
የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን አህጉር አቀፍ ውድድሮችና ጠቅላላ ጉባኤ ያካሂዳል:: ከቀናት በኋላ የሚደረጉት ሁነቶችም ስፖርቱን በማሳደግና የሀ ገርን በጎ ገጽታ በመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ተገልጿል::
የአፍሪካ ዞን አምስት ኦፕን ወርልድ ቴኳንዶ ሲርየስ፣ የአፍሪካ ወርልድ ቴኳንዶ ዩኒየን ጠቅላላ ጉባኤ እና የአፍሪካ ፕሬዚዴንሺያል የወርልድ ቴኳንዶ ውድድር በቀጣይ ሳምንት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ ከተማ ይካሄዳሉ:: የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን የሚያካሂዳቸው እነዚህ መርሀ ግብሮች በኢትዮጵያ ሲካሄዱ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑም ፌዴሬሽኑ ትናንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተጠቁሟል::
አፍሪካዊያን ሀገራት ከሌሎች አህጉራት የተወጣጡ የቴኳንዶ ስፖርተኞች በሚካፈሉባቸው ውድድሮች ላይም ወደ 400 የሚጠጉ ልኡካን ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል:: ኢትዮጵያም በውድድሩ የሚካፈሉ 26 አባላት ያሉትን ብሔራዊ ቡድን ለሁለት ወር ተኩል ለሚሆን ጊዜ ስታዘጋጅ ቆይታለች::
ተወዳጅ የሆነውና በኢትዮጵያ በርካታ አዘውታሪዎች ያሉት የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት ውድድሮች በኢትዮጵያ መካሄዳቸው ስፖርቱን ከማሳደግ አንጻር ጉልህ ድርሻ እንደሚያበረክት ይጠበቃል:: የዓለም አቀፍ ውድድር ተሳትፎ እንዲሁም አዘጋጅነት ልምድ ይገኝበታል በተባለው መርሀ ግብር በርካታ የውጭ ዜጎች የሚካፈሉበት እንደመሆኑ የሀገርን በጎ ገጽታ ለመገንባትም ያስችላል ተብሏል:: በስፖርቱ ተሳታፊ ለሆኑ ታዳጊዎችም መነሳሳትን የሚፈጥር ከመሆኑም ባለፈ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ከቻሉ ተወዳዳሪዎችም ልምድ ያገኙበታል ተብሎ ይጠበቃል::
ውድድሮቹ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የሚከናወኑ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም ብሔራዊ ቡድኗን የምታሳትፍ ይሆናል:: በቅድሚያ የሚከናወነው የአፍሪካ ዞን አምስት ኦፕን ወርልድ ቴኳንዶ ሲርየስ ውድድር የዞኑ ሀገራት ሲካፈሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በመወከል 13 ወንድና 13 ሴት ስፖርተኞች ይካፈሉበታል:: ውድድሩ ለሁሉም ክፍት እንደመሆኑም ከ50 በላይ ስፖርተኞች በግላቸው ለመሳተፍ መመዝገባቸውም ታውቋል:: ፉክክሩ የሚመራውም በኢትዮጵያውያን ዳኞች ብቻ ነው::
ቀጣይ መርሀ ግብር የሆነው የአፍሪካ ወርልድ ቴኳንዶ ዩኒየን ጠቅላላ ጉባኤ ደግሞ ሚያዝያ 16/2017 ዓ.ም ይከናወናል:: በኢሲኤ አዳራሽ በሚከናወነው ጠቅላላ ጉባኤ 40 የሚሆኑ አባል ሀገራት ተሳታፊ ከመሆናቸውም በላይ የፕሬዚዳንታዊና የሥራ አስፈጻሚዎች ምርጫም ይደረጋል:: በፕሬዚዳንታዊ ምርጫው በእጩነት ከቀረቡት መካከልም የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፕሬዚዳንት ዳዊት አስፋው ይገኙበታል:: ለመመረጥ የሚያስችሉ ሥራዎችን ያከናወኑ ሲሆን፤ በጠንካራው ፉክክር አብላጫውን ድምጽ እንደሚያገኙ ያላቸውን ተስፋም ተናግረዋል።
በአህጉር አቀፍ ደረጃ ከትልልቅ ውድድሮች አንዱ የሆነው የአፍሪካ ፕሬዚዴንሺያል ወርልድ ቴኳንዶ ውድድርም ከሚያዚያ 17-19/2017 ዓ.ም ድረስ ይደረጋል:: ዘንድሮ ለ6ኛ ጊዜ በሚካሄደው በእዚህ ውድድር ከ44 ሀገራት የተወጣጡ 385 የሚሆኑ ተወዳዳሪዎች እንደሚካፈሉም አስታውቀዋል:: ከአፍሪካውያን ባለፈ የሌሎች ሀገራት ዜጎች እንዲሁም በዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ባንዲራ የሚወዳደሩ ስደተኞችም ተጠባቂዎች ናቸው:: በታዳጊና አዋቂዎች ምድብ በሚከናወነው በእዚህ ውድድርም 12 ሴትና 11 ወንዶች የሚካፈሉ ሲሆን፤ በግላቸው ለመሳተፍ የተመዘገቡ ኢትዮጵያውያንም አሉ:: ውድድሩ የሚመራው በ32 ዳኞች ሲሆን፤ 5ቱ ኢትዮጵያውያን እንደመሆናቸው ዓለም አቀፍ ውድድር ለማወዳደር የሚያስችል ከፍተኛ እድል እንደሚያስገኝም ተጠቁሟል::
ኢትዮጵያን የሚወክለው ቡድን እአአ በ2026 ዳካር ላይ በሚደረገው የወጣቶች ቻምፒዮና ተሳትፎን የሚያረጋግጥ እንደሆነም ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል:: ጠቅላላ ጉባኤውንና ውድድሮቹን ማስተናገድ ደግሞ ልምድ ከማስገኘቱም ባለፈ እአአ በ2028 ለሚደረገው ኦሊምፒክ የአፍሪካ ማጣሪያ ውድድርን የማስተናገድ ጥያቄ ለማቅረብ እንደሚያስችልም ይታመናል::
ለእዚህ ውድድር ከአንድ ዓመት በላይ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን የሚጠቁሙት ደግሞ የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሩ ተቋም ናቸው:: ለማወዳደሪያ አስፈላጊ የሆኑ ዘመናዊ ቁሳቁስ ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት የተገዙ ሲሆን፤ ስፖንሰሮች ላይም ተሠርቷል:: ትልልቅ ሀገራት ብቻ የማዘጋጀት ዕድል የሚሰጣቸውን ውድድር ማስተናገድ ስፖርቱን ለማሳደግ እንደሚያስችልም አመላክተዋል::
በኢትዮጵያ የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት የተዘወተረ ሲሆን፤ በአፍሪካ በሚካሄዱ ውድድሮች ላይም በርካታ ሜዳሊያዎችን ማስቆጠር ተችሏል:: እአአ በ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ደግሞ በሰለሞን ቱፋ አማካኝነት ዲፕሎማ መመዝገቡ የሚታወስ ነው::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 8 ቀን 2017 ዓ.ም