በአዲስ አበባ ከተማ የካ ክፍለ ከተማ አንቆርጫ በተለምዶ መድኃኒዓለም ፓርክ እየተባለ የሚጠራው አካባቢ ቲሸርት በለበሱ ችግኝ በሚተክሉ ሰዎች ተሞልቷል። በአካባቢው በተወሰነ ርቀት ላይ የግልና የመንግሥት ተቋማት ታፔላዎች ተሰቅለዋል።
በአውቶቡሶች ተሳፍረው የመጡ ሠራተኞች እየወረዱ ታፔላ ወደ ተሰቀለባቸው አካባቢዎች ችግኞቻቻውን ይዘው ጉዟቸውን ቀጠሉ። በተቆፈሩ ጉድጓዶች የወይራ፤ ጽድ፣ ዋንዛና ዝግባና መሰል አገር በቀል ዛፎችን ይተክላሉ።
ወይዘሮ የምስራች አበራ ቡትስ ጫማ ተጫምተው ከልጆቻው ጋር ነው በችግኝ መትከያው አካባቢ የተገኙት። የጽድ ችግኝ ሲተክሉ አገኘናቸው። ችግኝ የተከሉበት ስፍራ ከእሳቸው መኖሪያ ቤት ቅርብ ርቀት ላይ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህ አካባቢ ችግኝ መትከላቸው ደስተኛ እንዳደረጋቸው ይገልጻሉ።
«ዓለም ንጹህ አየር ባለማግኘትና በሙቀት መጨመር እየተቸገረ ባለበት በዚህ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ ዳርቻዎችን አረጓዴ ማድረግ ለከተማው ሕዝብ እንደሚጠቅም ወይዘሮ የምስራች ይናገራሉ።
ሁሉም ሰው የተከላቸውን ችግኞች በፍላጎት የመንከባከብ ግዴታ እንዳለበት የሚናገሩት ወይዘሮ የምስራች ፣«ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለ50 ሰው ጌጡ ነው» በማለትም የመንከባከቡ ሥራ ርብርብ የሚያስፈልገው መሆኑን ይጠቁማሉ። «ሁሉም የተከላቸውን ችግኞች ከተንከባከበ የአረንጓዴ ልማትን በቀላሉ እውን ማድረግ ይቻላል።እኔም ሆንኩ ቤተሰቤ የተከልናቸውን ችግኞች ለመከባከብ ዝግጁ ነን» ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጮች ማህበር አባልና የዮት ኮንስትራክሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ዮናስ ሙሉጌታ በዚሁ ስፍራ በማህበራቸው አስተባባሪነት የግራቪያ፣ ሸውሻዌ፣ ወይራ ሲተክሉ አገኘናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ኢትዮጵያን የአረንጓዴ ምድር ለማድረግ ያላቸውን አቋም በመደገፍ ችግኝ ለመትከል መነሳሳታቸውን ይገልጻሉ። ማህበሩ ከ600 በላይ ችግኞችን መትከሉን ጠቅሰው፣ እሳቸው ትናንት በግላቸው አራት ችግኞችን ተክለዋል። የችግኝ እጥረት ባይኖር 30 እና 40 ለመትክል አቅደውም እንደነበር ነው የተናገሩት።
«አገር አቀፍ የችግኝ ተከላ ዘመቻው ትልቅ አገራዊ ትርጉም አለው» የሚሉት ኢንጅነሩ ዘመቻው የመትከል ብቻ ሳይሆን የመንከባከብን ኃላፊነት ጭምር የሚጠቃልል መሆኑን ይገልጻሉ። «ችግኞቹ ዛፎች እንዲሆኑ፣ ለምለሚቱ የምትባለው ግን ያልሆነችውን ኢትዮጵያ በርግጥም ለምለም ለማድረግ ችግኞችን መትከልና መንከባከብ ይገባል።» ያሉት ኢንጂነሩ፣ ማህበራቸውም ችግኞቹን ለመንከባከብ ማቀዱን አስታውቀዋል።«ለዚህም የኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጮች ማህበር በቂ በጀት መድቧል» ብለዋል።
ኢንጂነሩ፤ በየአካባቢው የደን ሽፋን በአደገ ቁጥር የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም ብቻ ሳይሆን አገሪቱን የቱሪስት መናገሻና የኢኮኖሚ ጥቅም ማግኛ ማድረግ ይቻላል የሚል ሀሳብ አላቸው።
ቄስ ኃይለማርያም ካሳ «አንቆርጫ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት አባቶች የእምነት አስተማሪ ብቻ ሳይሆኑ ለሁሉም በጎ ነገሮች አርአያ መሆን አለባቸው» በሚል ችግኝ ለመትክል በስፍራው ተገኝተዋል።«አንድ በሬ ስቦ አንድ ሰው አስቦ አይሆንም» የሚለውን ብሂል የጠቀሱት ቄስ ኃይለማርያም፣ ችግኞችን ተንከባክቦ ማሳደግና መጠበቅ፣ ደኖች እንዳይጨፈጨፉ መከላከል የሁሉም ሰው ኃላፊነት መሆን እንዳለበት ያስገነዝባሉ።
የቆሎ ተማሪ እያሉ በአንድ ሺ ካሬ ሜትር ላይ ችግኞችን መትከላቸውን ጠቅሰው፣ «ፍራፍሬዎች እና የእንጨት ዛፎችን መትክል ለጥላ አገልግሎት ከመዋል በተጨማሪ አካባቢው እንዲቀዘቅዝ ያስችላሉ» ሲሉ ይገልጻሉ። የኢኮኖሚ ጥቅም የሚያስገኙ መሆናቸውንም ነግረውናል። እንክብካቤ እንደሚያስፈልጋቸው፣ ቢቻል ቶሎ እንዲያድጉ ውሃ ማጠጣት እንደሚያስፈልግም ይናገራሉ። ካልተቻለ ደግሞ ከእንስሳት ንክኪ ነፃ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባ፣ ካልተቆረጡ አገሪቱን የአረንጓዴ ምድር ማድረግ እንደሚቻል ይገልጻሉ።
የ21 ዓመቱ ወጣት አብዱ ኢብራሄም በኮተቤ የ02 ቀበሌ ነዋሪ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይን የችግኝ ተከሉ ጥሪ ተከትሎ በራሱ ተነሳሽነት በስፍራው በመገኘት ችግኞችን ተክሏል።
20 ችግኝ ለመትክል አቅዶ በስፍራው ቢገኝም በችግኝ እጥረት ሳቢያ እቅዱን ማሳካት አለመቻሉን ይገልጻል።የሚተክለው የሰው ቁጥር ከመብዛቱ አንጻር በስድስት ችግኝ መወሰኑ ቁጭት ፈጥሮበታል።
ብዙ የሰው ጉልበትና ጊዜ የጠፋባቸውና የተለፋባቸው ችግኞች እንዲጸድቁ ሁሉም የተከለውን ችግኝ መንከባከብ እንዳለበት ጠቅሶ፣ በተለይ ችግኞቹ የተተከሉበት አካባቢ ኅብረተሰብ አደረጃጀት ፈጥሮ በዘላቂነት መንከባካብ እንደሚኖርበት ያስገነዝባል።
የልደታ ጤና ጣቢያ የጤና ባለሙያ አቶ ስታየሁ አሰፋ እንደሚለው አንድ ሕፃን ልጅ የእናት ጡትና ተጨማሪ ጡት እንደሚያስፈልገው ሁሉ ችግኞቹም ተንከባካቢ ያስፈልጋቸዋል። ችግኝ ለመትክል የታየው መነቃቃት ችግኙ አድጎ ዛፍ እስኪሆን ድረስም መቀጠል እንዳለበት ያሳስባል። «ተቋማት ተከልሎ በተሰጣቸው ቦታ የተከሉትን ችግኝ መንከባከብ ይጠበቅባቸዋል። በዘላቂነት ደግሞ በአካባቢው ያሉ ወጣቶችን በማደራጀት እንዲጠበቁት ማድረግ ያስፈልጋል» ይላል።
በአካባቢው ዋንዛ ዝግባ፣ ጽድ ወይራና ሌሎች አገር በቀል ዛፎች ችግኝ ተካላ ተካሂዷል። በአካባቢው ችግኝ የተከሉ ተቋማትም በቀጣይ ችግኞቹን ለመንከባከብ አጥር የሚያስፈልጋቸውን ስፍራዎችንም ለማጠር ጭምር ዕቅድ መያዙ ተገልጿል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 23/2011
ጌትነት ምህረቴ