የምንማር መንግሥት ከአንድ ዓመት በፊት በቁጥጥር ስር ያዋላቸውንና የሰባት ዓመታት እስር የፈረደባቸውን ሁለት የሮይተርስ (Reuters) ጋዜጠኞች እንዲፈታ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚደረገው ጫና ቀጥሏል፡፡ ዋ ሎን እና ካው ሶ ኡ የተባሉት ጋዜጠኞች የታሠሩበትን አንደኛ ዓመት አስመልክቶ ጋዜጠኞችና የመብት ተሟጋች ቡድኖች ባሰናዱትና በምያንማር ዋና ከተማ በተካሄደ ሰልፍ ‹‹ጋዜጠኝነት ወንጀል አይደለም›› የሚል መፈክር በማሰማት፣ መንግሥት ጋዜጠኞቹን እንዲለቅ ተጠይቋል፡፡
በአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሕንፃ አካባቢ በተካሄደው በዚህ ሰልፍ ላይ የተገኙት ሰልፈኞች፣ የአገሪቱ መንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ሥራቸውን እንዳያከናውኑ እንዲሁም ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ለማፈን የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዲያቆም ጠይቀዋል፡፡
የ32 ዓመቱ ዋ ሎን እና የ28 ዓመቱ ካው ሶ ኡ ከአንድ ዓመት በፊት የታሰሩት የምያንማር ጦር በሮሂንጋዎች ላይ የፈፀመውን ጥቃት አስመልከተው በሰሩት ዘገባ ምክንያት ነው፡፡ ጋዜጠኞቹ ጦሩ በመስከረም 2010 ዓ.ም በሰሜናዊ ራኪን ግዛት ውስጥ በሚኖሩ የሮሂንጋ ሙስሊሞች ላይ የፈፀመውን ጥቃት በተመለከተ ዝርዝር ዘገባ ሰርተው ነበር፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በመላው ዓለም የሚገኙ ጋዜጠኖችና የመብት ተሟጋች ቡድኖች ሁለቱ የሮይተርስ ጋዜጠኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ እየጠየቁ ነው፡፡ ‹‹አታን (Athan) የተባለው የመብት ተሟጋች ቡድን መስራችና ዳይሬክተር ማንግ ሳንግ ካ ‹‹ጋዜጠኞቹ የታሰሩት ያላግባብ ነው፤ የተፈረደባቸውም ተገቢ ባልሆነ የሕግ ድንጋጌ ነው፡፡ የሁላችንም ፍላጎት ጋዜጠኞቹ በነፃ እንዲለቀቁ ነው›› ብሏል፡፡
ፓሊንግ ሶ ኡ የተባለ ጋዜጠኛ፣ የምያንማር መንግሥት በድርጊቱ ሊያፍርና ጋዜጠኞቹን በአስቸኳይ ሊፈታ እንደሚገባ ተናግሯል፡፡ ዲፕሎማቶች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥራ ኃላፊዎችና ታዋቂ ግለሰቦች በጋዜጠኞቹ ላይ የተላለፈውን ውሣኔ ኮንነዋል፤ የምያንማር መንግሥት ጋዜጠኞቹን በነፃ እንዲያሰና ብታቸውም ተይቀዋል፡፡
የሮይተርስ የዜና ዋና አርታዒ ስቴፈን አድለር በበኩላቸው፣ የጋዜጠኞቹ እስራት የምያንማር መንግሥት ለሕግ የበላይነትና ለዴሞክራሲ ሥርዓት መስፈን ያለውን ቁርጠኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጋዜጠኞቹ እስር ቤት ውስጥ በሚያሳልፏቸው በእያንዳንዱ ቀናት የአገሪቱ መንግሥት ለፍትህ መስፈን ሊያበረክተው የሚገባው አስተዋጽኦ እያመለጠው እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰባት ዓመታት እስራት ተፈርዶባቸው በእስር ቤት የሚገኙት እነዚህ ጋዜጠኞች የዝነኛውና የአንጋፋው ‹‹ታይም (Time)›› መጽሔት ‹‹የዓመቱ ሰው (Person of the Year)›› ሽልማት ውስጥ ከተካተቱት ግለሰቦች መካከል ሆነዋል፡፡
ከሁለቱ ጋዜጠኞች በተጨማሪ የመጽሔቱ የዘንድሮው ተመራጮች ግድያው ዓለምን እያነጋገረ የሚገኘው ሟቹ ሳዑዲ አረቢያዊ ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ፣ ባለፈው ሰኔ ወር አምስት ሠራተኞቹ (አራት ጋዜጠኞችና አንድ የሽያጭ ሠራተኛ) የተገደሉበት የአሜሪካው ‹‹ካፒታል ጋዜጣ (Capital Gazette)›› ፣ ፍሊፒናዊቷ የ2018 የ‹‹ሲ.ፒ.ጄ (Committee to Protect Journalists – CPJ)›› የዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ሽልማት አሸናፊዋ ማሪያ ሬሳ ናቸው፡፡
ምያንማር በወታደራዊ መንግሥት በምትተዳ ደርባቸው ዓመታት የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ክፉኛ የታፈነ እንደነበር ይነገራል፡፡ በወቅቱም በርካታ ጋዜጠኞች ለስደት፣ ለእስራትና ለሞት ተዳርገዋል፡፡ ቴይን ሴይን የተባሉት የወታደራዊው መንግሥት ባለሥልጣን እ.ኤ.አ በ2011 ወደመሪነት ከመጡ በኋላ በአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን አሠራርና ነፃነት ላይ ተስፋ ሰጪ ለውጥ መታየት ጀምሮ ነበር፡፡ ቅድመ ምርመራ እንዲቀርና ታስረው የነበሩ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ አድርገዋል፡፡ ‹‹ይሁን እንጂ እንዲም ሆኖ ጋዜጠኞች ስለአገሪቱ ጦርና ስለወታደራዊ መሥሪያ ቤቱ የሙስና ቅሌት መዘገብ እንደማይችሉት ያውቁ ነበር፤ የሁለቱ የሮይተርስ ጋዜጠኞች እስራትም ምያንማር ውስጥ ጋዜጠኞች ምንም ዋስትና እንደሌላቸው ማሳያ ነው›› ይላሉ የሲ.ፒ.ጄ የደቡብ ምስራቅ እስያ ተወካይ ሻውን ክሪስፒን፡፡
እ.ኤ.አ በ2016 ለረጅም ዓመታት በመብት ተሟጋችነታቸው የሚታወቁት ኦንግ ሳን ሱ ኪዪ ወደመሪነቱ መንበር ሲመጡ ለፕሬስ ነፃነት እንደትልቅ ድል ተደርጎ ተቆጥሮ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እንደተጠበቀው ሳይሆን መቅረቱን ክሪስፒን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ናሽናል ሊግ ፎር ዴሞክራሲ (National League for Democracy – NLD)›› የተባለው የኦንግ ሳን ሱ ኪዪ ፓርቲ ምርጫ አሸንፎ ስልጣን በያዘ ማግሥት በእስር ላይ የነበሩ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች ቢፈቱም ፓርቲው ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እውቅናና ፈቃድ ውጭ መረጃ ለጋዜጠኞች እንዳይሰጥ ያፀደቀው ሕግ የተስፋ ጭላንጭልን አይቶ ለነበረው የአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ አስደንጋጭ ሆኗል፡፡
በተለይ ደግሞ መንግሥትን የሚቃወም ማንኛውንም መልዕክት በፌስቡክ ማጋራት ለክስ እንደሚዳርግ የሚደነግገው የአገሪቱ የቴሌኮሚዩኒኬ ሽንስ ሕግ፣ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ላይ የተጋረጠ አደጋ ሆኗል፡፡ የ‹‹አታን›› የጥቅምት ወር ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ ‹‹ናሽናል ሊግ ፎር ዴሞክራሲ›› ፓርቲ ሥልጣን ከያዘ ወዲህ 44 ጋዜጠኞች ለፍርድ ተከሰው ለችሎት ቀርበዋል፤ ከነዚህ መካከልም አብዛኞቹ ጋዜጠኞች ለችሎት የቀረቡት በዚሁ የቴሌኮሚዩኒኬሽንስ ሕግ ድንጋጌ ምክንያት ነው፡፡
በዚሁ የሕግ ድንጋጌ ምክንያት ለእስር ተዳርጎ የነበረው የ ‹‹አታን›› መስራችና ዳይሬክተር ማንግ ሳንግ ካ ‹‹ሀሳብን በነፃነት የመግለፅና የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት በምንማር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ መጥቷል፤ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ካልተከበረ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ አደጋ ላይ ይወድቃል›› ይላል፡፡
ጋዜጠኞች የአገሪቱ ጦር በንቃት በሚንቀሳቀ ስባቸው አካባቢዎች ተጉዘው ዘገባዎችን ለመሥራት ጥያቄ ሲያቀርቡ ፈቃድ እንደማያገኙና ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞችም ወደ አገሪቱ ለመግባት የሚያልፉት ሂደት አድካሚና ቁጥጥር የበዛበት እንደሆነ ይነገራል፡፡
‹‹ዴሞክራቲክ ቮይስ ኦፍ በርማ (Democratic Voice of Burma)›› ለተባለ መገናኛ ብዙኃን ትሠራ የነበረችው ኪምበርሌይ ፊሊፕስ የተባለች ጋዜጠኛ ሕዝቡ ለጋዜጠኞች ያለው አመለካከት መቀየሩንና መረጃ ለመስጠት የነበረው ፍላጎት በእጅጉ መቀነሱን ትናገራለች፡፡
የምያንማር መንግሥት ባለሥልጣናት ከወታደራዊ ጉዳዮች ውጭ ባሉ አጀንዳዎች ላይ እንኳ ለጋዜጠኞች መረጃ ለመስጠት ፍላጎት እንደሌላቸው በግልፅ እያሳዩ ነው፡፡ ለአብነት ያህል የአገሪቱ መንግሥት ቃል አቀባይ ዛው ሃታይ በቅርቡ ከጋዜጠኞች የሚቀርቡላቸውን የስልክ ጥሪዎች እንደማያስተናግዱና በአስራ አምስት ቀናት አንድ ጊዜ ብቻ መግለጫ እንደሚሰጡ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
የምያንማር ፕሬስ ካውንስል አባል የሆኑት ዛያር ሀሊንግ፣ የአገሪቱ መንግሥት መረጃን ለጋዜጠኞች እየሰጠ እነዳልሆነ ገልፀው፣ ይህም ትክክለኛ መረጃዎችን ለማግኘትና ሀሰተኛ መረጃዎችን ለማጣራት ትልቅ ፈተና እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡ በእስር ላይ ሚገኙትን የሮይተርስ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ አክቲቪስቶች ጫና ለማሳደር ቢሞክሩም ጥረታቸው በከባድ ፈተናዎች የታጀበ እንደሆነም ይገልፃሉ፡፡
ባለፈው ወር መጨረሻ ላይ የአገሪቱ መሪ ኦንግ ሳን ሱ ኪዪ ከምያንማር ፕሬስ ካውንስል አባላት ጋር ሲወያዩ በመገናኛ ብዙኃን ላይ ብዙም እምነት እንደሌላቸውና ሁሉንም መረጃ ለጋዜጠኞች ክፍት ማድረግ ተገቢ ነው ብለው እንደማያምኑ መናገ ራቸው ብዙዎችን ግራ አጋብቷል፡፡ ይሁን እንጂ ካውንስሉ ችግሩ መፍትሄ እንዲያገኝ ጥረቱን እንደሚቀጥል ሀሊንግ ተናግረዋል፡፡
ደቡብ ምስራቃዊቷ አገር ምያንማር በ2108 የድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን የፕሬስ ነፃነት መለኪያ መሰረት ከ180 አገራት መካከል 137ኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት ስድስት ደረጃዎችን አሽቆልቁላለች፡፡
የምያንማር መንግሥት የአገር ምስጢር የሆነ ወታደራዊ መረጃ ለዘገባ ተጠቅማችኋል ተብለው የሰባት ዓመታት እስራት የተበየነባቸው የሮይተርስ ጋዜጠኞችን እንዲፈታ የሚደረገው ጫና ግን ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ (የመረጃው ምንጭ ፡ አልጀዚራ)
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 5/2011
አንተነህ ቸሬ