
አዲስ አበባ፡- ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰሙነ ሕማማት በጸሎተ ሐሙስ ያሳየውን ትህትናና ዝቅ ማለት ምዕመኑም በሕይወቱ ሊተገብረው ይገባል ሲሉ መጋቢ ሀዲስ አባ ወልደገብርኤል ገብረኢየሱስ ቆሞስ ገለጹ፡፡
በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ስብከተ ወንጌል ክፍል አገልግሎት አካል የሆኑት መጋቢ ሀዲስ አባ ወልደገብርኤል ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ አምላክ ከሰሙነ ሕማማት አንዱ በሆነው በጸሎተ ሐሙስ የደቀ መዛሙርቱን እግር ዝቅ ብሎ በማጠብ ትህትናን እና ዝቅ ማለትን በተግባር አስተምሯል፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑም ይህንን በሕይወቱ ላይ በመተግበር ከሌሎች ጋር በሰላምና በፍቅር ሊኖር ይገባል ሲሉ ተናግረዋል ፡፡
መጋቢ ሀዲስ አባ ወልደገብርኤል ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የደቀመዛሙርቱን እግር ዝቅ ብሎ ካጠባቸው በኋላ በመካከላቸው ሆኖ እናንተም ለወንድሞቻችሁ የበላይ ስትሆኑ ለታናናሾቻችሁ ይህንን አድርጉ ብሎ አስተምሯል፡፡ በእዚህም እለት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መታዘዘን እና ዝቅ ማለትን ለማስታወስና ለማስተማር ቅዱስ ፓትሪያርኩ በጸሎተ ሐሙስ የቅዱስ ጳጳሳቱን እግር ዝቅ ብለው ያጥባሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን እንግዳን በአክብሮት መቀበል እግር ማጠብ ወላጆችን እና ታላላቆችን ማክበር የቆየ ባሕላችን ቢሆንም አሁን ላይ ግን የትህትና ምሳሌያችን እየተዳከመ ነው ያሉት መጋቢ ሀዲስ አባ ወልደገብርኤል፤ የትህትና መጓደል ደግሞ እርስ በእርስ እንድንጠፋፋ የሚያደርግ በመሆኑ እንደ ከእዚህ ቀደሙ ልንተገብረው የሚገባ እንጂ ሊደበዝዝ እንደማይገባ አስገዝበዋል፡፡
እንደ መጋቢ ሀዲስ አባወልደገብርኤል ገለጻ፤ ክርስቶስ የይሁዳንም እግር ዝቅ ብሎ በማጠብ ጭምር ያለውን ትህትና በማሳየት ዓለሙን ሁሉ ያለምንም ልዩነት በመውደድ ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ የሰው ልጆችም ሰውን በሰውነቱ በመውደድ ፣ በማክበር ጌታችን ያስተማረን በመሆኑም በጸሎተ ሐሙስ ጌታችን ያደረገው የሚያስተምረው ትልቁ ትህትናና ፍቅርን ፣ ራስን አሳልፎ ለሌሎች መስጠትን ልንማርበትና የሕይወታችን አካል ልናደርገው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ክርስቶስ ራሱን ለሰው ልጆች አሳልፎ እንደሰጠው ያለንን በማካፈል ለተቸገሩ ወገኖች በመድረስ ፣ የምንሰጠው ባይኖረን እንኳን መልካም አንደበትን በመያዝ ያዘኑ ሰዎችን ማጽናናት፣ የደከሙ ሰዎችን በመልካም አንደበት ማበርታት ይገባናል ሲሉ አመልክተዋል፡፡
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9 ቀን 2017 ዓ.ም