ፕሮፌሽናሊዝም እና የኢትዮጵያ ስፖርት

ዜና ትንታኔ

በኢትዮጵያ ስፖርት እድገት ውስጥ ክፍተቶች ናቸው ተብለው በጥናት ከተለዩ ችግሮች መካከል አንዱ የ‹‹ፕሮፌሽናሊዝም›› ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥታዊና ሕዝባዊ የስፖርት አደረጃጀትና አሠራር በፖሊሲ ተኮር ግቦች ላይ ያለው ተፅዕኖና የኢትዮጵያ ስፖርት ልማት ስኬቶችና ተግዳሮቶች በሚል ጥናት ላይ ተመሥርቶ የተዘጋጀ ሰነድ፤ ፕሮፌሽናሊዝምን በባሕሪ፣ በግንኙነት ስልቶችና በአፈጻጸም ደረጃዎች ላይ የሚጠበቁ ደንቦችን በማቋቋም የሥራ ባህልን ማሻሻል ተገቢ መሆኑን ያመላክታል።

ስፖርት ግዙፍ ገንዘብ የሚያንቀሳቅስ የሀገራትንም ኢኮኖሚ የሚደግፍ ዘርፍ የሆነው ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ስፖርት በፕሮፌሽናል መንገድና ደረጃውን በጠበቀ አሠራር መታገዙ ደግሞ ለዚህ ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክቷል። የስፖርት ውድድሮችን የሚመሩ ሊጎችና መሰል አካላት መበራከት አስተማማኝ ገቢ በመሰብሰብና ስፖርተኞችም ከፍተኛ ገንዘብ እንዲያገኙ በማድረግ የውድድር ጥራትን በመጨመሩ የስፖርት ወዳዶች ቁጥር ቢሊዮኖችን ሊሻገር ችሏል።

በአንጻሩ በኢትዮጵያ አሁንም ድረስ ስፖርተኞችን የሚያተጋ የአመራር፣ የሥልጠና፣ የውድድር፣ የዕውቅናና ሌሎች ፕሮፌሽናል አሠራሮች ላይ ክፍተቶች እንዳሉ ብዙዎች ይስማማሉ። የፕሮፌሽናሊዝም ጽንሰ ሃሳብ በብዙ መንገድ ሊተረጎም ቢችልም እንደ ኢትዮጵያ ከውድድር አንጻር ተነጥሎ ሲፈተሽ ፌዴሬሽኖች ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ሆኖ ይገኛል። እንደ ሀገር ደረጃቸውን የጠበቁ ውድድሮች ባለመኖራቸው ስፖርተኞችን የማያበረታታ፣ ፉክክሩም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በዚህ ደረጃ በኢትዮጵያ ስፖርቶች ፕሮፌሽናል ውድድሮችን ማስፋት ያልተቻለበት ምክንያትም የበርካቶች ጥያቄ ሆኖ ይገኛል።

የሶል ኢንተርናሽናል (ACISA) መሥራች ኢንስትራክተር ዮሴፍ ነጋሽ እንደሚያስረዳው በአሠራር፣ በውሳኔና አፈጻጸም ረገድ አበረታች ሁኔታ አለመኖሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ፕሮፌሽናል ውድድሮች እንዳይስፋፉ እንቅፋት ሆኗል። ዋነኛ ትኩረቱን የቦክስ ስፖርት ላይ ያደረገው ሶል ኢንተርናሽናል፤ ኢትዮጵያ በቦክስ ስፖርት እስከ ትልቁ ኦሊምፒክ የደረሰ ተሳትፎ ቢኖራትም በአማተሮች ብቻ የሚንቀሳቀስ ስፖርት ነው።

ይህን ለመቀየርና የቡጢ ተፋላሚዎች ብቃታቸውን ሊያሳድጉ እንዲሁም ጠቀም ያለ ገቢ የሚያገኙበትን ሁኔታ ለመፍጠር የመጀመሪያ የሆነውን ፕሮፌሽናል የቦክስ ፍልሚያ አዘጋጅቶ ነበር። በዚህም ፕሮፌሽናል ቦክሰኞችን ከሌሎች ሀገር በመጋበዝና ጀማሪ (ሰሚ ፕሮፌሽናል) ቦክሰኞችን ደግሞ ከሀገር ውስጥ በማሳተፍ ለአሸናፊዎች 120ሺ ብር እንዲሁም የቀበቶ ሽልማት ተበርክቷል። ይሁንና ለኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመሪያ ሃሳቡም መልካም ከነበረው ከዚህ ውድድር ምንም ዓይነት ትርፍ አለመገኘቱን ኢንስትራክተር ዮሴፍ ያስታውሳል።

ውድድሩ በተጠበቀው የፕሮፌሽናል ደረጃ እንዳይገኝም ስፖርቱን የማስፋፋት ተልዕኮ ያለው የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ከማገዝ ይልቅ ዳር ቆሞ መመልከቱን እንደ አንድ ምክንያት ያስቀምጣል። ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ውድድር እንደታሰበው ከሞራልም ሆነ ከገንዘብ ትርፍ ስላልተገኘበት በቀጣዩን ውድድር በዩጋንዳ ለማዘጋጀት ተገዷል።

ሙሉ ለሙሉ መስፈርቱን አሟልቷል ማለት ባይቻልም ኢትዮጵያ ውስጥ ፕሮፌሽናል አካሄድን በመከተል ረገድ ሊጠቀስ የሚችለው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ነው። በማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ ከፕሮፌሽናል ስፖርት እይታ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ውስጥ መሠረታዊ ክፍተት መኖሩን ይጠቁማሉ። እንደ አቶ ክፍሌ ገለፃ፣ ፕሮፌሽናል ስፖርት ሲባል በርካታ ጉዳዮችን በውስጡ ያካተተ ሲሆን፤ ከውድድር፣ ከስፖርተኞች፣ ከአሠለጣጠን፣ ከመገናኛ ብዙኃን አዘጋገብ፣ አደረጃጀት ወዘተ አንጻር አስቀድሞ መለየት የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ።

ይህንንም ሲያብራሩ፣ ሙያውን የሚመራው አካል ስፖርቱን በተሻለ ሁኔታ የሚያውቅና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ያለው አመራር እንዲመራው ያስፈልጋል ይላሉ። ይህ ሁኔታ እንደየደረጃው ስፖርቱን(ሙያውን) መሠረት ያደረገ ሙያተኛ ሊመራው ይገባል። ውድድርን ጨምሮ እንደ ሌሎች ዘርፎች ሁሉ ሙያተኛው ስፖርቱን እንዲመራ ካልተደረገ ለውጥ ሊመጣ እንደማይችልም ስጋት አላቸው።

እንደአጠቃላይ ሲታይም ስፖርቱ የተደራጀ አካዳሚ፣ ማዘውተሪያ፣ ካምፕ፣ የወጣቶች ክህሎት ማሳደጊያ ማዕከልና ሌሎችም የለውም፤ ፕሮፌሽናል ስፖርት ደግሞ ከነዚህ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ ነው።

ስፖርቱን በበላይነት የሚመሩ ፌዴሬሽኖችና የስፖርት ማኅበራት ዘርፉን በፕሮፌሽናሊዝም ደረጃ ለመምራትና ለማሳደግ ከአደረጃጀት ጀምሮ የራሳቸው ችግሮች ቢኖሩባቸውም በመርሕና በሕግ ደረጃ እንቅፋት የለባቸውም። እንዲያውም የስፖርት ማኅበራት የሚደራጁበት መመሪያ ከዚህ ጋር በተያያዘ ደጋፊ ሁኔታዎች መኖራቸውን ሥራ አስኪያጁ ያስረዳሉ። ምቹ ሁኔታዎች እያሉ ከአፈጻጸም አንጻር ያሉባቸው ክፍተቶች ግን ሰፊ ናቸው። ሙያው ውስብስብ እንደመሆኑ ሰነዶችን ለመተግበር አስቸጋሪ ሁኔታዎች የሉም ማለት ግን አይቻልም። በመሆኑም መንግሥት በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ በመግባት ማስተካከል የሚገባው ጉዳዮች እንዳሉ ነው አቶ ሰይፈ የሚያስረዱት።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ረብጣ ገንዘብ ከሚገኝባቸውና ከፍተኛ ተመልካች ካላቸው ውድድሮች መካከል የሚጠቀሰውን ፕሮፌሽናል የቦክስ ውድድር በኢትዮጵያ በማዘጋጀት የከባድ ሚዛን ቦክሰኞችን የማፋለም ዕቅዱን የሰረዘው የሶል ኢንተርናሽናል መሥራች ኢንስትራክተር ዮሴፍ በበኩሉ፣ በዘርፉ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ የለም ይላል። በመሆኑም ስፖርቱን በበላይነት የሚመራው የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ለመሥራት የሚፈልጉ አካላት እንዳይሠሩ እንቅፋት የሚሆኑ ጉዳዮችን ለይቶ በማውጣት መፍትሔ ማፈላለግ እንደሚገባ ይጠቁማል። ለዚህም የግሉን ዘርፍ በማበረታታት፣ በአሠራር፣ በውሳኔና አፈጻጸም ላይ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ምክረ ሃሳብ ያስቀምጣል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You