የፌስቡክ የቀድሞ ሠራተኛ ኩባንያውን በሀገር ጥቅም ጉዳይ ወነጀለች

የፌስቡክ እና ኢንስታግራም ማኅበራዊ ሚዲያዎች ባለቤት የሆነው ሜታ ከቻይና ጋር የ18 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ስምምነት ለማድረግ ሲል የብሔራዊ ደህንነትን ችላ ብሏል ስትል የድርጅቱ የቀድሞ ሠራተኛ ሳራ ዋይን ዊሊያምስ ለአሜሪካ ምክር ቤት ተናገረች። ከዚህ በፊት በፌስቡክ የዓለም አቀፍ የፐብሊክ ፖሊሲ ዳይሬክተር የነበረችው ሳራ ዋይን ዊሊያምስ፣ የድርጅቱ ኃላፊዎች ለቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የአሜሪካውያንን ጨምሮ የሜታ ተጠቃሚዎችን መረጃዎችን እንዲያገኙ ፈቅዷል ብላለች።

ሜታ የመረጃ አሹላኪዋን፣ ዋይን ዊሊያምስን ውንጀላ ውድቅ አድርጓል። “የሳራ ዋይን ዊሊያምስ ምስክርነት ከእውነታው የተፋታ እና በሐሰት ውንጀላዎች የተሞላ ነው” ሲል የሜታ ቃል አቀባይ ራያን ዳንኤልስ ተናግሯል። ዳንኤልስ የሜታ የበላይ ኃላፊ ማርክ ዙከርበርግ ኩባንያቸው በቻይና መስጠት ስለሚፈልገው አገልግሎት በይፋ ተናግረዋል ሲሉ አክለዋል። “እውነታው ይህ ነው፤ በአሁኑ ወቅት በቻይና ምንም ዓይነት አገልግሎት እየሰጠን አይደለም።”

ሜታ ይህንን ይበል እንጂ ኩባንያው አሁንም በቻይና ከሚገኙ የማስታወቂያ ድርጅቶች ገቢ ያገኛል። ዋይን ዊሊያምስ በአሜሪካ ምክር ቤት (ሴኔት) የሕግ ንዑስ ኮሚቴ ፊት ቀርባ ስለ ሜታ ባስረዳችበት ወቅት፣ የፌስቡክ እና የኢንስታግራም ማኅበራዊ ሚዲያዎች እናት ኩባንያ ከቤይጂንግ ጋር የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ተቃዋሚዎችን በማፈን ረገድ “እጅ እና ጓንት” ሆኖ ሲሠራ ነበር ብላለች።

በተለይ ደግሞ ሜታ ቻይና በስደት አሜሪካ የሚኖሩትን የጉኦ ዌንጉኡ የፌስቡክ አካውንት እንዲዘጋ ላቀረበችው ጥያቄ ተገዢ ሆኗል ብላለች። ሜታ በበኩሉ የጉኦ ገጽ እንዲታገድ እና ጽሑፋቸው እንዳይወጣ የሆነው የኩባንያውን ፖሊሲ የሚቃረን ሆኖ በማግኘቴ ነው ብሏል። “የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ እና ማርክ ዙከርበርግ የሚጋሩት አንድ ነገር ተቺዎቻቸውን ዝም ማሰኘት መፈለጋቸው ነው። ይህንን ከራሴ ልምድ ተነስቼ መናገር እችላለሁ” ስትል በሴኔት ፊት ቀርባ ምስክርነቷን ስትሰጥ ተናግራለች።

በመጋቢት ወር ዋይን ዊሊያምስ በፌስቡክ ውስጥ ስትሠራ የነበሯትን ገጠመኞች የያዘ “ኬርለስ ፒፕል” የተሰኘ የግል ማስታወሻዋን አሳትማለች። ሜታ ግለሰቧ በድርጅቱ ውስጥ ስትሠራ የነበሯትን ገጠመኞች ያካተተችበት መጽሐፏን በአሜሪካ እንዳታስተዋውቅ ያቀረበው የይታገድልኝ ጥያቄ ለጊዜው ተቀባይነት አግኝቷል። በወቅቱ ሜታ “ሐሰተኛ እና ስም የሚያጠለሽ መጽሐፍ መታተም አልነበረበትም” ብሎ ነበር።

ረቡዕ ዕለት የአሜሪካ ሴኔት አባላት በተገኙበት መረጃ አሹላኪዋ ምስክርነቷን ስትሰጥ፣ ከዚህ በፊት የፌስቡክ ሠራተኞች የነበሩት እና ምስክርነታቸውን የሰጡት ፍራንሲስ ሀውገን እና አርትሮ ቤዣር ተገኝተዋል። ሴናተር ሀውሌ “ለምንድን ነው ፌስቡክ ግለሰቧ ያላትን መረጃ እንዳትሰጥ ለመከላከል ይህንን ያህል የሚጥረው?” ሱሉ ጠይቀዋል።

በአውሮፓውያኑ ጥር 2024 ዙከርበርግ ኮንግረስ ፊት በቀረበበት ወቅት፣ ሴናተር ሀውሌ በማኅበራዊ ሚዲያው ልጆቻቸው መጎዳታቸውን የገለፁ ቤተሰቦችን ይቅርታ እንዲጠይቅ ጠይቀውት ነበር። በወቅቱ በምክር ቤቱ ውስጥ በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ በተሠራጩ መረጃዎች የተነሳ ልጆቻቸው ራሳቸውን የጎዱ ወይንም የሞቱባቸው በርካታ ቤተሰቦች ከዙከርበርግ ጀርባ ተቀምጠው ነበር። ዙከርበርግ እናንተ ባለፋችሁበት ሁኔታ ውስጥ “ማንም ማለፍ የለበትም” ሲል ተናግሯል። ረቡዕ በነበረው ምስክርነት የመስማት ሂደት ላይ ሴናተር ሀውሌ ዋይን ዊሊያምስ በመናገሯ ገንዘብ ቅጣት ሊጣልባት እንደሚገባ መገለጹን ተናግረዋል።

“ምንም እንኳ የምተናገረው እውነት ቢሆንም ፌስቡክን በአደባባይ እየወነጀለች በየጊዜው ለምታደርሰው ጉዳት 50 ሺህ ዶላር ለመቅጣት አስፈራርተዋል” ያሉት ሴናት ሀውሌ፣ “ዛሬ እንኳ እዚህ ተቀምጠን፣ ፌስቡክ ሙሉ በሙሉ የገንዘብ ቀውስ ውስጥ እርሷን ለማስገባት እየሞከረ ነው” ብለዋል።

ረቡዕ ዕለት ኩባንያው እንደተናገረው ግለሰቧ ድርጅቱን በአውሮፓውያኑ 2017 ስትለቅ የፈረመችው ሰነድ በእያንዳንዱ ለምትፈጽመው ጥሰት እና ለምታደርሰው ጉዳት የ50 ሺህ ዶላር ቅጣት ለመክፈል ተስማማታለች ብሏል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You