ ማህበረሰባዊ አውድ እንዲኖረው አድርጎ መንቀሳቀስ የሚያስችል የአስተሳሰብ መታደስ ያስፈልገናል።

በተለይም የለውጡ ትውልድ ሀገራዊ ለውጡ የተወሰኑ ግለሰቦችን፣ ቡድኖችን እና የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለመጥቀም የመጣ ሳይሆን፤ እንደ ሀገር የሕዝባችንን ትናንቶች የመለወጥ ፤ ተስፋን ተሳልሞ የማለፍ እርግማንን የመስበር አልፋ እና ኦሜጋ መሆኑን ተገንዝቦ ፤ራሱን ለሁለንተናዊ የለውጥ አበርክቶ ማዘጋጀት ይጠበቅበታል!

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You