
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቬትናም ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ነው
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያና ቬትናም ለሥራ የተነሳሳ ወጣት ሕዝብ ያለን፣ ለልማት እና እድገት የቆረጥን እንዲሁም በታሪካችን ሂደት በፅናታችን የምንታወቅ ሀገራት ነን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቬትናም ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትናንት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት፤ የቬትናም ጠቅላይ ሚኒስትር ፋም ሚን ቺን በይፋዊ ጉብኝታችን ወቅት ላደረጉልን የደመቀ አቀባበል እና የክብር መስተንግዶ
አመሰግናለሁ። ኢትዮጵያና ቬትናም የሚያመሳስሏቸው ብዙ የጋራ ጉዳዮች አሏቸው። ሁለታችንም ትልቅ እና ለሥራ የተነሳሳ ወጣት ሕዝብ ያለን፣ ለልማት እና እድገት የቆረጥን እንዲሁም በታሪካችን ሂደትም በፅናታችን የምንታወቅ ሀገራት ነን ብለዋል።
የቬትናም ጠቅላይ ሚኒስትር ፋም ሚን ቺን ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸው፤ውይይታቸው በንቁ ተሳትፎ የሚገለጥ እና ጥልቀትም እንደነበረው አውስተዋል።
ለጋራ እድገት እና ትብብር ያለንን ፅኑ የጋራ ተነሳሽነትም አንፀባርቀናል። የሃሳብ ልውውጣችን በሁለቱ ሀገሮቻችን መካከል ለጠንካራ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር በር ከፍቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር ፋም ሚን ቺን በቅርብ ኢትዮጵያን በሚጎበኙበት ወቅት የጋራ ርዕዮቻችንን የበለጠ የምናጠናክርበት እና በዛሬው የዓለማችን አውድ የሁለትዮሽ ግንኙነታችንን ይበልጥ የምናፀናበት ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በሀኖይ ቬትናም ይፋዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በ2025 የፒ4ጂ ቬትናም ጉባኤ ላይም እንደሚሳተፉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ አመልክቷል፡፡
በቆይታቸው ከቬትናም የፀሀይ ኃይል ማመንጫዎች በማምረት ወደ ውጭ የሚልከውን ቶዮ ሶላር የተባለውን ፋብሪካ ጎብኝተዋል። ድርጅቱ በቅርቡ በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በመግባት በኢትዮጵያ ሥራ ጀምሯል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድርጅቱ ከፀሀይ ኃይል ማመንጫ ምርት ባሻገር የኃይል ማመንጫ ፋብሪካ እንዲያቋቁም አበረታተዋል። ይኽም ሀገራችን ከያዘችው የአረንጓዴ አሻራ ፖሊሲ ጋር የተናበበ በማደግ ላይ ላለው የኃይል ጥያቄም ምላሽ በመስጠት ሊያግዝ የሚችል መሆኑን አውስተዋል።
ኢትዮጵያና ቬትናም በአዲስ አበባና በሃኖይ መካከል በኢትዮጵያ አየር መንገድ የቀጥታ በረራ የሚያመቻች የሲቪል አቪዬሽን ስምምነት ተፈርሟል። ተጨማሪም በንግድ እና በትምህርት ትብብር ላይ የመግባቢያ ስምምነቶች ተፈርመዋል።
ሁለቱ መሪዎች የሁለትዮሽ ውይይትም አድርገዋል። መሪዎቹ የትብብር ሰነዶች የፊርማ ሥነሥርዓት ላይም ተገኝተዋል። በውይይቱ በሁለቱ ሀገራት የተካሄዱ ማሻሻያዎች፣ ለትብብር የሚሆኑ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በተለይም የልምድ ልውውጥንና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሃሳብ ተለዋውጠዋል።
በንግድ እና በትምህርት ትብብር ላይ የመግባቢያ ስምምነቶች ተፈርመዋል። በተጨማሪም በአዲስ አበባ እና በሃኖይ መካከል በኢትዮጵያ አየር መንገድ የቀጥታ በረራ መንገድ የሚያመቻች የሲቪል አቪዬሽን ስምምነት ተደርጓል።
የቬትናም ጠቅላይ ሚኒስትር ፋም ሚን ቺን በቤተ መንግሥታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ይፋዊ የአቀባበል ሥነ-ሥርዓት አድርገውላቸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቬትናም ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከተመሠረተ ከሃምሳ ዓመታት በኋላ የመንግሥት መሪ ያደረጉት የመጀመሪያ ይፋዊ የኦፊሴላዊ ጉብኝት መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
በቬትናሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ፋም ሚን ቺን እና ባለቤታቸው ግብዣ እየተካሄደ ያለው ጉብኝቱ፤ የኢትዮጵያ ልዑካን በ4ኛው ዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ትብብር (P4G) ጉባዔ ላይ መሳተፍን ያካትታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከትናንት በስቲያ ቬትናም ሲገቡ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡
እንደ ቬትናም የዜና ድርጅት (ቪኤንኤ) ዘገባ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጉብኝት፤ የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከተመሠረተበት ከጎርጎሮሳውያኑ 1976 ወዲህ በኢትዮጵያ መሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቬትናም የተደረገ ኦፊሴላዊ ጉብኝት ነው።
በተጨማሪም ጉብኝቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ከሰባት ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የከፍተኛ ልዑካን ግንኙነት ነው። ከእዚህ ቀደም ከቬትናም ባለሥልጣናት ጋር በተደረገ ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ከቬትናም ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት አፅንኦት ሰጥተው መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያ እና ቬትናም የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመሩት በታኅሣሥ 1969 ዓ.ም ሲሆን፤ ሁለቱ ሀገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመሩበትን የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል በሚቀጥለው ዓመት ያከብራሉ። የመጀመሪያው የኢትዮ-ቬትናም የጋራ ፖለቲካዊ ምክክር ባለፈው የካቲት ወር 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ እና ቬትናም ከ10 እስከ 15 ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ የንግድ ልውውጥ አላቸው። ኢትዮጵያ ቡና፣ ቅመማ ቅመም፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ የቆዳ ውጤቶች እና ማዕድናትን ወደ ቬትናም ስትልክ፤ ቬትናም በበኩሏ የግብርና ውጤቶችን፣ የፍጆታ እቃዎችን፣ ማሽነሪዎችንና ኬሚካሎችን ወደ ኢትዮጵያ ትልካለች።
ኢኖቬሽን፣ አረንጓዴ ልማት እና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለሁለቱ ሀገራት ዘላቂ የምጣኔ ሀብት እድገት ቁልፍ ግብዓቶች ናቸው። ሁለቱ ሀገራት በአረንጓዴ ልማት፣ በታዳሽ ኃይልና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ጥናትና ምርምር፣ በሰው ሀብት ልማት እንዲሁም በግብርና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ለማሳደግ እንደሚሠሩ ይጠበቃል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8 ቀን 2017 ዓ.ም