
የአትሌቲክስ አሠልጣኞች ደረጃ መስጫ ተግባራዊ ለማድረግ የሚሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ። ፌዴሬሽኑ ከአትሌቲክስ አሠልጣኞችና ባለሙያዎች ጋር በአሠራር ሥርዓትና መመሪያዎች ላይ ተወያይቷል።
ኢትዮጵያ መልካም ገጽታዋን በገነባችበት የአትሌቲክስ ስፖርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር ምስጉን የሆኑ ባለሙያዎችን አፍርታለች። ይሁንና ስመጥር አትሌቶችን ማፍራት ከቻሉ የሥልጠና ባለሙያዎች መካከል አብዛኛዎቹ ልምድን መሠረት ያደረጉ ናቸው። በዚህም ከዘመናዊውና ሳይንሳዊው ዓለም ጋር መራመድ አልቻሉም ተብለው ይወቀሳሉ። ፌዴሬሽኑ በበኩሉ የአትሌቲክስ አሠልጣኞች ደረጃ መስጫን ያዘጋጀ ሲሆን፤ አስፈላጊውን የትምህርትና የሥልጠና ደረጃ እንዲሁም የሥራ ልምድ አስቀምጧል። ይህም እአአ በ2014 ዓም የተሻሻለ ነገር ግን እስካሁን አስፈላጊ ሊሆን ያልቻለ ነው። በየሁለት ዓመቱ ይታደሳል የተባለው የአሠልጣኞች የሙያ ደረጃ መስጫ ውይይት ሲደረግበት፤ ከቶኪዮ ዓለም ሻምፒዮና በኋላ ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚችልም ነው የተጠቆመው።
አትሌቶችን ጨምሮ ከባለሙያዎች ውይይት በማከናወን ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፤ ከአሠልጣኞችና ባለሙያዎች ጋር በአሠራር ሥርዓትና መመሪያዎች ላይ ንግግር አድርጓል። በክለብና በግላቸው የሚያሠለጥኑ ስመጥር፣ አንጋፋና ወጣት ባለሙያዎች በተገኙበት መድረክ የአትሌቲክስ አሠልጣኞች ደረጃ መስጫ እንዲሁም የብሔራዊ ቡድን አትሌቶችና አሠልጣኞች ምርጫ መመሪያ ቀርቧል። ይህንን መነሻ ያደረገ ሃሳቦችም በስፋት ተንሸራሽረዋል። ወጥ የሆነ የአሠለጣጠን ሥርዓትን ተግባራዊ በማድረግ ተተኪዎችን በብዛትና በጥራት ማፍራትን ዓላማው ያደረገው የአሠልጣኞች ደረጃ መስጫ፤ ከታዳጊዎች ሥልጠና (ከ13) ዓመት በታች እስከ ብሔራዊ ቡድን አስፈላጊውን መስፈርት በግልጽ ያስቀምጣል።
ነገር ግን አብዛኛዎቹ ውጤታማና ስመጥር አትሌቶችን ያፈሩ አሠልጣኞች የሙያ ደረጃ ያግኙ መባሉ በተለይ ከትምህርት ደረጃ አንጻር አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ነው የተነሳው። አሠልጣኞችን በደረጃ መለየት ብቻውን ስፖርቱ ላይ ለውጥ ላያመጣ ስለሚችል በጉዳዩ ላይ በይበልጥ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል። ነባር አሠልጣኞች በምን መልኩ ሊስተናገዱ ይችላሉ የሚለው በስፋት የተነሳ ጥያቄ ነው። ፌዴሬሽኑ ካለው አቅም አንጻር ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ አሠልጣኝነት ሥልጠናን በምን ያህል ደረጃ እንደሚሰጥም ራሱን ሊፈትሽ ይገባል። የአትሌቶች ከሥልጠናና ውድድር ጊዜ ጋር በተያያዘ ትምህርት ለመከታተል አስቸጋሪ በመሆኑ ስለስፖርቱ በተግባር ጠንቅቀው የሚያውቁት አትሌቶች ወደ አሠልጣኝነት እንዳያድጉ የሚያደርግ ነው። መስፈርቱ ተግባራዊ የሚደረገው በብሔራዊ ቡድን ወይስ በክለቦች መሆኑን ያለየ እንደመሆኑ፤ አትሌቶችን ለብሔራዊ ቡድን ያስመረጡ አትሌቶች ከደረጃ በታች ቢሆኑ ይመረጡ ይሆን የሚለውም ጥያቄ ሆኗል።
ዓለም አቀፍ ውድድሮች በተቃረቡ ቁጥር ውዝግብ እና አከራካሪ ጉዳዮች የማያጣው የብሔራዊ ቡድን አትሌቶችና አሠልጣኞች ምርጫ መመሪያም በባለሙያዎች ገለጻ ተደርጎበታል። የምርጫ ሂደቱ ግልጽ፣ ፍትሐዊና ተጠያቂነትን ያካተተ ሥርዓት እንዲኖረው ያደርጋል የተባለው መመሪያ ላይም ውይይት ተደርጎበታል።
በአሠልጣኞች ከተነሱ ሃሳቦች መካከልም በዚህ ወቅት አብዛኛዎቹ አትሌቶች በማናጀር የሚሠለጥኑ እንደመሆኑ ለብሔራዊ ቡድን ሲመለመሉ ባስመረጡት ልክ ቡድኑን የመምራት ዕድል የሚሰጣቸው አሠልጣኞች በምን መልኩ ተግባራዊ ይደረጋል። ውስን ጠንካራ አትሌት በመያዝ በሚያስፈራሩ አሠልጣኞች ላይስ ፌዴሬሽኑ በበላይነት ውሳኔ ማሳለፍ የሚያስችል አቅም ከማዳበሩ አንጻርም ጥያቄዎች ተንፀባርቀዋል። ከማራቶን ብሔራዊ ቡድን ምርጫ ጋር ተያይዞም የተቀመጠው መስፈርት ሰዓት የሚመዘገብበት የዓለም አትሌተክስ ደረጃ አሰጣጥ አንጻር ሳይሆን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በስፋት በሚሳተፉበትና ከሚገቡበት ሰዓት ተነስቶ ሊሆን እንደሚገባም ተመላክቷል።
የተነሱ ሃሳቦችን ተከትሎም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ስለሺ ስኅን፤ መሰል ውይይቶች ለስፖርቱ እድገት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ገልጻል። ከተነሱ ሃሳቦች መካከል አብዛኛዎቹ በግብዓትነት የሚያዙ ሲሆን፤ በቀጣይም መሰል መድረኮችን በማዘጋጀት ለውይይቱ መነሻ በሆኑት የአሠራር ሥርዓቶችን በይበልጥ ለማዳበር የሚሞክር ይሆናል። ከአሠልጣኞች የሙያ ፈቃድ አንጻርም ልምድ ያላቸው አትሌቶች ከአሠራሩ ጋር በሚጓዙበት ሁኔታ ላይ የሚሠራ ይሆናል። በዚህም መሠረት አሠራሩ በመጪው ዓመት ማለትም ከዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኋላ ተግባራዊ የሚደረግ እንደሚሆንም አስረድቷል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም